በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ወዴት እያመራ ነው? መፍትሔውስ ምንድነው?

የዶላር ምልክት እና የኢትዮጵያ አንድ ብርን የሚያሳይ ሚዛን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰናይት ‘ሱዙኪ ዲዛዬር’ የተሰኘች 1200 ‘ሲሲ’ ያላትን መኪና ባለፈው ግንቦት የገዛችው 1.38 ሚሊዮን ብር ነበር።

ከአምስት ወር በኋላ ተሽከርካሪዋ 2.2 ሚሊዮን ብር እየተሸጠች እንደሆነ ቢቢሲ አዲስ አበባ ከሚገኙ መኪና ሻጮች መረዳት ችሏል።

በአገረ ሕንድ የምትመረተው ዲዛዬር ሦስተኛ ምርት (ሰርድ ጄነሬሽን) መኪና ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ ለገበያ ውላለች።

የመኪናዋ ዋጋ በአሜሪካ ዶላር ሲሰላ 10 ሺህ ዶላር ገደማ ነው። ይህ አሁን ባለው የባንክ ምንዛሪ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል።

ይህ ዋጋ በጎረቤት አገር ኬንያ ከ1.3 እስከ 1.4 ሚሊዮን ሽልንግ ይገመታል። ይህ ወደ ዶላር ሲመታ 11 ሺህ ዶላር ይጠጋል።

በኡጋንዳ ደግሞ መኪናዋ በካምፓላ ገበያ በ43 ሚሊዮን የኡጋንዳ ሽልንግ ትሸጣለች። ይህም በዶላር ወደ 11 ሺህ ገደማ ይመነዘራል።

ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት መጋቢት ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ34.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጦ ነበር።

የዋጋ ንረቱ ለምግብነት በሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እና እህሎች፣ ቅመማ ቅመም እና ዘይት፣ ቅቤ እና ቡና ላይ ይጠነክራል።

ሄኖክ የልጁን አንደኛ ዓመት ልደት “አነስ ባለ ድግስ” ለማክበር 40 ሺህ ብር ገደማ እንዳወጣ ለቢቢሲ ገልጿል።

“ከባለቤቴ ጋር ብዙ ሰው አንጠራም ብለን ተስማማተን ቤተሰብ ብቻ ነው ልደቱን የታደመው” ይላል።

“ዲኮር ብቻ 6 ሺህ ብር የፈጀው። ዲኮር ስልህ ፊኛና ‘ዲም ላይት’ እንጂ ሌላ ምንም አልነበረውም። ለባለቤቴ ባሕላዊ ቀሚስ፤ ለእኔና ለሁለት ልጆቼ ደግሞ ከላይ የሚለበስ ልብስ 10 ሺህ ብር፤ ስጋና ሽንኩርት እንዲሁም ዘይትና አትክልት 11 ሺህ ብር ገደማ፤ ኬክ 3 ሺህ አውጥቻለሁ።”

ሄኖክ ከልጁ ልደት በኋላ ትራንስፖርትን ጨምሮ ለሌሎች ጥቃቅን ወጪዎች ያወጣውን ሲያሰላ 40 ሺህ እንደደረሰ ሲረዳ ግራ እንደተጋባ ይናገራል።

ይህ ብቻ አይደለም ለትልቁ ልጁ ደብተር ሊገዛ ወጥቶ ከብዙ አሰሳ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ስሙ የገነነ ደብተር አንዱን ደርዘን 880 ብር አውጥቶ ሸምቶ ተመልሷል።

የዋጋ ግሽበት ጉዳይ በማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ዘንድም ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ከተማ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ተብሎ በሚታወቀው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ወጣት፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለይ የቲማቲም እና የነጭ ሽንኩርት ዋጋ እጅግ መናሩን ለቢቢሲ ይናገራል።

“አንድ ኪሎ ቲማቲም በችርቻሮ ዋጋ እንደ ጥራቱ ከ55 አስከ 70 ብር፤ ነጭ ሽንኩርት ደግሞ እስከ 250 ብር በኪሎ ይሸጣል።”

የዋጋ ግሽበት ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዋጋ ግሽበት የአንድ ሸቀጥ አሊያም አገልግሎት ዋጋ መናር ነው።

ቬኒዝዌላ በዓለም ትልቁ የዋጋ ግሽበት ያለባት አገር ናት። በዚህ ዓመት መጀመሪያ (2022) በአገሪቷ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 1198.0 በመቶ ነበር።

በዚህ ምክንያት በገበያ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ በፍጥነት የሚቀያየር በመሆኑ የንግድ ተቋማት የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ዋጋ መተመን ትተው ደንበኞች በየቀኑ የሚኖረውን ዋጋ እንዲጠይቁ ብለው ነበር።

እንዲህ ዓይነት የዋጋ ንረት፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አሊያም ‘ሃይፐር ኢንፍሌሽን’ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የመንግሥት ወጪ ከልክ በላይ ሲሆን እና መንግሥት ወጪዎቹን ለመሸፈን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በብዛት ሲያትም የሚከሰት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ነው።

‘ሃይፐር ኢንፍሌሽን’ ብዙውን ጊዜ በጦርነት፣ በሥርዓት ለውጥ ወይም ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተከትሎ የሚመጣ ነው።

ቬኒዝዌላ፤ ከደቡብ አሜሪካ አገራት ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ የነበራት ነበረች።

አብዛኛው የአገሪቱ ገቢ ከነዳጅ ንግድ የሚገኝ ስለነበረ በ80 እና 90ዎቹ የነዳጅ ዋጋ ሲዋዥቅ ኢኮኖሚዋን ለአደጋ አጋለጠው።

የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ በ2014 ከነበረው 100 ዶላር በ2016 ከ30 ዶላር በታች ሲወርድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ኪሳራ ደረሰበት።

ከአፍሪካ አገራት ሱዳን፤ በባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ 340.0 በመቶ የዋጋ ንረት ተመዝግቦባታል። በዚህ ምክንያት በዓለም ሁለተኛ ትልቁ የዋጋ ንረት ያለባት አገር ሆናለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሱዳን የምግብና መጠጥ ዋጋ መናሩ እንዲሁም ዶላር በጥቁር ገበያ ያለው ምንዛሪ መናሩ የዋጋ ግሽብቱ ከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ እያሳየ ነው።

ይህ የዋጋ ንረት የወለደው የሱዳን ተቃውሞ የቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል-ባሽር በ2019 ከስልጣናቸው እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል።

በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ወደ 12.2 በመቶ ያደገ ሲሆን አብዛኛዎቹ አገራት ጠንካራ የማዕከዊ ባንክ ሥርዓት ስለሌላቸው ነው ይላል ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ።

የዋጋ ግሽበት፤ በስሪ ላንካ የነበረው ፖለቲከዊ አለመረጋጋት እንዲጋጋል ከማድረጉም በላይ ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ከሥልጣናቸው ወርደዋል።

የዋጋ ግሽበት በአሁኑ ወቅት በርካታ የዓለም አገራትን እየፈተነ ሲሆን የኤነርጂ (ኃይል አቅርቦት) ዋጋ መጨመር፣ የምግብ እና የሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለዚህ መባባስ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይነገራል።

ግራፍ

የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 37.2 በመቶ ነበር። ይህ በፈረንጆቹ 2011 በኋላ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ነው።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ነሐሴ 2014 ዓ.ም. የተመዘገበው ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 32.5 በመቶ ደርሷል።

ኤጀንሲው በዚህ ወር የዋጋ ግሽበቱ መጠን ዝቅ ያለበት ምክንያት የምግብ ዋጋ ግሽበት አንጻራዊ መረጋጋት ስላሳየ ነው ይላል።

ሆኖም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካላቸው አገራት ተርታ ትገኛለች።

በአፍሪካ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት የተመዘገበባት አገር ዚምባብዌ ስትሆን ይህም 285 በመቶ ነው። በተከታይነት ደግሞ በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን በ125 በመቶ የሸቀጦች የዋጋ ሁለተኛ ናት።

የፋይናንስ አማካሪው እና የኦዲት ባለሙያው ጥላሁን ግርማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው ጋር የሚያያዝ ነው” ይላሉ።

ባለሙያው “ዓለም እንዲህ ያለ የዋጋ ግሽበት አይታ አታውቅም” ሲሉ የዓለም አገራት ችግር ላይ እንደወደቁ ያስገነዝባሉ።

በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄድ ያለው ጦርነት እንደ ነዳጅ፣ ስንዴ፣ ዘይትና ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጨመረበት ወቅት “የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ነዳጅ ላይ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ማንሳቱ ችግሩ የበለጠ እንዲባባስ አድርጓል” ይላሉ።

“በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በሚጨምርበት ወቅት የሁሉም ምርቶች ዋጋ ከፍ ይላል። ከነዳጅ ጋር በቀጥታ ጋር የሚገናኙ ዘርፎች ብቻ ሳይሆን የማይመለከታቸውም መጨመራቸው አይቀርም።”

አቶ ጥላሁን አክለው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተሄድ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት “ለኑሮ ውድነት መባባስ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል” በማለት ግጭቱ በጊዜ ካልተቋጨ ሁኔታው እንደሚባባስ ያሳስባሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፍጥነት እየጨመረ የሄደውን የተሽከርካሪዎች ዋጋ መናር እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ባለሙያው የዶላር እጥረት ትልቅ ድርሻ አለው ይላሉ።

“ወደ አገር ቤት መኪና የሚያስገቡ አስመጪዎች እንደሚፈልጉት ዶላር እየተፈቀደላቸው አይደለም። ተፈቅዶላቸው ዶላር አግኝተው ሲያስገቡ ደግሞ ትልቅ ትርፍ በማግኘት ነው የሚሸጡት።”

የተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን የሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ መናር ዶላር በጥቁር ገበያ ካለው ዋጋ ጋር እንደሚገናኝ አቶ ጥላሁን ያስረዳሉ።

“አንድ የአሜሪካን ዶላር ጥቁር ገበያው ላይ እስከ 90 ብር እየተመነዘረ ነው። መንግሥት ደግሞ በ53 ብር ተምኖታል። መኪና የሚያስገቡ አስመጪዎች ዶላር ከባንክ የሚጠይቁት ለይምሰል ነው እንጂ ዶላር ከጥቁር ገበያው እየገዙ ነው መኪና የሚያስገቡት። ታዲያ ይህንን የጥቁር ገበያ ዋጋ ነው ለገዢዎች የሚያስተላልፉት።”

የቢዝነስ ድረ-ገፁ ብሉምበርግ ረቡዕ ዕለት ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ጥቁር ገበያ አንድ የአሜሪካን ዶላር እስከ 92 ብር እየተመነዘረ ነው ሲል ስማቸውን ያልተጠቀሱ ምንጮችን በመጥቀስ አስነብቧል።

በተቃራኒው ባንኮች አንድ ዶላር በ52.5 ብር እየመነዘሩ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ብሉምበርግ፤ ዶላር በጥቁር ገበያውና በባንክ መካከል ላለው ልዩነት ትልቁ ምክንያት የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት ነው ሲል የማዕከላዊ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ፍቃዱ ድጋፌን ዋቢ በማድረግ ፅፏል።

ኢትዮጵያ በዋጋ ንረት ከአፍሪካ አገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ግራፍ

መፍትሔው ምንድነው?

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በምግብ እና በምግብ ነክ ቁሳቁሶች እንዲሁም በግንባታ ግብአቶች ላይ ነው።

መንግሥት በተለያዩ ወቅቶች ለሸቀጦች እና ለቁሳቁሶች የዋጋ ተመን ቢያወጣም መሰል ፖሊሲዎች ከጥቂት ሳምንት በላይ ተግባራዊ አይሆኑም።

ለምሳሌ በቅርቡ የሲሚንቶ ዋጋ መናርን ተከትሎ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዲስ የዋጋ ተመን ማውጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ሲሚንቶ ከፋብሪካ የሚወጣበት አዲሱ የዋጋ ተመን ዝቅተኛው 510 ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር ከ44 ሳንቲም እንዲሆን ሚኒስቴሩ ወስኗል።

ነገር ግን ይህ አዲስ ተመን ከወጣ በኋላ ሲሚንቶ እስከ 1050 ብር እየተሸጠ እንዳለ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ደላላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውጭ አገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሠሩ መንግሥት መፍቀዱን ተከትሎ ያናገርናቸው የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀ-መንበር ዘመዴነህ ንጋቱ ባንኮቹ ዶላር ይዘው መምጣታቸው ችግሩን ሊያቃልል እንደሚችል ያምናሉ።

“እንደ አጭር ጊዜ መፍትሔ መንግሥት፤ ሕዝቡ በየቀኑ መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ድጎማ ማድረግ አለበት” የሚሉት የፋይናንስ አማካሪው አቶ ጥላሁን ደግሞ “ነገር ግን ለዋጋ ግሽበት ዋናው መፍትሔ የግብር አሰባሰብ።”

“ለምሳሌ እኔ ለተሽከርካሪዬ የመድን ፈንድ ለመክፈል በቅርቡ ሄጄ ነበር። ለአንድ ዓመት 125 ብር ብቻ ነው ያስከፈሉኝ። ይህ ምን ያደርግላቸዋል?” በማለት በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

“የግብር አሰባሰብ ሂደቱ በደንብ መታየት አለበት። ግብር ማለት ካለው ላይ ሰብስበህ ለሌለው እንደመስጠት ነው። በዚህ ላይ መንግሥት ጠንክሮ መሥራት አለበት።”

ከዚህ ቀደም የዋጋ ግሽበትን አስመልክቶ ያናገርናቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) “ችግሩ እጅግ ውስብስብ ስለሆነ” የአጭር ጊዜ መፍትሔ አለው ብለው እንደማያምኑ ገልጠዋል።

ለንዶን የሚኖሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ ደግሞ “መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ መቀነስና አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶችን ማቆም፣ አስፈላጊ የሚባሉ ፕሮጀክቶችንም ቢሆን ለጊዜው መፍትሔ እስኪገኝ ማዘግየት አለበት” ሲሉ መክረዋል።

“የኢትዮጵያን ብር የመግዛት አቅም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የማውረድ እንቅስቃሴ ወደ አገር ቤት የሚገቡ እቃዎችን ስለሚያንር በአስቸኳይ መቆም አለበት፤ መንግሥት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስድ ከሆነ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ውጤት ማየት ይቻላል” ይላሉ አብዱልመናን።

የዓለም ባንክ፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ አገራት የሕዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ መትጋት አለባቸው ሲል ይመክራል።