በአሜሪካ አንድ ጨቅላ ከተኩላ ጋር በተዳቀለ ውሻ ተነክሶ ሞተ

የተኩላ እና ውሻ ድቅል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካዋ አላባማ ግዛት ቤተሰቦቹ በሚያሳድጉት የተኩላ እና ውሻ ድቅል ተነክሶ የሦስት ወር ህጻን መሞቱን ፖሊስ አስታወቀ።

ህጻኑ ባለፈው ሐሙስ ቼልሲ ውስጥ ህይወቱ ያለፈው በእንስሳው በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ነው።

የተኩላ እና ውሻ ድቅሉ በእንስሳት ሐኪሞች ድጋፍ መገደሉንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

የከተማዋ ከንቲባ የህጻኑን ሞት “ያልተጠበቀ እና አሳዛኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

“በቼልሲ የሚገኝ አንድ ህጻን በቤተሰቦቹ የቤት እንስሳ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ወደ ህክምና ጣቢያ ቢወሰድም ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ አልፏል” ሲሉ ከንቲባው ቶኒ ፒክልሲመር ገልጠዋል።

ፖሊስ የእንስሳት ጥቃት መድረሱን የሚገልጽ ስልክ ጥሪ ከደረሰው በኋላ በመኖሪያ ቤቱ መድረሱን አስታውቋል።

ህጻኑ ወደ ሆስፒታል ቢወሰደም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።

ፖሊስ እንስሳውን “የተኩላ ድቅል” ያለው ሲሆን የህጻኑ ቤተሰቦች እንደቤት እንስሳ ያኖሩት ነበር ተብሏል።

ህጻኑን ለሞት የበቃበትን ሁኔታ እንደሚያጣራም ፖሊስ ጨምሮ ገልጧል።

ከንቲባ ፒክልሲመር ለቢቢሲው አሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት አደጋው በደረሰበት ወቅት ሌሎች ህጻናትም ቤት ውስጥ ነበሩ።

እአአ በ2018 በደረሰ ተመሳሳይ የተኩላ እና ውሻ ድቅል ጥቃት ቨርጂንያ ውስጥ የስምንት ቀን ህጻን ህይወት አልፏል።

የውሻ እና ተኩላ ድቅል ምንድን ነው? እንደ ቤት እንስሳስ ማሳደግ ይቻላል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሚኒሶታ የሚገኘው የተኩላ ማዕከል እንደሚለው ከሆነ ድቅል ተኩላ የሚዳቀለው ከተኩላ እና ከውሻ ጋር ነው።

“ሁለቱ ዝርያዎች የሚዳቀሉ እና ውጤታማ ዝርያ የሚሰጡ” መሆኑን በድረ ገጹ ገልጿል።

“በሌላ አገላለጽ ተኩላ እና ውሻ መራባት የሚችሉ ሲሆን የሚገኙት ዝርያዎችም በተመሳሳይ የተዳቀለ ዝርያ መፍጠር የሚችሉ ናቸው።”

እነዚህ የሚዳቀሉት ዝርያዎች በበርካቶች ዘንድ የተኩላ-ውሻ (wolfdogs) ከሚባሉት ጋር ውዥንብር ሲፈጥሩ ቢታይም የተለዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተኩላ-ውሻ የሚባሉት ከተለመደው የሚበልጥ በተፈጥሮ የተኩላ ዝርያ ያለባቸው መሆናቸውን ጂስል ናርቫዬዝ ሪቬራ የተባሉት የዓለም አቀፍ የተኩላ ማዕከል ባልደረባ ተናግረዋል።

አሜሪካ ውስጥ ከተኩላ-ውሻዎች አንጻር ከውሻ እና ተኩላ የተዳቀሉ ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ማዳቀሉ የተሻለ ዝርያ ይሰጣል አይሰጥም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው።

እንደየዓለም አቀፍ የተኩላ ማዕከል ከሆነ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናው የተኩላ እና ውሻን ድቅል እንደቤት እንስሳ በማሳደግ የተሳካላቸው።

የተኩላ ዝርያው መጠን ከፍ ባለ ቁጥር እንደቤት እንስሳ ለማሳደግ አስቸጋሪነቱም ይጨምራል።

አሜሪካ ውስጥ ሰዎች በርካቶችን ሳይዘጋጁ በመግዛታቸው ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩትን በየጎዳናው እንደሚለቋቸው ተገልጿል።

የተዳቀለ ተኩላ እና ውሻ ማሳደግ ባላቸው ውስብስብ እና የማይገመት ባህሪ ምክንያት እንደቤት እንስሳት ለመንከባከብ አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል ሲሉ ናርቫየዝ ተናግረዋል።

“ለማሳደግ ከወሰኑ ብዙ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ተገቢ ነው። በተለይም ልጆች ካሉ ጉዳዩን ጠንከር ያደርግዋል” ሲሉ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

የአሜሪካ የፌደራል ህግ የተኩላ እና ውሻ ድቅሎችን እንደቤት እንስሳት ማሳደግን ይፈቅዳል።

የተለያዩ ግዛቶች ግን ማዳቀል እና ባለቤት መሆን ላይ የተለያየ ህግ አላቸው።

እንደኢሊኖይ፣ ሚቺጋን እና ኒው ዮርክ ያሉት ግዛቶች የተኩላ እና ውሻ ድቅሎችን እንደቤት እንስሳት ማሳደግን በህግ ከልክለዋል።

በአላባማ የተኩላ እና ውሻዎችን ድቅል ማሳደግ ቢፈቀድም በአያያዝ እና በአስተዳደጋቸው ዙሪያም ህግ ወጥቷል።

እንግሊዝ ውስጥ በአደገኛ እንስሳት ህግ መሠረት ከተኩላ የተዳቀሉ የመጀመሪያ ትውልዶችን ለማሳደግ ፈቃድ ያስፈልጋል።

ከድቅል የተገኙ የተገኙት ዝርያዎች ሦስተኛ ትውልድ ከደረሱ በኋላ ማሳደግ ግን ህጋዊ ነው።