በሎስአንጀለስ ሶስት የጎዳና ተዳዳሪዎችን እንደገደለ የተጠረጠረው ግለሰብ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሳምንት በፊት በሎስአንጀለስ ከተማ አራት ሰዎችን ተኩሶ እንደገደለ የተጠረተጠረው ግለሰብ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለ።
ይህ ግለሰብ ገድሏቸዋል ተብሎ ከተጠረጠሩት አራት ሰዎች፣ ሶስቱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሲሆኑ ከተማውን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል።
ጄሪድ ጆሴፍ ፖዌል ተባለው የ33 ዓመቱ ግለሰብ በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ብቻቸውን መንገድ ላይ የሚያድሩ ግለሰቦችን ኢላማ ማድረጉ ተገልጿል።
ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት የመኪና የሚያስጠግንበትን ግለሰብ ተኩሶ በመግደልና በመዝረፍ ተጠርጥሮ ታስሯል።
ፖዌል አራት ግድያዎችን በመፈጸም የተከሰሰ ሲሆን ፍርድ ቤት የዋስ መብቱን በመከልከል እንዲታሰር ወስኗል።
በተጨማሪም ዘረፋ በመፈጸም እና ህገ ወጥ መሳሪያ በመታጠቅም ተከሷል።
ሰውዬው በአራት የተለያዩ ቀናት ተጋላጭ ሰዎችን ሆን ተብሎ በሚመስል መንገድ ኢላማ እንዳደረጋቸው ተጠርጥሯል።
የ37 ዓመቱ ጆዜ ቦላኖስ ተኝቶ ባለበት መንገድ ላይ በተጠርጣሪው የተገደለ የመጀመሪያ ሰው እንደሆነ ተገምቷል።
ይህ ከሆነ ከ24 ሰዓታት በኋላ ጋሪ የሚገፋው የ62 ዓመቱ አዛውንት ማርክ ዲገስ በሎስአንጀለስ ከተማ ተገድሎ ተገኝቷል።
ቀጥሎ ባለው ቀን ማለዳ ላይ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ በተተኮሰበት ጥይት ሞቶ ተገኝቷል። ቤተሰቦቹ ባለመገኘታቸው ምክንያት ፖሊስ እስካሁን ሟቹን በስም አልጠቀስም።
ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ የሎስአንጀለስ ፖሊስ አዛዥና ከንቲባ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ኢላማ ያደረገ ተከታታይ ግድያ ሊኖር እንደሚችል አሳውቀው ነበር።
ፓዌል ባለፈው ረቡዕ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ ሌላ ግለሰብን እንደገደለ ተጠርጥሯል።
በዚያ ቀን የሑለት ልጆች አባት የሆነውን የ42 ዓመት ግለሰብ ገድሎ በመዝረፍ መጠርጠሩን ፖሊስ ገልጿል።
የተጠርጣሪውን የመኪና ሰሌዳ ለመለየት ፖሊስ አወዛጋቢ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ አውሏል።
ይህ ቴክኖሎጂ የሰዎችን ግላዊ ነጻነት ይጋፋል ቢባልም የሎስአንጀለስ ፖሊስ ሊመጣ የሚችል ጉዳትን ለመቀነስ እንደተጠቀመበት አስታውቋል።
የሎስአንጀለስ ፖሊስ አዛዥ ተሽከርካሪው ሶስት የጎዳና ተዳዳሪዎችን የገደለው ግለሰብ የሚጠቀምበት እንደሆነ ታምኗል።
አዛዡ ጨምረውም ከተጠርጣሪው ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው መሳሪያ ሶስቱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከተገደሉበት ጋር እንደሚመሳሰል አስረድተዋል።
ተጠርጣሪው ከተያዘ በኋላ በትላንትናው ዕለት አጭር የፍርድ ቤት ቆይታ የነበረው ሲሆን ለፈረንጆቹ ጥር 8 ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በካሊፎርኒያ 170 ሺህ ቤት አልባ/ ጎዳና ተዳዳሪዎች የሚኖሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 46 ሺህ የሚሆኑት በሎስአንጀለስ የሚኖሩ መሆናቸውን የከተማዋ ቤትአልባ ሰዎች አገልግሎት ባለስልጣን ይጠቅሳል።
በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
ባለፈው ወር በካሊፎርኒያ መገድ ላይ የተኛ ጎዳና ተዳዳሪ ከመሞቱ ጋር ተያይዞ አንድ ግለሰብ ክስ ተመስርቶበታል።
ባለፈው አርብ በላስቬጋስ፣ ኔቫዳ ማንነቱ እስካሁን ያልታወቀ ታጣቂ ጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ተኩሶ አንዱ ሲሞት ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ተጎድተዋል።












