ዋነኛ ምልክቱ የጀርባ ሕመም የሆነው የደም ካንሰር ዓይነት

የዚህ ካንሰር ዓይነት ዋነኛ ምልክቱ የጀርባ ህመም ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መልቲፕል ማይሎማ (Multiple myeloma) የደም ሥርዓትን የሚያጠቃ እና በብዛት ያልተለመደ የደም ካንሰር ዓይነት ነው።

በብዛት በኩላሊት እና በአጥንት ላይ የተለያዩ እክሎችን ያስከትላል።

በዚህም የተነሳ የሕመም ምልክቶቹ ከሌላ ሕመም ለመለየት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ይህ ሕመም በሽታ ተከላካይ የሆኑትን ነጭ የደም ህዋሳትን፣ ፕላዝማ ህዋሳትን ያጠቃል።

እነዚህ የተጠቁ ህዋሳት ደግሞ የተበላሹ ህዋሳትን በመፈጠር እየተባዙ፣ ጤናማ ያልሆነ የሰውነት በሽታ ተከላካይ ህዋሳትን ያመርታሉ።

ይህም ኤም ፕሮቲን ( M-protein) ወይንም ሞኖክሎናል ፕሮቲን (monoclonal protein) ይሰኛል።

እነዚህ ፕሮቲኖች የተለያዩ የሰውነት ክፍላችን ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ 'መልቲፕል' የሚል ስያሜን አግኝተዋል።

በዚህ ካንሰር የተያዙ ሰዎች ተጨማሪ ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ቀድሞ የጀርባ ሕመም ይኖራቸዋል።

ይህ ምናልባት በሚተኙበት ወቅት ምቾት በማጣት የሚፈጠር ሊሆን ይችላል። ካልሆነም በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ጠንካራ ልምምድ ከማድረግ ወይንም ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።

በንግድ ሥራ የተሰማራው የ37 ዓመቱ ሉዊዝ ፈርናንዶ ፎንቴኔል በርካታ የህክምና ምርመራዎችን እና ክትትሎችን ካደረገ በኋላ ነው በዚህ የካንሰር ዓይነት መያዙ የታወቀው።

“በጣም ነበር ሕመም የሚሰማኝ። ነገር ግን የመጀመሪያው ስብራት ከሰባት ወር በፊት ካጋጠመኝ በኋላ ነው ሕክምና ያገኘሁት። ስለ ሕመሜ ያለኝን ጥርጣሬ ያነሳሁት እኔ ራሴው ነኝ። ኢንተርኔት ላይ የተወሰነ ነገር አንብቤ ስለነበር" በማለት ያስታውሳል።

ልክ ሉዊዝ ፈርናንዶ እንዳጋጠመው ሁሉ፣ ይህ የካንሰር ዓይነት የአጥንትን ጥንካሬ በማዳከም ስብራት ሊከተል ይችላል።

ይህ ደግሞ የሚከሰተው ከፍተኛ የፕላዝማ ሴሎች በመቅኒ ውስጥ እንዲፈጠሩ በማድረግ የሄማቶፖየቲክ ህዋሳት ሲቀንሱ ነው።

በዚህ የካንሰር ዓይነት የተነሳም የኩላሊት ሥራ ሊስተጓጎል ይችላል።

ምንም እንኳ ይህ የካንሰር ዓይነት በብዛት የሚያጋጥም ባይሆንም፣ ከደም የካንሰር ዓይነቶች መካከል በመከሰት ሁለተኛው ነው።

በብራዚል ከ100 ሺህ ሰዎች መካከል አራቱ በዚህ የካንሰር ዓይነት ሊያዙ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።

ይህም ማለት በየዓመቱ 7600 አዳዲስ በዚህ ካንሰር የሚያዙ ሰዎች ይኖራሉ።

ይህ የካንሰር ዓይነት እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ ሰዎቸን የሚያጠቃ ቢሆንም በወጣቶችም ላይ ታይቶ ይታወቃል።

መልቲፕል ማይሎማ በሽንት አልያም በደም ምርመራ ሊታወቅ እችላል።

መልቲፕል ማይሎማ ፈጽሞ የሚፈውስ መድኃኒት ባይኖርም፣ ነገር ግን በዚህ የካንሰር ዓይነት የተያዙ ግለሰቦች ረዥም ጊዜ ጤናቸው ተሻሽሎ መኖር እንዲችሉ ማድረግ እንደሚቻል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በይበልጥ ቀድሞ የተደረሰበት ከሆነ የግለሰቦችን ጤና የበለጠ አደጋ ላይ ከመጣሉ በፊት ለመከላከል እንደሚቻል ያስረዳሉ።

ይህንን የካንሰር ዓይነት ለማከም ኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የመቅኒ ንቅለ ተከላ በማካሄድ ሕክምናው ይሰጣል።

ሉዊዝ ፈርናንዶ የመቅኒ ንቅለ ተከላ ቢያካሄድም ሕመሙ ዳግም አገርሽቶበት መሰቃየቱን ያስታውሳል።

ከ28 ዓመቴ ጀምሮ ከሕመም ውጪ ያሳለፍኩበትን ቀን አላስታውስም የሚለው ሉዊዝ፣ 28 ቀናት በሆስፒታል 21 ቀናት ደግሞ ቤቱ ሆኖ የተለያዩ መድኃኒቶችን ቅንብር እየወሰደ እና ክትትል እየተደረገለት ሕክምናውን አካሂዷል።

በዓመታት ውስጥ ከበሽታው ጋር ተዋውቆ እንዴት መኖር እንዳለበት የተረዳው ሉዊዝ አሁን በተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ያስረዳል።