በግብፅ በወርቅ የተለበጠ ጥንታዊ አጽም መገኘቱ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በግብፅ ለ4300 ዓመታት ያልተከፈተ እና በወርቅ የተሸፈነ የደረቀ አጽም ማግኘታቸውን አርኪዎሎጂስቶች አስታወቁ።
አርኪዎሎጂስቶች በወርቅ ተለብጦ የደረቀ አጽም በድንጋይ መቃብር ውስጥ ማግኘታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
የደረቀው አጽም ሔካሼፕስ የተባለ ግለሰብ ነው የተባለ ሲሆን፣ ከንጉሣውያን ዘር ያልሆነ እና ይህም ዕድሜ ጠገብ ሙሉ አካሉ ሳይፈራርስ የተገኘ ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ሌሎች የደረቁ አጽሞች የተገኙበት ምዕራብ ካይሮ በሚገኝ ሳቅራ፣ በተባለ የመቃብር ስፍራ የተገኘው ይህ አስከሬን፣ ከጎኑ ሌሎች ሦስት መቃብሮች ነበሩ።
ይህ 15 ሜትር ወደታች ባለስፍራ ከተገኘው አጽም ጎን የተገኘው አንደኛው መቃብር “ለምስጢራዊው ጠባቂ” የተዘጋጀ ነበር።
በጥንታዊቷ ኔክሮፖሊስ የተገኙት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደረቁ አጽሞች የክሁኑምድጄዴፍ ነው ተብሏል።
እነዚህ አጽሞች ቄስ፣ ፖሊስ እና የባለጠጎች ተቆጣጣሪ መሆናቸው ይታመናል።
ሌላው ሜሪ የተባለ ግለሰብ እና ከፍተኛ የቤተመንግሥት ኃላፊ “ምስጢራዊው ጠባቂ” የሚል ማዕረግ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም የተለየ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን እንዲፈጽም ያደርገዋል ተብሏል።
በሌላኛው መቃብር ደግሞ ዳኛ እና ደራሲ የሆነው ፌቴክ እንደተቀበረ ይታመናል።
በእነዚህ መቃብሮች ከውስጥም ፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቅርጻ ቅርጾች መገኘታቸው ተጨምሮ ተገልጿል።
ከመቃብሮቹ በተጨማሪ የተለያዩ የሸክላ ሥራ ውጤቶች ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግብፅ የጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስትር የነበሩት ዛሂ ሐዋስ፣ ሁሉም የተገኙት የደረቁ አጽሞች እና ሌሎች ቅርሳ ቅርሶች እድሜያቸው ከክርስቶስ ልደት በፊት 25ኛው እስከ 22ኛው ምዕተ ዓለም ይገመታል ብለዋል።
“ግኝቶቹ ንጉሦችን ከሕዝቡ በማገናኘት ረገድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ናቸው” ያሉት ደግሞ በቁፋሮው ላይ የተሳተፉት ሌላው አርኪዎሎጂስት አሊ አቡ ዴሺሽ ናቸው።
ሳቅራ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የተመዘገበ እና ለ3000 ዓመት የቀብር ስፍራ በመሆን ያገለገለ ነው።
ይሀ ስፍራ ጥንታዊዋ ግብፅጽ ዋና ከተማ ሜምፊስ መገኛ፣ እንዲሁም በርካታ የደረቁ አጽሞች የተገኘበትን ጨምሮ የሌሎች ፒራሚዶችንም የያዘ ነው።
ሐሙስ ዕለት ይፋ የተደረገው ይህ ግኝት፣ በምዕራብ ግብፅ በምትገኘው ሉክሶር ከተማ፣ በሮማውያን ዘመን (ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ2ኛው እና 3ኛው ምዕተ ዓመት) መኖሪያ የነበረች ከተማን ማግኘታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
አርኪዎሎጂስቶች የመኖርያ ሕንጻዎች፣ ማማዎች እና “የብረታ ብረት መሥሪያ ቦታዎች” ሲሉ የገለፁትን ስፈራ ማግኘታቸውንም ይፋ አድርገዋል።
የግብፅ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ ቅርሶች ጥናት ተመራማሪዎች በዚህ ስፍራ ማሰሮ፣ የሮማውያን ሳንቲሞች እና ሌሎች መሳርያዎችን አግኝተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግብፅ በርካታ ጥንታዊ ቅርሶችን በቁፋሮ እያገኘች ሲሆን፣ ይህም የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ እንዲነቃቃ ያደርገዋል ተብሏል።












