ንግሥት ኤልዛቤጥን ለመሰናበት ከ20 ሺ በላይ ሰዎች ተሰልፈዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩናይትድ ኪንግደም ንግሥት የነበሩት ንግሥት ኤልዛቤጥን ለመሰናበት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች 1.6 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሰልፍ ይዘው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ሐዘንተኞች ሰኞ ዕለት ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ነበር የንግሥቲቱ አስከሬን ወደሚገኝበት ካቴድራል መጓዝ የጀመሩት።
የሳልቬሽን አርሚ ቤተክርስቲያን መኪኖች ምሽቱን በሰልፍ ለሚያሳልፉት ሐዘንተኞች ትኩስ መጠጦች እና ፈጣን ምግቦችን ሲያቀርቡም ታይተዋል።
እንዲሁም ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤቶች እና የመጠጥ ውሃ የሚገኝባቸው ቦታዎች በወረፋው ላይ ለሚቆዩ ሰዎች ተዘጋጅቷል።
መንገደኞች ለሰዓታት ወረፋ የሚጠብቁትን ሐዘንተኞች በመመልከት ድንጋጤያቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
ነገር ግን ሰልፈኞቹ በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ የመሳተፍ እና ለንግሥቲቱ ክብር የመስጠትን አስፈላጊነት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል ኡጋንዳዊቷ ኤልዛቤጥ ትገኝበታለች። ኑሮዋን በግላስጎው ያደረገችው ኤልዛቤጥ ከሁለት ልጆቿ ጋር ረጅሙን ሰልፍ ተያይዛዋለች።
ልጇ ዳንኤል ክብረ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት የሚለበስ ልብሱን ለብሶ ነው የንግሥቲቷን የአስከሬን ሳጥን ለመመልከት የመጣው።
“እናቴ የተወለደችው ንግሥቲቱ በተወለደችበት ዓመት ሲሆን እኔንም ኤልዛቤጥ ያለችኝ ንግሥቲቷን ስለምትወዳት ነው’’ ስትል ኡጋንዳዊቷ ኤልዛቤጥ ተናግራለች።
“አሁን 96 ዓመቷ ነው፤ ቅዳሜ ዕለት ክብር ለመስጠት ወደ ባልሞራል ተጉዛለች’’ ስትልም ተናግራለች።
“በልጅነታችን የንጉሣዊው ቤተሰብ በጣም ትልቅ አድናቂዎች ነበርን ... ዛሬ እዚህ መምጣት እና የታሪካዊው ወቅት አካል መሆን እንፈልጋለን’’ ስትል ተናግራለች።
ከምሥራቃዊ ሊተን የመጡት ካሎም እና አኔት ኪንግ በበኩላቸው ንግሥቲቷን ለመሰናበት ወረፋ በመጠባበቃቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የ54 ዓመቱ ካሉም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የሚያካሂደውን ስልጠና ቅዳሜ እና እሁድ በማጠናቀቅ ከኖቲንግሃም ተጉዞ ነው ንግሥቲቷን ለመሰናበት የመጣው።
“የዛሬ 34 ዓመት ገደማ ለንግስቲቷ ታማኝ ለመሆን ቃለ መሃላ ፈጽሜ ነበር። ስለዚህ አሁን የመጨረሻ ሰላምታዬን ባቀርብላቸው ትክክል ብቻ ነው የምሆነው’’ ብሏል።
“ንግስቲቷን ለመመልከት ጠዋት 10 ወይም 11 ሰአት ላይወረፋ እንደሚደርሰን አንድ ሰው ነግሮናል። ከዚህ እንደጨረስን ወደ ቤት እንሄዳለን:: ነገ ጠዋት 2፡30 ላይ ሥራ ገባለሁ’’ ሲሉ ም አክለዋል።
የሬሳ ሳጥኑን ለመመልከት የቻሉት ሃዘንተኞች ወደ ካቴድራሉ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስለነበራቸው "ስሜታዊ" ግዜ ለቢቢሲ ስኮትላንድ ተናግረዋል።
እስከ ማክሰኞ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ንግሥቲቱን መሰናበት ይችላሉ።












