የንግሥቲቷን ሞት ተከትሎ አንቲጓ ሪፓብሊክ ለመሆን ሕዝበ ውሳኔ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው አንቲጓ እና ባርቡዳ የንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ ሞትን ተከትሎ ሪፓብሊክ ለመሆን ሕዝበ ውሳኔ ልታካሂድ ነው።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጋስቶን ብራዎን ሕዝበ ውሳኔው ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደሚከናወን ገልጸው፤ ሕዝበ ውሳኔ የማካሄድ እቅዱ “የጠላትን ድርጊት አይደለም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራቸው ሪፓብሊክ ብትሆን “ነጻ እና ሉዓላዊ” መሆናችንን የምናገረጋግጥበት የመጨረሻው እርምጃ ይሆናል ብለዋል።
ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የአንቲጓ እና ባርባዱ ርዕሰ ብሔር ነበሩ።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አንቲጓ ሕዝበ ውሳኔ እንደምታደርግ የተናገሩት ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ የካሪቢያኗ አገር አንቲጓ እና ባርባዱ ርዕሰ ብሔር መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው።
ጋስቶን ብራዎን በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ካሸነፉ ሕዝበ ውሳኔውን እንደሚያስፈጽሙ ገልጸዋል።
ንግስት ኤልዛቤጥ ከካረቢያኗ አገር በተጨማሪ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ኒው ዚላንድን ጨምሮ የበርካታ የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ርዕሰ ብሔር ናቸው።
የንግስቲቱ ሞት በአውስትራሊያ ሪፓብሊክ የመሆን እንቅስቃሴን ዳግም አጋግሎታል።
በአሁኑ ወቅት ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ከዩናይትድ ኪንግደም በተጨማሪ የ14 አገራት ርዕሰ ብሔር ናቸው። እነዚህም አንቲጓ እና ባርባዱ፣ አውስትራሊያ፣ ባህማስ፣ ቤሊዝ፣ ካናዳ፣ ግሬናዳ፣ ጀማይካ፣ ኒው ዚላንድ፣ ፓፐዋ ኒው ጊኒ፣ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ፣ ሴንት ሉሺያ እና ዘ ግሬናዲኢስ፣ ሰለሞን ደሴቶች እና ቱቫሉ ናቸው።
ከአንድ ዓመት በፊት ባርባዶስ ንግስት ኤልዛቤጥን ከርዕሰ ብሔርነት አንስታ ተመራጭ ፕሬዝዳንቷን ርዕሰ ብሔር በማድረግ ሪፓብሊክ መሆኗን አውጃ ነበር።
ሌላኛዋ የካረቢያን አገር ጀማይካ ገዢ የሠራተኞች ፓርቲ ሕዝበ ውሳኔ አካሂዶ ሪፓብሊክ መሆኑን ለማወጅ ማቀዱን አስታውቋል።












