ንጉሥ ቻርለስ የንግሥቲቷን የአገዛዝ ዘመን አወደሱ

ንጉስ ቻርለስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻርለስ ሳልሳዊ በሴንት ጄምስ ቤተ መንግሥት በተካሄደው የሲመት ስነ ስርዓት ንጉሥ መሆናቸው ከታወጀ በኋላ የንግሥቲቱን “አቻ የለሽ አገዛዝ” አወደሱ።

ንጉሥ ቻርለስ እናታቸው ካረፉ በኋላ ንግሥናቸው ቢታወቅም ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት ጳጉሜ 5፣ 2014 ዓ.ም በነበረ ስነ ስርዓት በይፋ ንጉስ ተብለዋል።

ሐሙስ ዕለት ህይወታቸው ያለፈው የንግሥት ኤልዛቤጥ ቀብር መስከረም 2፣ 2015 ዓ.ም እንዲሆንና ይህችም ዕለት ብሔራዊ በዓል እንድትሆን ተወስኗል።

 የንጉሣውያንን የስልጣን መተካካት ለሚከታተለው ምክር ቤት ባደረጉትም ንግግር ንጉሡ የእናታቸውን ሞት “ የማይጠገን ኃዘን” ብለውታል።

በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን ጨምሮ የኮመን ሃውስ ከፍተኛ የፓርላማ አባላት ለአዲሱ ንጉስ ቻርለስ ታማኝነታቸውን ገልጸዋል።

ንጉሥ ቻርለስ በለንደን በሚገኘው የቅዱስ ጄምስ ቤተ መንግሥት ባደረጉት ንግግር “በርካቶች ለእህቶቼ፣ ለወንድሞቼ ሃዘኔታቸውን መግለፃቸው እንዲሁም ከፍተኛ ፍቅር ማሳየታቸው ለእኔ ትልቁ መጽናኛ ነው። ለመላው ቤተሰባችንም ፍቅር እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።

ንጉስ ቻርለስ አክለውም ንግሥቲቱ ራሳቸውን ለአገልግሎት መስጠታቸውን በማስመልከትም “የእናቴ የግዛት ዘመን በቆይታው፣ በፅናት፣ በትጋት፣ እና በታማኝነት ተወዳዳሪ አልነበረውም” ብለዋል።

“በሃዘን ላይ ባለንበት ወቅት እንኳን ለዚህ ታማኝነት እናመሰግናለን” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ንጉሡ አክለውም ሉዓላዊነትን በተመለከተ ከባድ ኃላፊነቶች ተሸክመው የነበሩት እናታቸው የተውላቸውን አበረታች ምሳሌም ለመከተል ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። 

ንግሥናቸው ፖለቲከኞች፣ ዳኞች እና ባለሥልጣናትን ባካተተው የአክሰሺን ምክር ቤት ሲታወጅ ንጉሱ በስብሰሰባው የመጀመሪያ ክፍል አልነበሩም። 

ፕራይቪ የተሰኘው የንግሥቲቷ ምክር ቤት ጸሐፊ የሆኑት ሪቻርድ ቲልብሩክ ቻርለስን “ንጉሥ፣ የኮመንዌልዝ ዋና ኃላፊ፣ የእምነት ጠበቃ” በማለት ከጠሯቸው በኋላ” አምላክ ንጉሡን ይጠብቅ” ሲሉም አጠቃለዋል።

በዚህ ጉባዔ ላይ ስድስቱ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን የተገኙ ሲሆን ይህንን ሃረግም ደግመው ተናግረዋል።

ከዚያም አዋጁ በቅዱስ ጄምስ ቤተመንግሥት በሚገኘው ፍሪሪ ፍርድ ቤት በላይ ባለው በረንዳ ላይ ተነቧል። 

የንጉሣውያን ቤተሰብ የዘር ግንድ