ንግሥቲቱ እና አፍሪካ: ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት

ንግሥት ኤልዛቤጥና የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ንግሥት ኤልዛቤጥና የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ

የያኔዋ ልዕልት ኤልዛቤጥ በኬንያ ገጠራማ ሥፍራ በሚገኘውና በአረንጓዴ ተክሎች፣ በረጃጅም ዛፎች እና በዱር አራዊት በተከበበው ትሬቶፕስ ሆቴል ሲደርሱ አባታቸው ንጉስ ጆርጅ ስድስተኛ አረፉ።በዚያም በ25 ዓመታቸው የንግሥትነት ሥፍራውን ያዙ።

ንግሥት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ በሰባ ዓመት የንግሥና ዘመናቸው ከ20 በላይ የአፍሪካ አገሮችን ጎብኝተዋል።

በአንድ ወቅት ለቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ከማንኛውም ሰው በላይ የአፍሪካ አገራትን ጎብኝቻለሁ በማለት በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችን ፈገግ አሰኝተው ነበር።

ንግሥት ሲሆኑም በርካታ አገራትን ያካተተ የአፍሪካ አህጉርን በግዛትነት ጠቅልለው ወርሰው ነበር።

በግዛት ዘመናቸውም በአውሮፓውያኑ 1957 ነጻነቷን ካገኘችው ጋና ጀምሮ 14ቱም የአፍሪካ አገራት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ነጻነታቸውን አግኝተዋል።

ንግሥቲቷ ነፃነታቸውን ካገኙ አገራትም ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነትን መፍጠር ችለዋል፤ ይህን ማድረግ የቻሉትም በከፊል የብሪታንያ ግዛት ተተኪ የሆነውን የኮመንዌልዝ ድርጅትን በመመስረት ነው።

በአውሮፓውያኑ 1961 ጋና ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ እንድትሆን ከመሩት እና የመጀመሪያዋ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ጋር ሲደንሱም ታይተዋል።

በተለይም ኢምፓየር (ግዛት) የሚለው ቃል በአውሮፓውያኑ 1953 በነበረው የንግሥና በዓለ ሲመትና መሃላ ወቅት እንዲቀር ተደርጓል።

ንግሥቲቱ ማረፋቸውን ተከትሎ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ መሪዎች ብሪታንያ እና ኮመንዌልዝን ለረጅም ዓመታት በንግሥና ለመሩትን ንግሥት ኤልዛቤጥ ሃዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ንግሥናቸው የተጀመረበት ኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “ከራስ ባለፈ ለሰው ልጅ የሚያገለግሉ ትልቅ ተምሳሌት የሆኑና እና የዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ሳይሆን ኬንያ የተከበረች አባል የሆነችበት የኮመንዌልዝ ኅብረት ቁልፍ መሪ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ንግሥት ኤልዛቤጥና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዚምባብዌ እና የዩናይትድ ኪንግደም ግንኙነት ለረጅም ዓመታት ሻክሮ የቆየ ሲሆን ሟቹ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አገራቸው ከኮመንዌልዝ ኅብረት አባልነት ለቃ እንድትወጣ አድርገዋል።

ሆኖም ተተኪያቸው ኤመርሰን ምናንጋግዋ “የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለንጉሳዊው ቤተሰብ፣ ለዩናይትድ ኪንግደም እና ኮመንዌልዝ” በትዊተር ገጻቸው በፍጥነት ገልጸዋል።

በአፍሪካ ትልቋ ግዛት የነበረችው ናይጄሪያ መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ በበኩላቸው፣ ረዘም ያለ የሀዘን መግለጫ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩ ሲሆን “ከፍተኛ ሃዘንም ተሰምቶኛል” ብለዋል።

"የዘመናዊቷ ናይጄሪያ የታሪክ ምዕራፍ፣ ዓለም አቀፋዊ ስብዕና እና የላቀ መሪ ከሆኑት ያለ ንግሥት ኤልዛቤጥ ሙሉ አይሆንም። ሕይወታቸውን ለሕዝባቸው፣ ለኮመንዌልዝ እንዲሁም መላው ዓለምን የተሻለ ቦታ ለማድረግ ሰጥተዋል” ብለዋል።

የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቻርለስ ሳልሳዊ ወደ ዙፋኑ መምጣታቸውንም ፕሬዚዳንቱ በደስታ ተቀብለውታል።

አዲሷ የኮመንዌልዝ አባል የሆነችውና የፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛት የነበረችው ጋቦን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎም ሀዘናቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የአህጉሪቱ መሪዎች የሀዘን መግለጫቸውን ቢያስተላልፉም ሌሎች አፍሪካውያን በበኩላቸው በብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ወቅት የደረሰባቸውን ስቃይና በደል እየተናገሩ ሲሆን፣ ይህም በንጉሳዊ ቤተሰቦች ስም ተፈጽሟል እያሉ ነው።

አንዳንድ የአፍሪካ ንጉሶችና ቤተሰቦችም ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ልዑል ማንጎሱቱ ቡተሌዚ፣ በደቡብ አፍሪካ ዙሉ ሕዝብ መሪ ንጉስ ሚሱዙሉ ካዝዌሊቲኒ ስም ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

ከንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ጋር ያላቸውን ወዳጅነትም በመጥቀስ ለእርሳቸውም በግላቸው የሀዘን መግለጫ ልከዋል።

ንጉሥ ሚሱዙሊ፣ አባታቸው ዝዌሊቲኒ ከ50 ዓመታት ንግሥና በኋላ በቅርብ ጊዜ ያረፉ ሲሆን የንጉሥ ቻርለስንም ሁኔታ በቅርበት ይረዳሉ።

ንግሥቲቱ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው።

በአውሮፓውያኑ 1947 የ21ኛ ዓመት ልደታቸውን ያከበሩት በደቡብ አፍሪካ በጉብኝት ላይ ነበር። በኬፕታውን በሬድዮ ላይ በሰጡት መግለጫ ሕይወታቸውን ለኮመንዌልዝ ኅብረት እንደሰጡና ደቡብ አፍሪካም ሙሉ ሕይወታቸውን የኖሩበትን ያህል “በአገሬ ያለሁ ያህል ይሰማኛል” ብለዋል።

የፖለቲካ አቋማቸውን በማንጸባረቅ የማይታወቁት ንግሥት ኤልዛቤጥ ለአስርት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የነጮች ጥቂቶች አገዛዝ ካበቃ ከአንድ ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1995 ደቡብ አፍሪካን ሲጎበኙ ጠንከር ያለ ንግግር አድርገዋል።

“የእርቅ መንፈሱ ለዓለም ተምሳሌት የሆነ የሕዝብን አንድነት አምጥቷል። እኔም ተመልሼ መጥቼ ይህንን ተአምር ለመመልከት ችያለሁ” በማለት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ንግሥቲቱ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር መልካም ግንኙነት ነበራቸው። የንግሥቲቱን ማረፍ ተከትሎ የኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን፣ “[ ከኔልሰን ማንዴላ] ጋር በተደጋጋሚ በስልክ ያወሩ ነበር። ያለ ቅጥያ ክብር ስም በመጀመሪያ ስማቸው ነበር የሚጠራሩት ይህም የመከባበር እና የመውደድ ምልክት ነው” በማለት መግለጫ አውጥቷል።

መግለጫው አክሎም ማንዴላ ለንግሥቲቷ ልዩ ስም ነበራቸው “ሞትላሌፑላ፣ የሚል ሲሆን ትርጉሙም ከዝናብ ጋር መምጣት ማለት ነው” ለዚህም በአውሮፓውያኑ 1995 ሲመጡ ዝናብ ከመዝነቡ ጋር በመገጣጠሙ ነው።

ንግሥት ኤልዛቤጥ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images