የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ቀብር እና የሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶች

የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ ሕልፈተ ሕይወት በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ ረዥሙ የንግሥና ዘመን እንዲያበቃ አድርጓል።
ንግሥቲቱ ሐሙስ ጳጉሜ 03/2014 ዓ.ም. በቤተሰብ አባሎቻቸው ተከብበው ስኮትላንድ በሚገኘው ባልሞር ቤተ-መንግሥት ውስጥ ነበር በሰላም ያረፉት።
የአገሪቱ ዜጎች ለንግሥቲቱ ያላቸውን ክብር ባለፉት ቀናት እየገለጹ የቆዩ ሲሆን ዛሬ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ይፈጸማል።
የንግሥቲቱ ህልፈት ይፋ ከተደረገ በኋላ አስከ ዛሬ ድረስ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
አስክሬናቸው ከስኮትላንድ ወደ ለንደን ከመጣ በኋላ ቀድሞ ያረፈው በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አስክሬኑ ከይፋዊ መኖሪያ ቤታቸው ዝግ ባለ ፍጥነት በቤተሰብ አባላት እና በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ ወደ ዌስትሚንስተር አዳራሽ ተወስዷል።
ሥርዓተ ቀብር ከመፈጸሙ በፊት ለአራት ቀናት በዌስትሚኒስቴር አዳራሽ ቆይቷል።
በእነዚህ ቀናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ረጅም ሰልፍ ይዘው በየተራ አስክሬኑን በክብር ተሰናብተዋል።
ከብሪታኒያ መንግሥት መቀመጫ አካባቢ የሚገኘው ዌስትሚኒስተር ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘው አዳራሽ ከህንጻው ጥንታዊ ክፍሎች አንዱ ነው።
ከዚህ ቀደም እአአ 2002 በዚህ ስፍራ ቀብራቸው የተፈጸመው የኤልዛቤጥ እናት ነበሩ። የኤልዛቤጥ እናት አስክሬንን ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ በአካል ተገኝተው ተሰናብተዋል።

የአስክሬን ሳጥኑ ዘውዱን እና ዩናይትድ ኪንግደምን በሚወክለው ‘ሮያል ስታንዳርድ’ ሰንደቅ አላማ ይሸፈናል። አስክሬኑ ዌስትሚኒስቴር አዳራሽ ከደረሰ በኋላ ደግሞ ዝውዱ የአስክሬን ሳጥን ላይ ይቀመጣል።
የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዌስትሚንስትር አቤይ ዛሬ ይፈጸማል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቤይ በብሪታኒያ ነገሥታት ታሪክ ውስጥ በርካታ ታሪክዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ቤተ መቅደስ ነው።
እአአ 1953 ላይ የኤልዛቤጥ የንግሥና ሥነ ሥርዓታቸው የተከናወነ ሲሆን፣ የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውም የተፈጸመው በዚሁ ቤተ መቅደስ ነው።

ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በአቤይ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሳይካሄድ ቆይቶ የኤልዛቤጥ እናት የቀብር ሥነ ሥርዓት እአአ 2002 ተከናውኖበታል።
በዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም የበርካታ አገራት መሪዎች ወደ ለንደን ተጉዘው ከንጉሣውያን ቤተሰብ ጎን ይቆማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዕለት አስክሬኑን ከዌስትሚኒስተር አዳራሽ ወደ ዌስትሚኒስቴር አቤይ በሰረገላ ማጓጓዝ ይጀምራል።
ከአስክሬኑ ጀርባ ንጉሥ ቻርልስ ሦስተኛን ጨምሮ በርካታ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት ይከተላሉ።
ሥነ ሥርዓቱን የሚመሩት የዌስትሚኒስትር ካህን ዴቪድ ሆይል ከካንትበሪው አርክቢሾፕ ጀስቲን ዌብሊ ጋር በመሆን ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ጥቅስ እንዲያነቡ ሊጠየቁ ይችላሉ።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ዕለት ከሰዓት በኋላ የንግሥቲቱን አስክሬን የያዘው የሬሳ ሳጥን በዊንዘር ቤተ መንግሥት ውስጥ ወደሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-መቅደስ ያቀናል።
የአስክሬን ሳጥኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ መታሰቢያ ቤተ መቅደስ ይገባል።












