ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ የመጀመሪያውን ንግግር አደረጉ

የእናታቸውን ሞት ተከትሎ የንግሥና መንበሩን የተረከቡ ንጉሥ ቻርለስ በመጀመሪያው ንግግራቸው “በአግባቡ የተኖረ ሕይወት” ሲሉ “ተወዳጇን እናታቸውን” አሞካሽተው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
ስሜታዊነት በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ንግግራቸው ንጉሡ፣ የንግሥት ኤልዛቤጥ እንክብካቤን፣ ቀልድን እና በሰዎች ውስጥ ያሉ መልካም ነገሮችን የመመልከት ብቃታቸውን አድንቀዋል።
ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ፣ ዊሊያም እና ካትሪን የዌልስ ልዑልና ልዕልት እንደሚሆኑ ተናግረው፣ ለልዑል ሄሪ እና ለባለቤቱ ሜጋን ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።
ንግሥት ኤልዛቤጥ ሐሙስ ዕለት ስኮትላንድ ባልሞር ውስጥ ነበር ያረፉት።
የንጉሡ ንግግር የተላለፈውም ቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል ውስጥ ለንግሥቲቱ የተሰናዳው መታሰቢያ በሚካሄድበት ወቅት ነበር።
የ73 ዓመቱ ንጉሥ በንግግራቸው የንግሥቲቱ “በተለያዩ ለውጦች ውስጥ፣ በደስታ እና በመልካም ጊዜ፣ እንዲሁም በመጎዳት እና በሐዘን ወቅት ሁሉ፤ ለኃላፊነታቸው የማይናወጥ መሰጠት ነበራቸው” ብለዋል።
ንጉሡ፣ ልጃቸው የሆነውን ዊሊያም የዌልስ ልዑል ባለቤቱን ካትሪንን ደግሞ የዌልስ ልዕልት አድርገው መሰየማቸውን ይፋ አድርገዋል።
ጨምረውም “በባሕር ማዶ ሕይወታቸውን መምራት ለመረጡት ለሄሪ እና ሜጋን” ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።
ንግሥት ስለሆኑት ለ17 ዓመታት በትዳር ስለተጣመሯቸው የ75 ዓመቷ ካሚላም “ለሚጠበቅባት አዲስ ኃላፊነት በጽኑ እንደምትቆም እና ለእኔም ድጋፍ እንደምትሆነኝ አውቃለሁ” ብለዋል።
ንጉሡ ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ሕይወታቸው መለወጡንም አመልክተዋል።
“ለበጎ አድራጎትና ለሌሎች ጉዳዮች ከዚህ በፊት ሳደርገው እንደነበረው አብዛኛውን ጊዜዬን እና ጉልበቴን መስጠቴ ያበቃል፤ ነገር ግን እነዚህ አስፈላጊ ተግባራት በሌሎች አስተማማኝ ሰዎች እንደሚከወኑ አውቃለሁ” ብለዋል ንጉስ ቻርለስ።
የዙፋናቸው አልጋ ወራሽ ልዑል ዊሊያም፣ የንጉሥ ቻርለስ የቀድሞ የስኮትላንድ ማዕረግ እና ኃላፊነት የሆነውን የኮርንዌል አልጋ ወራሽነትን ይረከባሉ።
“አዲሱ የዌልስ ልዑል ካትሪንን ከጎኑ አድርጎ፣ የሚጠበቅበትን ኃላፊነቶች ሁሉ ያከናውናል። የሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ ይደረግለታል” ብለዋል ንጉሡ።
ስለእናታቸውም “ለቤተሰባችን ለነበረሽ ፍቅር እና ላደረግሽው ነገር ሁሉ እንዲሁም ለዘመናት በትጋት ላገለገልሻቸው ሕዝቦች አመሰግንሻለሁ” ብለዋል።
ንጉሥ ቻርለስ የንግሥና መንበሩን እንደተረከቡ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው የሆነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ጋር ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ውስጥ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
አርብ ዕለት በዌስትሚኒስቴር ውስጥ በተካሄደው ንግሥቲቱን የማሰብ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የፓርላማ አባላት እና ባለሥልጣናት ተገኝተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትረስ ንግሥቲቱን “ዓለማችን እስካሁን ካየቻቸው ታላላቅ መሪዎች አንዷ ነበሩ” ብለዋቸዋል።
የንጉሡ ቤተ መንግሥት በቀጣይ ቀናት ስለሚከናወኑ ነገሮች ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።
እስካሁን የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት መቼ እንደሚፈጸም የተቆረጠ ቀን ባይኖርም በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በፊት የንግሥቲቱ አስከሬን ኤደንብራ ውስጥ ከቆየ በኋላ ወደ ለንደን ይወሰዳል።
ለንደን ውስጥ በሚገኘው የዌስትሚኒስቴር አዳራሽ አስከሬኑ ለሕዝብ ክፍት ተደርጎ በአጠገቡ እያለፉ አክብሮታቸውን በመግለጽ እንዲሰናበቱ ይደረጋል።












