የዩክሬን ግድብ መመታቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ

ተፈናቃዮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩክሬኑ ግድብ በሩሲያ ድብደባ መፍረሱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጎርፍ በመሸሽ ለቀው እየወጡ ነው።

ግድቡ የተሠራበት ወንዝ የሚያስከትለውን ጎርፍ በመፍራት በተፋሰሱ የታችኛው ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ወጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እንዳሉት 80 መንደሮችና ሰፈሮች በጎርፍ ሊጥለቀለቁ ይችላሉ።

ኖቫ ካኮቫካ የተባለው ግድብ የተመታው በሩሲያ መሆኑ ተገልጿል።

ሩሲያ ግድቡን እንዳላፈረሰች ነው የተናገረችው።

ቢቢሲ በሩሲያም ይሁን ዩክሬን የተባለውን ማጣራት አልቻለም።

ድናፕሮ የተባለው ወንዝ ከፍተኛ ጎርፍ እንደሚያስከትል ተገልጿል።

ይህ ግድብ ለቀጠናው ጠቀሜታው የጎላ ነበር። ለአርሶ አደሮች የውሃ ምንጭ ከመሆኑ በተጨማሪ ኃይል ማመንጫም ነበር።

በሩሲያ ወደተያዘቸው ክሬሚያ ውሃ የሚሄደው በዚህ በኩል ነው።

ወንዙ መፍሰስ ከጀመረ በኋላ ከአራት እስከ አምስት ቀናት ሊቀጥል እንደሚችል ተጠቁሟል።

በአውሮፓ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የሆነው ዛፖሪዚሀ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ይህንን ውሃ በመጠቀም ነው የሚቀዘቅዘው።

ለጊዜው ግን የኒውክሌር ኃይሉ ላይ ስጋት እንዳልተጋረጠ ዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቋም ተናግሯል።

ብዙ ከተሞች ከአሁኑ በጎርፍ እየተሞሉ ሲሆን በአውቶብስና በባቡር አካባቢውን ትተው የወጡ ነዋሪዎች ተስተውለዋል።

ምክትል ዐቃቤ ሕግ ቪክቶሪያ ሊትቪኖቫ ወደ 40 ሺህ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል። 17 ሺህ የሚሆኑት በዩክሬን ይዞታ ሥር ባለው አካባቢ 25 ሺህ ደግሞ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኘው አካባቢ ይፈናቀላሉ።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ኢሆር ክሊሜንኮ 24 ይዞታዎች ጎርፍ ገብቶባቸው 1,000 ሰዎች እንዲወጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የውሃ መጠን በመጨመሩ የማዕድን አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስም ተሰግቷል።

ግድቡ አቅራቢያ የሚኖው አንድሪ “ሩሲያ አገሬን ልታሰጥም ፈልጋለች” ብሏል።

በኼርሶን የምትኖረው ሉድሚያ “ጎርፍ እንዳይወስደን ፈርተናል” ብላለች።

“ሩሲያውያን ከዚህ መውጣት አለባቸው። ይተኩሱብናል። አሁን ደግሞ በውሃ ሊያሰጥሙን ነው” ስትልም አክላለች።

ሌላ ሸርሊ የተባለ የከተማው ነዋሪ “ሁሉንም ነገር ነው የምናጣው። ሕይወት ያለው ሁሉ ይጠፋል” ብሏል።

በሩሲያ ሥልጣን የተሰጣቸው የአካባቢው ከንቲባ ቭላድሚር ሌንቴቭ ከተማው በውሃ እንደተጥለቀለቀና 900 ሰዎች እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ውሃው እስከ 11 ሜትር ወደላይ ወጥቷል።

ካዝኮቫ ዲብሮቫ የእንስሳት ማቆያ በውሃ ተሞልቶ 300 እንስሳት ሞተዋል።

ግድብ

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES/REUTERS

ግድቡ በምን ምክንያት እንደፈረሰ ግልጽ ባይሆንም ዩክሬን ሩሲያን ከሳለች።

ግድቡን በመጠቀም የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ወደተያዙ አካባቢዎች ይጓዛሉ በሚል ስጋት ሩሲያ በግድቡ ጥቃት አድርሳ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።

ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እርምጃዋ ስኬታማ አለመሆኑን ለመሸፈን ግድቡን መትታ ሊሆን እንደሚችል ትከሳለች።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ግድቡ የደረሰበት ጉዳት ዩክሬንን እንደማያስቆም ገልጸው “አሁንም አገራችንን ነጻ እናወጣለን” ብለዋል።

የዩክሬን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሀና ማሊር የዩክሬን ወታደሮች በባኽሙት እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ባኽሙት ባለፉት ወራት ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዶባታል።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ኃላፊ ጄንስ ስቶልትበርግ፣ ግድቡ ላይ የደረሰው ጥቃት ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ያሳየችው “ጭካኔ ማሳያ ነው” ብለዋል።