መንግሥት የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ እምነት የሚጣልበት አይደለም አለ

Gov't Comm

የፎቶው ባለመብት, Gov't Comm

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች ምዕራብ ትግራይን በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ እምነት የሚጣልበት አይደለም አለ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዛሬ ግንቦት 29/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ምዕራብ ትግራይን የተመለከተው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት “ተገቢው ምርመራ ያልተደረገበት እና በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ከመሆኑ አንጻር እምነት የሚጣልበት አይደለም” በማለት ሪፖርቱን “መሠረተ ቢስ” ሲል አጣጥሎታል።

ከቀናት በፊት ማለትም ግንቦት 24/2015 ዓ.ም. ሂዩማን ራይትስ ዋች የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በምዕራብ ትግራይ የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመ ነው ብሎ ነበር።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ የአማራ ኃይሎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመተባበር የትግራይ ተወላጆችን በኃይል ከምዕራብ ትግራይ እንዲለቁ እያደረጉ ነው ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አደረኩት ባለው ጥናት ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ድርጊት ተጠያቂ የተደረጉት ግለሰቦችን በስም በመጥቀስ አሁንም እኚህ ግለሰቦች ሰዎችን ከሕግ ውጭ በማሰር፣ በማሰቃየት እና የትግራይ ተወላጆችን በኃይል በማፈናቀል ተግባር ተሰማርተዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለዚህ ሪፖርት በሰጠው ምላሽ ላይ የመብት ተሟጋቹ ያቀረበው ሪፖርት “የተዛባ እና በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማይገልጽ” ነው ብlኦታል።

ጨምሮም ሪፖርቱ “ለዘመናት አብረው የቆዩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠለሽ፣ በሕዝቦች መካከል ግጭት ቀስቃሽ የሆነ እና አገራችን እያደረገች ያለውን የእርቅ እና ምክክር ሂደት የሚያደናቅፍ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል።

ጽ/ቤቱ በመግለጫው መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሞ ስለማይታገስ በሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ እንዲደረገ ገለልተኛ የሆኑት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የምርመራ ቡድን እንዲያጣሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን እንዲሁም ሪፖርቱም ሲወጣም የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን ለመተግበር እንቅስቃሴ ማድረጉን ገልጿል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርቱን ያወጣው ከመስከረም 2015 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ባሉት ወራት 35 የዐይን እማኞችን፣ ተጎጂዎችን እና የእርዳታ ሰጪ ድርጅት ሠራተኞችን ጨምሮ 35 ሰዎችን በስልክ ካነጋገረ በኋላ መሆኑን ገልጿል።

ለመብት ተሟጋቹ በስልክ ቃላቸውን የሰጡ ሰዎች የአማራ ኃይሎች እና የአካባቢው አስተዳደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በኃይል ከአካባቢው ከማፈናቃላቸው በፊት በሁመራ፣ ራዊያን እና አደባይ ከተሞች አስረው አቆይተዋቸው እንደነበረ ገልጸዋል።

የዐይን እማኞች እና ተጎጂዎች ሰዎች ይፋዊ ባልሆኑ ቦታዎች ጭምር ያለ በቂ ምግብ እና መድኃኒት ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ግን የመብት ተሟጋቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረትን ከግምት ሳያስገባ እና በቂ ማስረጃ በሌለበት የወጣው ሪፖርት ገንቢ ያልሆነ እና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።