‘የፀጥታ ኃይሎች አስረው ገንዘብ እየተቀበሉ እያንገላቱን ነው’ - የሸገር ከተማ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሸገር ከተማ ቀድሞ በኦሮምያ የአዲስ አበባ ዙርያ ልዩ ዞን ተብሎ በሚጠሩ የነበሩ ዞኖችን አንድ ላይ በማዋሀድ ከወራት በፊት የተቋቋመ ከተማ ነው።
ከተማው ክፍለ ከተማዎች እና ወረዳዎችን በማዋቀር ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ውስጥ በማድረግ ሥራ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ይሁን እንጂ ዝርፍያ፣ ዛቻ እና ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰውን ማሰር የተለመደ ሆኗል ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች።
ጉዳዩን ለየት የሚያደርገው “የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ፖሊስ፣ ሚሊሻ ወንጀል መርማሪዎች እና የደኅንነት ሰዎች እየተፈጸመ መሆኑ ነው” ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር እና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮማንደር ሌንጂሶ ጆተ በበኩላቸው ይህንን የነዋሪዎች ቅሬታ እንደማያውቁ ጠቅሰው “በሸገር ከተማ ስር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 ወረዳዎች አሉ እስካሁን ይህን መሰል ክስ አልገጠመንም” ብለዋል።
ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ እና በቡራዩ ከተማ 15 ዓመት የኖረ ግለሰብ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ ሁለት ጊዜ ገንዘብ ከፍሎ መለቀቁን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ ግለሰብ በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ሸገር ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ድሬ ከሚባል አካባቢ በፖሊሶች ተይዞ እስር ቤት መግባቱን ይናገራል።
ሁኔታውን ሲያስረዳም “በወቅቱ የመኪና አደጋ ገጥሞኝ ነበር። ልክ ክሊኒክ ልገባ ስል ከብበው ያዙኝ” ይላል።
በመጀመርያ ሚሊሻዎች ያዙት ቢሆንም በኋላ ላይ ፖሊሶች በመኪና መጥተው ሦስተኛ ወረዳ ወደሚባል ፖሊስ መምርያ እንደወሰዱት ይናገራል።
ምንም ጥፋት አላጠፋሁም የሚለው ይህ ግለሰብ ሁለት ወር ከሁለት ሳምንት ታስሮ መለቀቁን ያስረዳል።
“የተለቀቅኩት ሃያ ሺህ ብር ከፍዬ ነው። ከወጣሁ በኋላ ደግሞ ሌላ አስር ሺህ ለመክፈል ተገድጃለሁ” በማለት በአጠቃላይ ሰላሳ ሺህ ብር ከፍሎ ከእስር መውጣቱን ይናገራል።
የተጠረጠረበትን ወንጀል ሲያስረዳም “ከተማ ውስጥ ሆነህ ለሸኔ የሎጀስቲክ ድጋፍ እያቀረብክ ነው” የሚል መሆኑን ያስረዳል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመው እና አስፈራርቶ ገንዘብ መቀበል የተለመደ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
እንደ ፖሊስ፣ ደኅንነት ያሉ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በጉዳዩ ላይ የሚሳተፉ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ቢገልፁም፣ በከፍተኛ ሁኔታ ግን ተሳትፎ እያደረጉ ያሉት የአካባቢ ሚሊሻዎች ናቸው ይላሉ።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ “የፀጥታ ኃይሎች ተስማምተው፣ ተቀናጅተው፣ ሰላማዊ ዜጎችን ይዘው እና አስረው ገንዘብ ማስከፈል ቋሚ ሥራቸው አድርገውታል። ማንኛውም ሰው ወንጀል ከፈጸመ መጠየቁን እኛም አንቃወምም። ግን ይኸኛው ከዚህም የተለየ ነው” ይላል።
ይህ ግለሰብ ከወራት በፊት ከሚሰራበት የመንግሥት መሥርያ ቤት ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲያመራ በቡራዩ ክፍለ ከተማ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ይናገራል።
ፖሊስ ጣቢያ የደረሰበትንም ሲናገር “ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ከእስር ቤት እንደሚወጡ ወንጀል መርማሪዎች እና ፖሊሶች የሚናገሩበት ኮድ አላቸው” ይላል።
በዚህም መንገድ ሰዎች ገንዘብ ከፍለው መውጣታቸውን ይናገራል።
‘ፍርድ ቤት ማቅረብ የለም’
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩበት ጊዜ ክስ እንዳልተመሰረተባቸው እና ፍርድ ቤትም እንዳልቀረቡ፣ ነገር ግን ገንዘብ ከፍለው እንደወጡ ተናግረዋል።
ረቢራ የሸገር ከተማ ነዋሪ ሲሆን፣ ለደኅነነቱ ሲባል የየትኛው ክፍለ ከተማ ነዋሪ እንደሆነ እንዳይገለጽ ጠይቋል። እርሱም አንዲሁ ከሚሰራበት መሥርያ ቤት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ታስሮ ነበር።
ከታሰረ በኋላ 100 ሺህ ብር ከፍሎ እንዲወጣ ቢነገረውም ሳይስማማ በመቅረቱ ለአራት ወራት እስር ቤት መቆየቱን ለቢቢሲ ገልጿል።
“መንግሥት ለፖሊስ ደመወዝ የሚከፍለው ሕዝቡን እንዲጠብቁ እንጂ ሕዝቡን እንዲዘርፉ አይደልም” ሲል ይህ ወንጀል የዕለት ተዕለት ተግባር እየሆነ መምጣቱን ይናገራል።
ረቢራ አንድም ጊዜ ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ጨምሮ አስረድቷል።
“ከያዙኝ በኋላ ቢሮ ጠርተውኝ. . .መርማሪው ክፍል ስገባ የጠየቁኝ ምን ታሰራናለህ? ምን ትሰጠናለህ? ብለው በግልጽ ነው የጠየቁኝ። ፈርተህ ከፍለህ እንድትወጣ ያደርጉሃል። ሽጉጥ ትሸጣለህ፣ አንተ ሸኔ ነህ ይሉሀል። ካልከፈልካቸው አንተ አባ ቶርቤ ነህ ይሉሃል። ነገር ግን አንድም ማስረጃ አያቀርቡብህም።”
ረቢራ ገንዘብ አልከፍልም ሲል ለሥልጠና ብለው ወደ አዋሽ ወስደው እንዳሰሩት ይናገራል።
በግል ሥራ የሚተዳደረው ረቢራ ገንዘብ አለው ብለው የሚያሰቡትን ሰው “በዚህ መንገድ ስሙን አጠልሽተው ገንዘብ ለመቀበል ይሞክራሉ” ይላል።
ረቢራ አዋሽ ታስሮ ከወጣ በኋላ “አንተ በእርጥብ እጅ አልጨበጥከንም። ለዚያ ነው የታሰርከው አሉኝ” ሲል የፀጥታ አባላቱ ገንዘብ አለመስጠቱ ለእንግልቱ ምክንያት መሆኑን በተዘዋዋሪ እንደነገሩት ገልጿል።
“እነርሱ ላይ [የፀጥታ ኃይሎች] ምርመራ የሚያካሄድ ቢኖር፣ በርካቶቹ ሚሊየነሮች ናቸው። ምክንያቱም በየቀኑ በርካታ ሰዎች ናቸው ታስረው ገንዘብ ከፍለው የሚለቀቁት” ሲል ትዝብቱን ያጋራል።
እነዚህ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች፣ የሚከፍለው ገንዘብ ካለው ማንም የትኛውንም ዓይነት ወንጀል ፈጽሞ ወዲያውኑ መለቀቅ ይችላል ይላሉ።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ገንዘብ መጠየቅ ሲፈልጉ “ጠላት ወይንም የሸኔ ደጋፊ” በሚል ስም ያስፈራራሉ ሲሉም ያክላሉ።
ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ከሰጡ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው የሸገር ከተማ ነዋሪ “ፍርድ ቤት አቅርቡን ብለን ስንጠይቅ፣ ፍርድ ቤት እኛ ላይ ሥልጣን የለውም እንደፈለግን እናደርጋችኋለን” ብለው ማስፈራሪያ ተሰንዝሮባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, SM
መንግሥት በሚቀርብበት ክስ ላይ ምን ይላል?
የሸገር ከተማ አስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮማንደር ሌንጂሶ የነዋሪዎች ቅሬታ በዚህ ደረጃ መሆኑን እንደማያቁ ጠቅሰው “በሸገር ከተማ ስር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 ወረዳዎች አሉ፤ እስካሁን ይህን መሰል ክስ አልገጠመንም” ብለዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ሥነ ምግባር በቅርበት እንከታተላለን የሚሉት ኮማንደሩ፣ በግልም ሆነ በጋራ የቀረበ ቅሬታ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ገንዘብ ሰጥተው ከእስር የተለቀቁ እና ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎች ደግሞ ቅሬታ እንዳያቀርቡ “ከእስር ስንለቀቅ ገንዘብ ከፍለን እንደወጣን መረጃ እንዳንሰጥ ከፍተኛ ማስጠንቀቅያ ተሰጥቶናል” ይላሉ።
ኮማንደር ሌንጂሶ በበኩላቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ማንነታቸውን ሳይገልጹ ይህን መሰል ወንጀል የፈፀመን የፀጥታ ኃይልን ማጋለጥ የሚችሉበት መንገድ አለ” ሲሉ ያብራራሉ።
“ማንኛውም ሰው በአካል እኔም ጋር ወይም ሌላ ጋር መጥቶ ጥቆማ መስጠት ይችላል” የሚሉት ኮማንደሩ፣ ከዚህ በፊት በዚህ መንገድ የሥነ ምግባር እርምጃ የተወሰደበት እና የታሰረ የፖሊስ አባል እንዳለ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ አሸዋ ሜዳ የሚባለው አካባቢ፣ የፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ ሰዎችን አስረው ገንዘብ እየጠየቁ በመሆናቸው እና ነዋሪዎችን እያማረሩ በመሆኑ ‘ቤርሙዳ’ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
ሸገር ከተማ ከተቋቋመ በኋላ በዚያ አካባቢው በሚገኝ ፖሊስ መመርያ የሥነ ምግባር ጉድለት ባለባቸው የፀጥታ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ኮማንደር ሌንጂሶ ተናግረዋል።
“በአካባቢው በወሰድነው እርምጃ ከደረጃቸው ዝቅ የተደረጉ የፖሊስ አካላት አሉ። ሌሎች ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በሂደት ላይ ነው። ውሳኔ የተላለፈባቸውም አሉ” ሲሉ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የሸገር ከተማ ከመመሥረቱ በፊት ቡራዩ የሚገኘው ሦስተኛ ወረዳ ፖሊስ መምርያ ድብደባ፣ እንግልት እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜ የሚታሰሩበት እንደሆነ ይነገራል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እማኞችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
ኮማንደር ሌንጂሶ ግን በፖሊስ መምርያው ይፈጸማል ስለሚባለው እንግልት እና ሰዎችን አስሮ ገንዘብ መጠየቅን በሚመለከት መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።
‘ከወጣን በኋላም ዛቻ ይደርስብናል’
ስማቸውን ሳይጠቅሱ ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ እና የሚኖሩበትን ክፍለ ከተማ መጥቀስ ያልፈለጉ ሰዎች ገንዘብ ሰጥተው ከእስር ከወጡ በኋላ ዛቻ እየተከተላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ተበድያለሁ ከሚሉት መካከል አንዱ የሆኑት ግለሰብ፣ የፀጥታ አካላት መንገድ ላይ አሁንም ሲያገኙት ጥርሳቸውን እንደሚንክሱበት ይናገራል።
“ከወጣንም በኋላ አልቀረልንም። አንድ ቀን አለቃቸው ራሱ መንገድ ላይ አግኝቶኝ፣ እናንተ አሁንም ሰላም እየነሳችሁን ነው አይደል ሲል ዝቶብኛል” ይላል።
ረቢራም እንዲሁ ከእስር ከወጣም በኋላ ስልክ እየተደወለ ዛቻ እንደሚደርስበት ይናገራል።
“ይኸው ዛሬ እንኳ ደውለውብኝ ነበር። ና ና ይህንን አድርግልን፤ ይህንን ካላደረግክ እንዲህ እናደርግሃለን፤ [ገንዘብ ካልሰጠኽን አናስርሃለን] ይሉኛል” ይላል።
ረቢራ ታስሮ በነበረበት ወቅት ቤቱ ተፈትሾ የቤት እቃዎች እንደተወሰደበት ተናግሯል።
ከእስር ከተለቀቀም በኋላ የተወሰደበትን ንብረት ለማስመለስ ወደ ፖሊስ መምሪያ ቢሄድም ምላሽ እንዳላገኘ ይናገራል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰዎችን አግተው የመሰወር ሂደት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል በማለት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
ብዙ ጊዜ ሲቪል በለበሱ እና የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎች እየታሰሩ እንደሆነ የሚጠቅሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ ይህ ዓይነቱ ተግባር በተለይ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ አካባቢዎች እና በአማራ ክልል በስፋት እየገጠመ አንደሆነ ገልጿል።
ኮሚሽኑ አክሎም ለእንደዚህ ዓይነት ተግባር የተጋለጡ ሰዎች ከቤታቸው፣ ከመሥሪያ ቤታቸው እና ከጎዳናዎች ላይ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ የማይታወቅ ቦታ ተወስደው እንደሚደበቁ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ከደረሰው ጥቆማዎች አንጻር ባደረገው ክትትል ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ተይዘው የተደበቁ ሰዎች ገሚሶቹ በቀናት፣ በሳምንታት እና በወራት ጊዜ ውስጥ ሲገኙ፣ ሌሎች ግን ደብዛቸው ሳይገኝ እንደቀረ መረዳቱን ገልጿል።












