ሩሲያ የዩክሬንን ትልቅ ግድብ መደብደቧ ተገለጸ

የተጎዳው ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Maxar images

የዩክሬን መከላከያ፣ ሩሲያ በአገሪቱ የሚገኝ ትልቅ ግድብን ደብድባ ጉዳት እንዳደረሰች ገለጸ።

በሞስኮ ቁጥጥር ሥር በወደቀው የዩክሬን ደቡባዊ ግዛት የሚገኘው ይህ ግድብ በሩሲያ ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል።

ከግድቡ በታች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በጎርፍ ሊወሰዱ እንደሚችሉ ተሰግቷል።

በሩሲያ ሹመት የተሰጣቸው አስተዳዳሪ በበኩላቸው የግድቡ የኃይል ቋት የላይኛው ክፍል ብቻ በድብደባው ጉዳት እንደደረሰበትና ግድቡ ግን እንዳልተጎዳ ተናግረዋል።

በሁለቱም ወገን ያሉትን ክሶች ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

በሶቭየት ዘመን የተገነባው ግድብ በዩክሬን፣ ኼርሶን ግዛት፣ በኖቫ ካክሆቫክ ነው የሚገኘው።

ይህንን ከተማ ጨምሮ ሌሎችም በአካባቢው ያሉ ግዛቶች በሩሲያ ሥር ናቸው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት እና መከላከያ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

የምክር ቤቱ ጸሐፊ ኦሌክሲ ዳንሎቭ በትዊተር ገጻቸው “ውይይቱ ከካኽቮስኪ ግድብ ፍንዳታ ጋር የተያያዘ ነው” ብለዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የታዩ ምሥሎች ግድቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ያሳያሉ።

ግድቡ የተሠራበት ዲፕሮ የተባለው ወንዝ ወደ ኼርሶን አቅጣጫ እየፈሰሰ መሆኑም ተገልጿል።

በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ የሚኖሩ ሰዎች በፍጥነት አካባቢውን ትተው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

ዩክሬን ለፍንዳታው ተጠያቂ ያደረገችው ሩስያን ነው። ዩክሬናውያን ይህንን መስመር ተጠቅመው ወታደር በማሻገር መልሶ ማጥቃት ያደርጋሉ በሚል ፍርሃት ሩሲያ እርምጃውን ወስዳ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።

የዩክሬን መከላከያ ሠራዊት አማካሪ ዩሪ ሳክ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የስልክ መስመር መቆራረጥ እንደገጠመና ይህም ሩሲያ ተጨማሪ ግድቦች ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል እንደሚጠቁም ገልጸዋል።

የኼርሶን ወታደራዊ ንቅናቄ ኃላፊ ኦክሳንደር ፕሮኩዲን ቢያንስ ስምንት መኖሪያ አካባቢዎች በጎርፍ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

ቢያንስ 16 ሺህ ሰዎች የጎርፍ ስጋት እንደተጋረጠባቸውም አክለዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጄምስ ክቫርሊ ግድቡ ላይ የደረሰው ጥቃት የሩሲያ ወረራ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።