በእስራኤል ወታደር የተተኮሰበት ፍልስጤማዊ ህጻን ሕይወቱ አለፈ

ሞሃመድ ታሚም

የፎቶው ባለመብት, PLO DEPT OF PUBLIC DIPLOMACY

የምስሉ መግለጫ, ሞሃመድ ታሚም በእዚህ ዓመት የተገደለ በእድሜ ትንሹ ፍልስጤማዊ ነው።

ከአራት ቀናት በፊት የእስራኤል ጦር ጭንቅላቱ ላይ በተኩስ የመታው የሦስት ዓመት ህጻን ሕይወቱ አልፏል።

ሞሃመድ ታሚሚ የተባለው ህጻንና ከአባቱ ጋር በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለው ዌስት ባንክ ከሚገኘው ቤታቸው በመውጣት ላይ ሳሉ ነበር የተተኮሰባቸው።

የእስራኤል ጦር በአይሁዶች መንድር ቀደም ብለው ጥቃት አድርሰው የሸሹ ታጣቂዎችን በሚያሳድድበት ጊዜ ተኩስ መክፈቱን ገልጿል።

ክስተቱን ተከትሎ ጦሩ ባወጣው መግለጫ ያልታጠቁ ሰዎች ላይ ላደረሰው ጉዳት ጸጸት እንደተሰማው ገልጿል።

በተከፈተው ተኩስ የተጎዳው የፍልስጤም አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ቢላል ታሚም ህጻኑ በተጎዳበት ስፍራ አድፍጦ የቆየው የእስራኤል ጦር ተሽከርካሪ ሲመጣ ተኩስ መክፈቱን ተናግሯል።

ህጻኑ በእስራኤል ወታደራዊ ሂሊኮፕተር ለጭንቅላት ህክምና እስራኤል ወደሚገኝ የህጻናት ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ ልትተርፍ አልቻለችም።

በተኩሱ የተጎዳው አባቱ ሃይታም ፍልሰጤም ከሚገኝ ሆስፒታል ህክምናውን ጨርሶ ወጥቷል። ልጁ ከመሞቱ በፊት እስራኤል በሚገኘው ሆስፒታል ልጁን መጎብኘት ችሏል።

የእስራል ጦር ቀደም ብሎ ሁለት ታጣቂዎች ሲተኩሱ የሚያሳይ ሊሆን የሚችል ጥራት የሌለው ቪዲዮ አጋርቷል።

ጦሩ በአይሁዱ መንድር የነበረው ተኩስ “ለረዥም ደቂቃዎች” የቆየ ነው ብሏል።

ጨምሮም የእስራኤል ወታደሮች በተኩስ ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜ ሁለቱ ፍልስጤማውያን ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልጿል።

“የእስራኤል ጦር ያልታጠቁ ሰዎች በመጎዳታቸው ጸጸት ይሰማዋል። እንዲህ አይነት ክስተቶችን ለመከላከል ባለው አቅም ሁሉ ይሰራል” ሲልም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

በታጣቂዎች ተኩስ የተከፈተበት ሃላሚሽ የተኘው የአይሁዶች መንድር እንደ አውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ የተመሰረተ ሲሆን በአቅራቢያ ከሚገኘው የፍልስጤሞች መንድር ጋር ተደጋጋሚ ፍጭት የሚታይበት ነው።

በአካቢው ለበርካታ አመታት በየሳምንቱ አርብ አክቲቪስቶች መሬታቸው እንደተወሰደ በመጠቀስ ተቃውሞ ያሰማሉ።

ይህ ተቃውሞ ብዙ ጊዜ ወደ ግጭት የሚያመራ ሲሆን የእስራኤል ወታደሮች ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስና የፕላስቲክ ጥይት ይጠቀማሉ።

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ ጀምሮ 150 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በአስራል ጦር ወይም በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ፣ ምስራቃዊ እየሩሳሌም እና ጋዛ ሰርጥ በሚገኙ ሰፋሪዎች ተገድለዋል።

ይህ ቁጥር ሲቪልና የታጠቁ ሰዎችን የሚያካትት ነው።

በእስራኤል በኩል ደግሞ 23 ሰዎች ከእስራኤል ፍልስጤም ግጭት ጋር በተያያዘ ተገድለዋል። ከተገደሉት ውስጥ አንዱ የእስራኤል ጦር ሃይል አባል ነው።

በሁለቱም በኩል ከሟቾች ውስጥ ህጸናት የሚገኙበት ሲሆን ሞሃመድ ታሚም በዌስት ባንክ የተገደለ በእድሜ ትንሹ ሰው ነው።

ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ሰፋሪዎች በአሁኡ ሰዓት በዌስት ባንክና ምስራቃዊ እየሩሳሌም ይኖራሉ።

ምንም እንኳን እስራኤል ባትቀበለውም ሰፋሪዎች በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ህገወጥ ተደርገው ይወሰዳሉ።