ቫግነር ‘ጠጥቶ’ ተኩስ ከፍቷል ያለውን ሩሲያዊ ወታደር አገተ

ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር አንድ መደበኛ የሩሲያ ወታደራዊ ባለሥልጣንን ማገቱን ገለጸ።

ዩክሬን ውስጥ በቫግነር ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ከፍቷል ተብሎ ነው ወታደሩ የታገተው።

ወታደሩ ተኩስ የከፈተው መጠጥ ጠጥቶ እንደሆነ ተንቀሳቃሽ ምሥል አሳይቷል። ወታደሩ ይህንን ያደረገው ቫግነርን ስለሚጠላ እንደሆነም ተገልጿል።

ቴሌግራም ላይ በተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሩሲያዊው ወታደራዊ ባለሥልጣን ስለ ክስተቱ ሲጠየቅ ይታያል።

በቫግነር ተሽከርካሪ ተኩስ የከፈተው በመጠጥ ተገፋፍቶና “የግል ፀብም” ስላለበት እንደሆነ ገልጿል።

የቫግነር መሪ እንዳለው፣ የሩሲያ ወታደሮች ባኽሙትን ጥለው የሚወጡበት መንገድ ተመቻችቷል።

ቫግነር እና የሩሲያ ወታደሮች መካከል ፍጥጫ ተስተውሏል።

የቫግነር መሪ የቨግንሊ ፕሪጎዚን የሩሲያ ከፍተኛ መከላከለያ ኃላፊዎች ላይ ብዙ ጥቃት ሰንዝሯል።

በዩክሬን ባኽሙት ውጊያ በቂ መሣሪያ አልቀረበም ሲል በመክሰስ ነው ጥቃት የሰነዘረው።

ቫግነር ሩሲያን ደግፎ ጦርነቱን በዚያ አካባቢ መርቷል። ከጦርነቱ ዘለግ ያለ ጊዜ የወሰደውም ይህ ነው።

ባለፈው ወር ቫግነር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረና ለሩሲያ መደበኛ ወታሮች እንደሚያስረክብ አስታውቋል።

መጠጥ ጠጥቶ ተኩስ ከፍቷል የተባለው ወታደር ከ10 እስከ 12 የሚደርሱ የትግል ጓዶቹ የቫግነር ወታደሮችን ትጥቅ እንዳስፈቱ ገልጿል።

ለምን ቫግነርን እንደሚጠላ ሲጠየቅ “አላውቅም” ብሎ መልሷል።

ይህንን ምላሽ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምሥል ከተለቀቀ በኋላ የቫግነር መሪ ባወጣው ሪፖርት፣ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ከባኽሙት መውጫ መንገድ ላይ ፈንጂ መቅበራቸውን ገልጿል።

ይህ መንገድ የቫግነር ተዋጊዎች ከባኽሙት ለመውጣት የሚጠቀሙበት ነበር።

የቫግነር መሪ መንገድ ላይ ፈንጂ ስለመቀበሩ ማስረጃ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ፣ የታገተውን ወታደር ምሥል አሳይቷል።

“ይኸውላችሁ የኬኩ ክሬም። ጥርጣሬ የለንም” ብሏል።

የቫግነርን ክስ ለማረጋገጥ ቀላል ባይሆንም በሩሲያ መደበኛ ወታደሮችና በቫግነር ተዋጊዎች መካከል ቁርሾ መፈጠሩን መረዳት ይቻላል።

ቫግነር በባኽሙት ከፍተኛ ሽንፈት ነው የገጠመው።

የሩሲያ መከላከያ ኃይል በባኽሙት ዙርያ ያሉ ቦታዎችን ማጣቱን ቫግነር ይከሳል። “ውርደት” ሲልም ገልጾታል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጊ ሾይጉ እና የቡድን ኃላፊው ቫለሪ ገርሚሶቭ ጣልቃ እንዲገቡም ጠይቋል። ወደ ጦር ግንባር ሄደው እየሸሹ ናቸው ያላቸውን ወታደሮችን እንዲቀሰቅሱ ቫግነር ጠይቋል።

“ይሄን ማድረግ ትችላላችሁ። ካልቻላችሁም በጀግንነት ትሞታላችሁ” ብሏል መሪው።