ፑቲን ደቡብ ኮሪያ ዩክሬንን ብታስታጥቅ “ትልቅ ስህተት ነው” ሲሉ አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ብታደርግ “ትልቅ ስህተት ነው” በማለት አስጠነቀቁ።

የፕሬዝዳንቱ አስተያየት የተሰማው ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ በዩክሬን ጉዳይ ያለኝን አቋም መልሼ አጤናለሁ ካለች በኋላ ነው።

ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ከየትኛውም ወገን በአንዳቸው ላይ ጥቃት ቢፈጸም አንዳቸው ሌላኛቸውን ለመከላከል ወታደራዊ ስምምነት መፈጸማቸውን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍን ስለመስጠት እያጤንኩ ነው ብላለች።

ሶውል ለኪዬቭ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ብትወስን ሞስኮ “የደቡብ ኮሪያን መንግሥት የማያስደስት ውሳኔን ትወስናለች” ሲሉ ፑቲን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አሜሪካ እና አጋሮቿ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ ከቀጠሉ ሞስኮ ለፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ ትሆናለች ብለዋል።

“ወታደራዊ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ [ለዩክሬን] ከእኛ ጋር ጦርነት ውስጥ እንዳልገቡ ነው የሚያምኑት። ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፤ ፒዮንግያንግን ጨምሮ በተቀረው ዓለም ለሚገኙ አገራት ወታደራዊ ድጋፍ የማድረግ መብት ይኖረናል” ብለዋል ፑቲን።

የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ስምምነትን ብሔራዊ ደኅንነቴን የሚጎዳ ነው ስትል ደቡብ ኮሪያ ቅሬታዋን አሰምታ ነበር።

የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቻንግ ሆ-ጂን አገራቸው “ለዩክሬን ወታደራዊ ግብዓቶችን ስለመላክ መልሳ እያጤነች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ደግሞ “የሩሲያ ውሳኔዎች ላይ ተመስርተን ለዩክሬን ሊደረግ ስለሚችል ወታደራዊ ድጋፍ የተለያዩ አማራጮችን እየተመለከትን ነው” ብሏል።

ደቡብ ኮሪያ ምንም እንኳን ሰብዓዊ እርዳታዎችን ብታደርግም እስካሁን ድረስ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍን ለማድረግ ፍቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች።

ዩክሬናውያን በሞስኮ እና ፒዮንግያንግ መካከል ወታደራዊ ትብብር መጠናከር ደቡብ ኮሪያ ዩክሬንን በተመለከተ የያዘችውን አቋም ትቀይራለች የሚል እምነት አላቸው።

በፑቲን የፒዮንግያንግ ጉብኝት ወቅት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት “ሙሉ በሙሉ” ትደግፋለች ስለማለታቸው ተገልጿል።

ምዕራባውያን ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ባለችው ጦርነት የፒዮንግያንግ ሚሳኤሎችን እየተጠቀመች እንደሆነ ያምናሉ።

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢይ በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን የሚጥር የትኛውም አገርን የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ስምምነት ያሳስበዋል ብለዋል።

ጃፓን እንዲሁ የፒንግያንግ እና የሞስኮ ስምምነት አሳሳቢ ነው ብላለች። የጃፓን መንግሥት ቃል አቀባይ ዮሺማሳ ሃያሺ “ተቀባይነት” የሌላው ባሉት ስምምነት ሞስኮ ከፒዮንግያንግ ጋር “ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ስምምነትን ጨርሶ መድረስ አልነበረባትም” ብለዋል።