የፑቲን የሰሜን ኮሪያ ጉዞ ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰሜን ኮሪያ ደርሰዋል።
ፑቲን ከ24 ዓመታት በኋላ እግራቸው በድጋሚ ፒዮንግያንግን ረግጧል።
ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው መስከረም በሩሲያዋ ቮስቶቺኒ ኮስሞድሮም ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ፑቲንም አገራቸውን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበውላቸው ነበር።
ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ዕድገት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ጉብኝቱ በተለይም ሊደረስ ከሚችለውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት አንጻር የመላውን ዓለም ትኩረትን ስቧል።
ጉብኝቱ በሞስኮ እና ፒዮንግያንግ መካከል በባህል፣ ግብርና እና ቱሪዝም ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነትም ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ ጉብኝቱ የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር መርሃ ግብሮች መደገፍን የተመለከተ መሆኑ ነው።
በሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ግንኙነት ዙሪያ ምርምሮችን የሚያደርጉት ኪም ዶንግ ዩፕ (ዶ/ር) የመሪዎቹ ጉባኤው ጥልቅ ውይይት ከሚደረግበት ይልቅ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
ሦስቱ አበይት የጉብኝቱ ዓላማዎች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ወታደራዊ፡ ሩሲያ የጦር መሳሪያ ትፈልጋለች፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ ቴክኖሎጂ
ሩሲያ ዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ሆኖታል።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ደግሞ እርስ በእርስ ጥገኛ እየሆኑ መጥተዋል።
የመሪዎቹ ዋና አጀንዳ "በሰሜን ኮሪያ የተሠሩ የጦር መሳሪያዎች ምን ያህል ለሩሲያ ስለመቅረባቸው ነው" ይላሉ በኮሪያ ዩኒቨርሲቲ የውህደት እና ዲፕሎማሲ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ዶ/ር ናም ሱንግ ዎክ።
ውይይቶቹ ከአጭር ጊዜ ስምምነቶች በዘለለ በዋና ዋና የጦር መሳሪያዎች ላይም ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል ብለው ያምናሉ። ሁለቱ አገራት የጦር መሳሪያዎችን በጋራ ማልማትን ጨምሮ በወታደራዊ ትብብር ላይ ሊስማሙ ይችላሉ።
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ ከምግብ እና ነዳጅ በላይ ልትጠይቅ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ሰሜን ኮሪያ ግንቦት ወር ላይ ሳይሳካ የቀረ ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ሞክራ ነበር። በዚህም ሩሲያ በኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ቴክኒካል ድጋፍ እንድታደርግላት ልትጠይቅ ትችላለች ሲሉ ዶክተር ናም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የጠፈር ቴክኖሎጂ ላይ ትልቅ አቅም ያላት ሩሲያ፣ ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ሳተላይቶችን በተሳካ ሁኔታ እንድታመጥቅ ድጋፏ ወሳኝ ይሆናል።
ሰሜን ኮሪያም የስለላ ሳተላይቶቿን ለማሻሻል እና ኒውክለር ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከቦችን ለማምረትም የሩሲያን ድጋፍ እንደምትፈልግ ይገመታል።
ስለኒውክለር የጦር መሳሪያ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች ለህዝብ ይፋ ሊሆኑ አይችሉም ብለው ዶ/ር ናም ያምናሉ።
ፑቲን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ወደ ዩክሬን መግባታቸውን እና ሩሲያን ግዛት ለማጥቃት ሊውሉ መቻላቸውን ከግምት በማስገባት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ኢኮኖሚ፡ ሩሲያ የጉልበት ሠራተኞችን ትፈልጋለች፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያም የኢኮኖሚ ትብብር ማሳደግን በተመለከተ መምከራቸው አይቀሬ ነው።
በዶንግ-ዋን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዲፕሎማሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ካንግ ዶንግ ዋን እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ አሁን ከሩሲያ በጣም የምትፈልገው "ከሠራተኞች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ነው።" ይህ ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ሠራተኞችን ወደ ሩሲያ የመላክ አጋጣሚን ከፍ ያደርገዋል።
ሩሲያ በበኩሏ በጦርነቱ የተጎዱ ሕንፃዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት እና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የሠው ጉልበት ያስፈልጋታል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ጦሯን በመቀላቀል እና ወጣቶች ወደ ውጭ በመሸሻቸው ምክንያት ከፍተኛ የሠራተኛ እጥረት ስላጋጠማት ሁለቱ መሪዎች ከሰሜን ኮሪያ ሠራተኞችን በመቅጠር ዙሪያ ሊወያዩ እንደሚችሉ ዶ/ር ካንግ ይናገራሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ በጣለው ማዕቀብ ምክንያት ዜጎቿ ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዳይሰሩ ተከልክለዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ሠራተኞች ለመቅጠር በይፋ ብትንቀሳቀስ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ መቃቃርን ሊያስከትልባት ይችላል።
ስለዚህ ሁለቱ አገራት በዓለም አቀፍ ተቃውሞ እና በዲፕሎማሲያዊ ጫና ውስጥ ሆነው የኢኮኖሚ ትብብርን እንዴት እንደሚያስቀጥሉ የሚታይ ይሆናል።
የባሕል ልውውጥ፡ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚደረግ ቱሪዝም እያደገ ነው?
እአአ በየካቲት 2020 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቢቋረጥም፤ ሩሲያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የቡድን ጉብኝዎችን ትልክ ነበር።
በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል ያለው የመንገደኞች የባቡር አገልግሎት ከአራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 6 ሥራ ጀምሯል።
እንደ ፕሪሞርስኪ ክራይ አስተዳደር (አንዱ የሩሲያ ክልላዊ መንግሥት) መረጃ ከሆነ ከየካቲት እስከ ግንቦት 2024 ባለው ጊዜ ከ 400 በላይ የሩሲያ ቱሪስቶች ወደ ሰሜን ኮሪያ ተጉዘዋል።
የሩሲያ የጉዞ ወኪል የሆነው ቮስቶክ ኢንቱር በድረ-ገጹ በ750 ዶላር ከአራት እስከ አምስት ምሽት ጉብኝት ወደ ሰሜን ኮሪያ ቱሪስቶችን እንደሚልክ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። ኤጀንሲው እስከ ምስከረም ድረስ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚደረጉ የቡድን ጉብኝቶችን ዘርዝሮ አስቀምጧል። በዚህም የፔክቱ ተራራን፣ የሰሜን ኮሪያ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት እና የኮሪያ ጦርነት ዓመታዊ ክብረ በዓላትን መመልከትን ያካትታል።
በሰሜን ኮሪያ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኪም ዶንግ ዩፕ "ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ግንኙነትን ለማሻሻል ትልቅ ሚና ይጫወታል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እንደ ዶ/ር ኪም ዶንግ-ዩፕ ከሆነ ሩሲያዊያን በሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉት ጉብኝቶች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳደግ ያግዛሉ። የህዝብ ለህዝብ ጉብኝቶች እርስ በርስ መደጋገፍን ከማጠናከር ባለፈ ወታደራዊ ውጥረትን ለመቀነስም አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የውጭ ቱሪስቶች ሰሜን ኮሪያን መጎብኘታቸው አገሪቱ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ራሷን ያገለለች እና አደገኛ ናት የሚለውን ገጽታዋን ለማላላት ይረዳል ሲሉ ይሞግታሉ።
የሰሜን ኮሪያ ቱሪዝም ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ የአገሪቷን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ለማሻሻል ጠቃሚ የማህበራዊ እና የባህል ልውውጥ ዘዴም ተደርጎ ይወሰዳል።
ይሁን እንጂ በቅርቡ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚደረጉ የቡድን ጉብኝቶች የተሰረዙ ሲሆን አንዳንድ ቱሪስቶች በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ያለው ውጥረት እየጨመረ መሄዱን እንደስጋት አንስተዋል።
የሩሲያ የጉዞ ወኪል የሆነው ቮስቶክ ኢንቱር በቅርቡ እንደዘገበው ለግንቦት የታቀደ የአራት ቀናት የቡድን ጉብኝት በጎብኚዎች እጥረት ምክንያት ተሰርዟል።
የሰሜን ኮሪያ ውስን የቱሪዝም መሠረተ ልማት እና የውጭ ዜጎች በነፃነት እንዳይዘዋወሩ መገደቧ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ እንዳያድግ ተግዳሮት ፈጥሯል።
ፕሮፌሰር ካንግ አክለውም የሰሜን ኮሪያ-ሩሲያ ግንኙነት የቱሪዝም ትብብርን ለማሳደግ ስለመወያየት ዕድል ይሰጣል ብለው ያምናሉ።
የአሁኑ ፑቲን ከ24 ዓመታት በፊት ካደረጉት ጉብኝት በምን ይለያል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ በ2000 ፕሬዝዳንት ፑቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ፒዮንግያንግን ጎብኝተው ከወቅቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ጋር ተገናኝተዋል። ጉብኝቱ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ግንኙነት ነው።
በወቅቱ ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንደገና ማንሰራራት የምትፈልግበት፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ እአአ በ 1990ዎቹ የሰሜን ኮሪያን ረሃብ ከሚባለው አስቸጋሪ ወቅት በኋላ ከውጪው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ የምትፈልግበት ወቅት ነበር።
ሁለቱ መሪዎች የሩሲያ-ኮሪያ የጋራ መግለጫን አወጡ። ይህም የሁለትዮሽ ትብብር እና የጋራ መረዳዳትን፣ የሰሜን ኮሪያን ሚሳኤል ጉዳይ የተመለከተ እና ወዳጅነት እንዲሁም ትብብርን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
ወታደራዊ ትብብርን በተመለከተ ደግሞ ሁለቱ አገራት ጥቃት ወይም አደጋ ሲደርስባቸው ወዲያውኑ እርስ በርስ እንዲገናኙ ስምምነቱ ይደነግጋል።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ አሁን ካሉበት ውጥረት አንጻር ስምምነቱ በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ሊታደስ እንደሚችል ባለሙያዎች ጥርጣሬያቸውን አስቀምጠዋል።
"ቀደም ሲል ፑቲን ወደ ሰሜን ኮሪያ ጉብኝት የፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትንኮሳዎች ውስን በነበሩበት ጊዜ ነበር። አሁን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሯል" በማለት ዶ/ር ናም ያብራራሉ። ግንኙነቱ “ከባለፈው ጊዜ የበለጠ ትብብር ብቻ ሳይሆን ወደ ጥምረት የተጠጋ ሊሆን ይቻላል” ሲሉ አክለዋል።
ለዶ/ር ናም ካለፈው ጉብኝት አንጻር የአሁኑ ያለው ዋናው ልዩነት ሰሜን ኮሪያ አሁን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት መሆኗ ነው።
"አሜሪካን ያማከለው የአንድ አገር የበላይነት ስርዓት እየተዳከመ ዓለም አቀፉ ስርዓት እየተቀየረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ የአገራቸውን ጥቅም ለማስከበር መተባበር የሚችሉባቸውን አዳዲስ መንገዶች እንደሚፈልጉ ይጠበቃል" ብለዋል ዶ/ር ኪም።
“በቅርብ ጊዜ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት ከግምት በማስገባት ሰሜን ኮሪያ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ ልትነድፍ ትችላለች” ሲሉም አክለዋል።












