በአራት መተላለፊያዎች በኩል ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እየገባ መሆኑን ተመድ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በአማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ አራት መተላለፊያዎች ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እየደረሰ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ገለጸ።
ኦቻ ሐሙስ ታኅሣሥ 06/2015 ዓ. ም. ባወጣው ዕለታዊ የሁኔታ መግለጫ እንደጠቀሰው፣ ከኅዳር 06 እስከ ኅዳር 29/2015 ዓ.ም. ባሉት ቀናት የተመድ አጋሮች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1,600 በላይ በሚሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሰብአዊ እርዳታ ተልኳል።
ከ63,800 ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ከ4,000 ሜትሪክ ቶን በላይ የጤና፣ የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የውሃ እና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ትግራይ መድረሳቸውንም የኦቻ መግለጫ ያትታል።
“የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞቻችን በሰጡን መረጃ መሠረት ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ወደ ትግራይ እርዳታ የሚላክበት መንገድ እየተሻሻለ ይገኛል” ይላል መግለጫው።
በሰላም ስምምነቱ ከተካተቱ ዋነኛ ነጥቦች መካከል ግጭትን ከመግታት በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩ የስልክ፣ የመብራት፣ የኢንተርኔት፣ የበረራ እና የባንክ አገልግሎቶችን መመለስ እንዲሁም ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማፋጠንን ያካትታል።
ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ተመድ፣ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር እና ሌሎችም የተራድኦ ድርጅቶች ወደ ትግራይ ሰብአዊ እርዳታ እየላኩ መሆናቸውን አሳውቀዋል። ሆኖም ግን ካለው ፍላጎት አንጻር እየቀረበ ያለው እርዳታ በቂ እንዳልሆነና ተጨማሪ እርዳታም በአፋጣኝ መላክ እንደሚገባው ሲገለጽ ቆይቷል።
ኦቻ ባወጣው መግለጫ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የሕክምና መስጫዎች በሰብአዊ በረራ መድረሳቸውን ጠቅሷል።
“ተደራሽነቱን ለማስፋት ተከታታይ ሰብአዊ በረራዎች እየተካሄዱ ነው። ወደ ትግራይ ከሚደረጉ ሰብአዊ በረራዎች በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ ኅዳር 30/2015 ዓ.ም. ከመቀለ ወደ ሽረ የእርዳታ ሠራተኞቻችን ተጉዘዋል። ከዚያ ቀን ወዲህ ጉዞው ቀጥሏል” ይላል መግለጫው።
ሆኖም ግን ካለው ፍላጎት አንጻር እንዲሁም ቀደም ሲል ሰብአዊ እርዳታ ተቋርጦ መቆየቱን ከግምት በማስገባት፣ አሁን እየተላከ ያለው እርዳታ ቀጣይነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ተገልጿል።
አክሱም እና ሽረን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ እና ቴሌኮምንኬሽን አገልግሎቶች እንደተመለሱ የገለጸው ኦቻ፣ “ይሄ ለሰብአዊ እርዳታ አወንታዊ እርምጃ ነው። ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በመመለስ ረገድ ተጨማሪ መሻሻሎች ሊታዩ ይገባል” ሲል አክሏል።
አያይዞም፣ በጦርነቱ በተጎዱ የአፋር እና አማራ ክልሎች አካባቢዎች ድጋፍ የመስጠት እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች መጨመረቻውን አሳውቋል።
“በተለይም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩና የደኅንነት ስጋት በመቀነሱ ወደ መንደራቸው እየተመለሱ ያሉ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል” ሲልም ኦቻ አሳስቧል።












