ሰብአዊ ቀውስ በሚባባስባቸው አገራት ዝርዝር ኢትዮጵያ ሁለተኛ ተባለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ በ2023 ሰብአዊ ቀውስ ከሚባባስባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ተቀመጠች።
ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (አይአርሲ) ትላንት ታኅሳስ 5/ 2015 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ በ2023 ሰብአዊ ቀውስ ይበረታባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ 20 አገራትን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ከሶማሊያ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ተጠቅሳለች።
በየዓመቱ ለአደጋ የተጋለጡ ዝርዝር በሚወጣበት ሪፖርት ላይ፣ አይአርሲ በግንባር ቀደምነት ያስቀመጠው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና አፍጋኒስታንን ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ የተባባሰው ድርቅ እያሳደረ ካለው ተጽዕኖ ባሻገር የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንደ አፍጋኒስታን ያሉ አገራትን መፈተኑን እንደሚቀጥል ሪፖርቱ ይጠቁማል።
በዝርዝሩ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የመን፣ ሶርያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሄይቲ እና ዩክሬን ተካተዋል።
በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ አንድ ሦስተኛው ለሰብአዊ ቀውስ እንደተጋለጠ የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ሰብአዊ ቀውስ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ የሚረዱት ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶች፣ የጦርነት ሕግጋት እና ሰብአዊ እርዳታ እየተዳከሙ መምጣታቸውን ይገልጻል።
ሰብአዊ ቀውስ በጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በምጣኔ ሀብት መሽመድመድ ምክንያት እየተባባሰ እንደመጣም ያክላል።
የአይአርሲ ዋና ኃላፊ ዴቪድ ሚሊባንድ፣ ቀጣዩ ዓመት ሰብአዊ ቀውሶች የሚባባሱበት እንደሆነ ተናግረዋል።
“አምና የሥርዓት መሽመድመድ ያስከተሉ የዲፕሎማሲ፣ የሕግና ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ብንሞክርም የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት፣ መፈናቀል እና የምግብ እጥረት ተባብሰው ቀጥለዋል” ብለዋል።
በተለይም በግጭት ቀጠና ውስጥ ያሚኖሩ ሰዎች ከለላ ማጣት ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል።
አገራዊ፣ ቀጠናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ከለላዎች በግጭት መስፋፋት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በምጣኔ ሀብት ውድቀት ሳቢያ መዳከማቸውን ዋና ኃላፊው አስረድተዋል።
“በዚህ ዝርዝር የገቡ አገራት አብዛኞቹ ባለፉት አሥር ዓመታት ወታደራዊ ግጭት ገጥሟቸዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በምሥራቅ አፍሪካ ሚሊዮኖችን ለረሃብ አጋልጧል። ዓለም አቀፍ የኑሮ ውድነት መከሰቱ ሩሲያ በጥቁር ባሕር ላይ ከጣለችው እቀባ ጋር ተደማምሮ አገራቱን ወደ አዘቅት ከቷል” በማለት አብራርተዋል።
እነዚህ ቀውሶች ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የደኅንነት እና የአየር ንብረት ለውጥ በመሆናቸው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ርብርን እንደሚጠይቁ የተቋሙ ዋና ኃላፊ አስምረውበታል።
እአአ በ2030 እርዳታ የሚፈልጉ ወደ 340 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንዳሉ የአይአርሲ ሪፖርት ይጠቁማል።
በሪፖርቱ ላይ ከተቀመጡት ሦስት ምክረ ሐሳቦች አንደኛው፣ አገራት ከቀውስ እሽክርክሪት እንዲወጡ የሚያሳስበው ነው። ለረሃብና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰጠው ድጋፍ ከፍ እንዲል ተጠይቋል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ በግጭት ውስጥ ንጹኃን ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተቋሙ አሳስቧል። የንጹኃን ዜጎች መብት እንዲከበር፣ ገለልተኛ ወገኖች እርዳታ እንዲያደርሱ፣ ሴቶች በሰላምና ደኅንነት ድርድሮች እንዲሳተፉ እንዲሁም የጅምላ ወንጀሎች ሲፈጸሙ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱን እንዲተገበር ተጠይቋል።
ሦስተኛው ምክረ ሐሳብ፣ ለቀውሶች ዓለም አቀፋዊ ምላሽ መስጠት ሲሆን፣ ከአየር ንብረት ለውጥና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሚደረጉ አካላት እንዲኖሩና የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ እንዲሰጣቸው ያሳስባል።












