የሃንጋሪዋ ፕሬዝዳንት ለእስረኛ በሰጡት ምህረት ምክንያት ሥልጣን ለቀቁ

ፕሬዝዳንት ካትሊን ኖቫክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ካትሊን ኖቫክ

በልጆች ላይ የተፈጸመን ወሲባዊ ጥቃት በመሸፋፈን ለተፈረደበት ግለሰብ ምህረት ያደረጉት የሃንጋሪዋ ፕሬዝዳንት በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ሥርጭት ሥልጣናቸውን ለቀቁ።

ፕሬዝዳንት ካትሊን ኖቫክ በመንግሥት የሚተዳደር የህጻናት ማሳደጊያ ኃላፊ ላይ የቀረበን የወሲባዊ ጥቃት ክስ፤ እንዲዳፈን ልጆችን አስገድዷል ለተባለው ግለሰብ ይቅርታ ማድረጋቸው የታወቀው ባለፈው ሳምንት ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ሃንጋሪያውያን ፕሬዝዳንቷ ሥልጣን እንዲለቁ የሚያቀርቡት ጥሪ እየበረታ በመምጣቱ ነው ከኃላፊነታቸው የለቀቁት።

ፕሬዝዳንቷ በቴሌቪዥን ቀርበው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት ጊዜ፣ ለግለሰቡ ምህረት ማድረጋቸው “ስህተት” መሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ይቅርታውን ያጸደቁት የቀድሞዋ የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር ጁዲ ቫርጋም የሃንጋሪ ገዢ ፓርቲ ለአውሮፓ ኅብረት ምርጫ የሚያደርገውን ዘመቻ ከሚመሩበት ኃላፊነት ተነስተዋል።

ውዝግቡ የተከሰተው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ በሃንጋሪ ከሚያደርጉት ጉብኝት ጋር በተያያዘ ምህረት የተደረጋላቸው 25 ሰዎች ስም ዝርዝር በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሳምንት ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።

ከእነዚህም መካከል በዋና ከተማዋ አቅራቢያ የሚገኝ የልጆች ማሳደጊያ ማዕከል ኃላፊ ላይ የቀረበውን የወሲባዊ ጥቃት ክስ እንዲያነሱ ልጆች ላይ ጫና በማሳደሩ የሦስት ዓመት እስር የተፈረደበት የማሳደጊያው ምክትል ኃላፊ ይገኝበታል።

ፕሬዝዳንት ካትሊን ኖቫክ ሥልጣን መልቀቃቸውን በቴሌቪዥን ቀርበው ሲያሳውቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ካትሊን ኖቫክ ሥልጣን መልቀቃቸውን በቴሌቪዥን ቀርበው ሲያሳውቁ

በመንግሥት በሚተዳደረው የህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰው የማሳደጊያው ኃላፊ የስምንት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ምክትል ኃላፊው በፕሬዝዳንቷ ይቅርታ እንደተደረገለት ከታወቀ በኋላ የሃንጋሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ተቃዋሚዎች ሥልጣን እንዲለቁ ሲጠይቁ ቢቆዩም፣ የፕሬዝዳንት ኖቫክ ውሳኔ ግን ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ነው።

ፕሬዝዳንቷ የገዢው ፓርቲ ታዋቂ ፖለቲከኛ ሲሆኑ፣ በወንዶች የበላይነት በተያዘው የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው የወጡ ሴት ናቸው። ኖቫክ የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁልፍ አጋር ከመሆናቸው በተጨማሪ ቀደም ሲል የቤተሰብ ሚኒስትር ነበሩ።

ፕሬዝዳንቷ የመጀመሪያዋ የሃንጋሪ ሴት ፕሬዝዳንት በመሆን ወሳኝ ሥልጣን የሌለውን ኃላፊነት የያዙት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በፕሬዝዳንቷ ላይ የቀረበው ተቃውሞ እና ሥልጣን መልቀቅ ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ ባለው እና ባህላዊውን የቤተሰባዊ ዕሴቶችን የማኅበራዊ ፖሊሲው ዋና ማዕዘን ባደረገው ገዢው ፓርቲ ላይ ጫና ይኖረዋል ተብሏል።

ፕሬዝዳንቷ ሥልጣን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት ንግግራቸው ምህረት እንዲደረግለት የወሰኑለት ግለሰብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ልጆች በእሱ የቀጥታ ጥበቃ ስር ያልበሩ በመሆናቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች “ከጎናችሁ እንዳልቆምኩ ተሰምቷችሁ ሊሆን ይችላል” በማለት ስህተት መሥራታቸውን በመግለጽ ፕሬዝዳንቷ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ከፕሬዝዳንቷ በተጨማሪ ይቅርታውን ያጸደቁት የፍትህ ሚኒስትሯ ኃላፊነታቻውን መልቀቃቸው በቪክቶር ኦርባን ለሚመራው ፓርቲ እና መንግሥት ሁለት ጉልህ ሴት ፖለቲከኞችን ማጣቱ ከባድ ጉዳት መሆኑ ተነግሯል።