ባይደን ከሰጡት ማረጋገጫ በተቃራኒ የአሜሪካ ባንኮች የአክሲዮን ድርሻ አሽቆለቆለ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ የፋይናንስ ስርዓት አይንገራገጭም የሚል ቃል ቢሰጡም ትናንት መጋቢት 4፣ 2015 ዓ.ም ሆኖ የታየው ግን በተቃራኒው ነው። ትናንት ሰኞ በአለም ዙሪያ የባንኮች የአክሲዮን ድርሻ ዝቅ ብሏል።

ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ብድር በማቅረብ የሚታወቀው ሲልከን ቫሊ ባንክ እንዲሁም ሲግኒቸር ባንክ ኪሳራ ያጋጠማቸው ሲሆን የደንበኞችን ተቀማጭ ገንዘብ ለመጠበቀ የአሜሪካ መንግሥት እርምጃ ወስዷል።

ጆባይደን የባንክ ስርዓቱ ለመጠበቅ “የሚያስፈልገው ሁሉ” ይደረጋል ሲሉ ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው የአክሲዮን ድርሻ ማሽቆልቆል ምክንያት የባንክ ባለድርሻዎች ሌሎችም ባንኮች ሊጎዱ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

ትናንት የስፔኑ ስታንዳርድ ባንክ እንዲሁም የጀርመኑ ኮሜርዝ ባንክ የአክሲዮን ድርሻቸው እስከ 10 በመቶ ዝቅ ብሎ ተመልክተዋል።

በርካታ የአሜሪካ አንሰተኛ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ከችግር የሚታደጉበት ወደ ገንዘብ ሊቀየር የሚችል ከበቂ በላይ ሃብት እንዳላቸው ቢገልጹም ከአውሮፓውያኑ መስል ተቋማት በከፋ ሁኔታ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።

ይህ ባንኮች ላይ ያጋጠመው ችግር የአሜሪካ ባንክ የአሜሪካ ግምዣ ቤት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የወለድ ምጣኔ ላይ የሚያደርገውን ጭማሪ እንዲገታ ሊያደርገው ይችላል የሚል ግምቶች እንዲበረክቱ አድርጓል።

መንግስት የተቀማጭ ገንዘብን ለመጠበቅ እርምጃ ከወሰደ በኃላ ፕሬዝዳንት ባይደን ሲልከን ቫሊ ባንክ ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ግለሰቦችም ይሁኑ የንግድ ተቋማት ከሰኞ ጀምሮ ማንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።

በርካታ የንግድ ተቋማት ባጋጠመው ችግር ገንዘባቸው መታገዱን ተከትሎ ለሰራተኞቻቸው እና አቅራቢዎች ገንዝብ መክፍል እስካለመቻል ደርሰው ነበር።

ቢቢሲ በሲልከን ቫሊ ባንክ ገንዘባቸውን ለማውጣት በካሊፎርኒያ የተሰለፉ ደንበኞችን ተመልክቷል።

ባንኩ በኢንተርኔት ገንዘብ የሚወጣበትን ስርዓት ማቆሙን ተከትሎ ደንበኞች ገንዘባቸውን በጥሬ ለማውጣት ተገደዋል።

ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ብድር በማቅረብ የሚታወቀው ሲልኮን ቫሊ ባንክ በአሜሪካ መንግሥት ተዘግቷል። ባለፈው አርብ ደግሞ ንብረቱ ተይዞ ነበር።

ለአሜሪካው ባንክ ይህ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት በ2008 ካጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ በኃላ የተከሰተ ትልቁ ኪሳራ ነው።

ባንኩ ንብረቶቹን በመሸጥ በከፍተኛ ወለድ ምክንያት ያጋጠመውን ኪሳራ ለመቋቋም ሲሞክርም ነበር። ያጋጠመው ችግር ደንበኞች ገንዘባቸው ለማውጣት እንዲጣደፉ ምክንያት ሆኗል። ይህም ባንኩን ለገንዘብ ቀውስ ዳርጎታል።