ሻክሮ ለቆየው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት ምን ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በመልካም ሁኔታ የቆየው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ንፋስ ገብቶታል።
በተለያዩ መስኮች ከአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍን ከሚያገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ምንም እንኳን በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን በሕዳሴው ግድብ የተነሳ ግንኙነቷ ላይ ጥላ አጥልቶበት የነበረ ቢሆንም፣ የትግራዩ ጦርነት ግን በበርካታ መስኩ የሁለቱን አገራት ግንኙነት አበላሽቶታል።
በተለይ ጦርነቱ ተባብሶ የኤርትራ ሠራዊት መሳተፉ እና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ አሜሪካ በይፋ ተቃውሞ እንድታሰማ አድርጓታል።
ከዚህ አለፍ ሲልም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ የመጀመሪያ የሚባለውን እርምጃ ወስዳለች።
በዚህም በጦርነቱ መባባስ እና በመብት ጥሰቶች ውስጥ እጃቸው ያለ ግለሰቦች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አግዳለች።
በማስከተልም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱ እንዲባባስ እና የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መስከረም 07/2014 ዓ.ም. መፈረማቸው ይታወሳል።
ከዚያም በኋላ ከቀረጥ እና ከታሪፍ ነጻ በሆነ መንገድ የተለያዩ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ከሚያስገቡ አገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትወጣ በማድረግ እርምጃ ወስዳለች።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአፍሪካ ቀንድን ሰላም ያናጋል የተባለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿን በልዩ መልዕክተኛነት በመሰየም ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከአሜሪካ በኩል የሚደረግበት ጫና ተገቢ ያልሆነ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው ሲል አጥብቆ ሲቃወመው ቆይቷል።
የጦርነቱ ጥላ
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካስከተለው ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ እና ከሌሎች የምዕራብ አገራት ጋር በነበራት ግንኙነት ላይ ጥላውን አጥልቶበት ቆይቷል።
በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት በኋላም፣ እስካሁን ይፋ ባልሆነ ምክንያት አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ትልቁ የሆነውን ኤምባሲዋን ይመሩት የነበሩት አምባሳደር ተነስተው አሁን ድረስ በጉዳይ ፈጻሚ እየተመራ ይገኛል።
ከዚህ ባሻገር በወቅታዊ የጦርነቱ እና የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ የአፍሪካ ክፍል ባልደረቦች ውጪ፣ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች በተደጋጋሚ ተመላልሰዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጋብ ብሎ ለወራት ቆይቶ የነበረው ጦርነት መልሶ ባገረሸበት ወቅት አሜሪካ በልዩ መልዕክተኛዋ በአምባሳደር ማይክ ሐመር በኩል ጦርነቱን ለማስቆም ጠንካራ ጥረት አድርጋለች።
ይህም ጥረት ኋላ ላይ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ወሳኝ እንደነበር ይነገራል።
ቀደም ካሉት ሁለት ዓመታት በተለየ 2015 ላይ አሜሪካ በከፍተኛ ባለሥልጣኗ በኩል ከኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ጋር በመገናኘት ውይይት አድርጋለች።
ከዚህ አንጻር የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ቀዳሚው ናቸው። ብሊንከን ቀደም ባሉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ጦርነት በተለይ ከጎረቤት ኬንያ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጋር መነጋገራቸው ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል።
ደም አፋሳሹን ጦርነት በንግግር ለማብቃት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ደቡብ አፍሪካ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች ተገናኝተው ውይይት እያካሄዱ በነበሩበት ጊዜ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መወያየታቸው ተነግሯል።
ይህም ጦርነቱ ከተባባሰ በኋላ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ መሪ ጋር በይፋ ሲነጋገር የመጀመሪያው ነበር።
በዚህም ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. በተደረገው ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ብሊንከን ጦርነቱ በአስቸኳይ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, @REDWANHUSSIEN
የከፍተኛ ባለሥልጣናት ንግግር
ከአፍሪካ ኅብረት ባሻገር አሜሪካ ከፍተኛ ሚና ነበራት የተባለው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ጦርነቱ በተጀመረበት ሁለተኛ ዓመት ዕለት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ላይ ተፈረመ።
ስምምነት ከተደረሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ ኅዳር 14/2015 ዓ.ም. የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የተደረሰው ስምምነት በአስቸኳይ ተግባራዊ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸው አሳውቋል።
በተከታይነት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሜሪካ - አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ በተጓዙበት ወቅት ታኅሣሥ 05/2015 ዓ.ም. ከውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ጋር በአካል ተገናኝተው ተወያይተው ነበር።
በዚህ ውይይት ላይም ዋና አጀንዳ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ሂደት እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ሙሉ ለሙሉ ለቀው በሚወጡበት ሁኔታ ላይ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር እንዲሁም ከፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ጋር ተወያይተዋል።
ምንም እንኳን በዚህ ወቅት በምን ጉዳይ ላይ እንደተነጋገሩ ይፋ ባይደረግም፣ በትግራይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አንድ አጀንዳ እንደሚሆን ይታመናል።
ጥር 13/2015 ዓ.ም. ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በውጭ ጉዳይ ኃላፊው ብሊንከን መካከል ውይይት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ዋነኛ ጉዳይ የነበረው ጦርነት ባስቆመው ስምምነት ትግበራ ላይ ነበር። በስምምነቱ መሠረት ጉልህ እርምጃዎች መወሰዳቸው እና የኤርትራ ወታደሮችም መውጣት መጀመራቸው ተጠቅሷል።
ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ ብሊንከን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ የቆየው የጦርነቱ ማብቃት እና የስምምነቱ ተግባራዊነት ነው።
ነገ ረቡዕ መጋቢት 06/2015 ዓ.ም. ብሊንከን በአዲስ አበባ ያደርጉታል ተብሎ በሚጠበቀው ጉብኝት ወቅት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ለማስቆም የተደረሰው ስምምነት አተገባበር እና የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።
በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት ብሊንከን አዲስ አበባ ላይ የትግራይ ክልል ባለሥልጣናትን አግኝተው እንደሚነጋገሩ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ሞሊ ፊ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, @ABIYAHMEDALI
የብሊንከን የአዲስ አበባ ጉዞ
በጦርነቱ ምክንያት ተበላሽቶ የነበረው የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ግንኙነት ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ ለማስተካከል ወደሚችልበት አቅጣጫ እያመራ መሆኑን በከፍተኛ ባለሥልጣናት በኩል ባለፉት ወራት የሚደረጉት ግንኙነት ያመለክታሉ።
ነገር ግን ይህ የተባላሸውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ተመልሷል ለማለት ገና ብዙ እንደሚቀር እና ለዚህም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ ፍላጎት እንዳላት ሞሊ ፊ ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በአካባቢው ካላት ተጽእኖ እና ልትጫወት ከምትችለው ሚና አንጻር አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲስተካከል የጎላ ፍላጎት እንዳላት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ፎሬን ፖሊሲ የተባለው መጽሔትም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታሻሽል ግፊት እያደረጉ መሆናቸውን ዘግቧል።
የሩሲያ እና የቻይና ተጽእኖ እየተስፋፋባት ባለችው የአፍሪካ አህጉር ውስጥ አሜሪካ ያላትን ሚና እንዳትነጠቅ አስፈላጊውን የመቀራረብ እርምጃ መውሰድ እንዳለባት ባለሥልጣናቱ ይከራከራሉ።
ይህ የአንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት ካለፈው ነሐሴ ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የብሊንከን ጉብኝት ለኢትዮጵያ በጦርነቱ የተዳከመውን ምጣኔ ሃብቷን ለመጠገን የገንዘብ ድጋፍ እና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በኩል የሚያስፈልጓትን ነገሮች ለማግኘት በር ሊከፍትላት ይችላል።
ከእዚህም መካከል ከእራሷ ከአሜሪካ እና ከፍተኛ ተደማጭነት ካላት ዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር፣ ያለባትን የዕዳ ክፍያ ጊዜ ማሸጋሸግ፣ በጦርነቱ መዘዝ የተነፈገቻቸውን እርዳታዎች እና የበጀት ድጎማዎችን እንዲሁም ወደ አጎዋ የቀረጥ እና ታሪፍ ነጻ ንግድ መመለስን ያካተታሉ።
ነገር ግን አሁንም ድረስ መቋጫ ያላገኘው በጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ እና የተጠያቂነት ሁኔታ በሁለቱ አገራት የግንኙነት ማሻሻል ሂደት ውስጥ የሚኖረው ተጽእኖ አልለየም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ አንጻር የተፈጸሙ በደሎችን በሽግግር ፍትሕ ሂደት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ደግሞ ተጠያቂነት እንዲቀድም ግፊት እያደረገ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከንም በአዲስ አበባው ጉብኝታቸው ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
ብሊንከን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በሚኖራቸው ውይይት የሰብዓዊ መብቶች እና የወንጀል ተጠያቂነት ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አምነስቲ ጠይቋል።












