ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን የአረብ ሊግ ቋሚ አጀንዳ አስደረገች፤ ኢትዮጵያ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Arab League
ከአስር ዓመታት በላይ ሲያወዛግብ የቆየውን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ግብፅ የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ አስደረገች።
ይህ የሆነው የአረብ ሊግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት 159ኛው ስብሰባ በግብፅ ፕሬዝዳንትነት በካይሮ በተካሄደበት ወቅት ነው።
ይህንን የአረብ ሊግ ውሳኔን ተከትሎ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የተቃወመችው ሲሆን፣ የአባይ ጉዳይ በአገራቱ መካከል በሚካሄድ ውይይት የሚፈታ መሆኑን በመጥቀስ የሊጉን ውሳኔ ተቃውማለች።
የምክር ቤቱን ፕሬዝዳንትነት ከሊቢያ ተወካይ የተረከቡት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹኩሪ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአረብ ሊግ ምክር ቤት ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን አስወስነዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የግድቡ ጉዳይ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን መወሰኑ የአረብ ሊግ የግብፅ እና የሱዳን መብቶችን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግድብ ጉዳይ 140 ሚሊዮን አረብ አገራት ዜጎችን የሚመለከት ስለሆነ የአረብ ሊግ አጀንዳ ይሆናል ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ።
ሽኩሪ አያይዘውም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአረብ ሊግ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ የግብፅ እና የሱዳንን ፍላጎት በመቀበል አውንታዊ እርምጃ እንድትወስድ የሚያሳስብ ነው ብለዋል።
ሽኩሪ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር አሳሪ የሆነ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳትደርስ በግድቡ ግንባታ፣ ሙሌት እና ኦፕሬሽን ቀጥላበታለች ሲሉ ከሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሞላል እና ኦፕሬሽን በተመለከተ የአረብ ሊግ የውሳኔ ሃሳብ በማውጣቱ ደስተኛ አይደለሁም ብሏል።
የግደቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን እንዲሁም የአባይ ወንዝ አስተዳደር እና አጠቃቀም ለሚመለከታቸው የአፍሪካ አገራት መተው ያለበት ጉዳይ ነው ያለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ የአባይ ወንዝ እና የተፋሰሱ አገራት መገኛቸው አፍሪካ ስለመሆኑ ለሊጉ ማስታወስ አይኖርብንም ብሏል።
መሠረታዊ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ችላ በማለት የአረብ ሊግ ለአንድ አገር ብቻ ቃል አቀባይ ሆኖ እያገለገለ ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ለጉዳዩ ፖለቲካዊ ገጽታ ማስያዝ መፍትሄ አይሆንም ብሏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በግድቡ ዙሪያ ድርድር ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አስታውሶ፣ የአረብ ሊግ የውሳኔ ሃሳብ ማውጣቱ ግብፅ በድርድሩ በቅን ልቦና ውስጥ ሆና ስትሳተፍ ስለመቆየቷ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE/TWITTER
ግብፅ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን በመጠቀም የአረብ ሊግ አገራት እና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በኩል ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ስትጥር ቆይታለች።
ቀደም ሲል ግብፅ እና ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባል በሆነችው ቱኒዚያ አማካይነት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከማካሄዷ በፊት በግደቡ ዙሪያ ስምምነት ለመድረስ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንድትደራደር ደብዳቤ እንዲጻፍ አድርገው ነበር።
110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ግብፅ፤ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ የውሃ ድርሻዬን ይቀንሳል የሚል ስጋት አላት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሕዝቦቿ 55 በመቶ የኤሌክትሪ ኃይል እንደማያገኙ በማስታወስ፤ ሁሉን ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ ላይ በመመርኮዝ ግድቡን በመገንባት የውሃ ደርሻዬን የመጠቀም መብት አለኝ ትላለች።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከ10 ዓመታት በፊት ጀምሮ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ከስምምነት ለመድረስ በርካታ ድርድሮችን ቢያደርጉም ይህ ነው የተባለ ውጤት አልተመዘገበም።
ከጥቂት ወራት በፊት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 83 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም መጠናቀቁን ይፋ ተደርጎ ነበር።
ግድቡ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች አማይካይነት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራ ጀምሯል።












