እስራኤል "መሣሪያዎች በፅንፈኞች እጅ እንዳይወድቁ" በመላው ሶሪያ የአየር ድብደባ እየፈጸመች ነው

ደማስቆ፤ ሶሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል የበሻር አል-አሳድን መውደቅ ተከትሎ የኬሚካል እና ሌሎች ስትራቴጅክ የጦር መሳሪያዎችን ለማውደም በሚል የአየር ጥቃት እየፈጸመች ነው።

እስራኤል የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የአየር ጥቃት መፈጸሟን ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ አንድ የሰብዓዊ መብት ተቋም እንደገለጸው እስራኤል በመላው ሶሪያ ከ100 በላይ ወታደራዊ ኢላማዎችን ደብድባለች።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ኢላማ ከተደረጉት የወታደራዊ ይዞታዎች መካከል የኬሚካል መሳሪያ ማከማቻዎች ዋነኞቹ ናቸው።

እስራኤል ጥቃቱን የምትፈጽመው መሳሪያዎቹ በጽንፈኞች እጅ እንዳይወድቁ ለመከላከል መሆኑን ገልጻለች።

የአሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ የመንግሥታቱ በሶሪያ ጉዳይ የሚመክር ስብሰባ አድርጓል። በቀጣዮቹ ቀናትም መግለጫ እንደሚያወጣ ገልጿል።

እስራኤል የአየር ድብደባውን የፈጸመችው የተባበሩት መንግሥታት የኬሚካል መሣሪያዎች ሁኔታ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ለሶሪያ ኃይሎች ባስጠነቀቀበት ወቅት ነው።

እነዚህ መሣሪያዎች በማንኛውም ተፈጥሯዊ በሆነ አካል ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት አደገኛ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ መሰረት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተከለከሉ ናቸው።

ሶሪያ ምን ያክል እና የት የኬሚካል መሳሪያ እንዳላት ግልጽ አይደለም። ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻር አል-አሳድ የኬሚካል መሳሪያ ክምችት እንደነበራቸው ይታመናል።

የኬሚካል መሳሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ ሶሪያ በ2013 (እአአ) ስምምነት ፈርማለች። ነገር ግን ከአንድ ወር በኋላ በደማስቆ ጫፍ አካባቢ መሳሪያው ጥቅም ላይ ውሏል። ይህም ከአንድ ሺህ አራት መቶ በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።

በወቅቱ የታዩት ዘግናኝ ምስሎች የብዙ ሰዎችን ስሜት የሚረብሹ ነበሩ። ምዕራባውያን ድርጊቱን የፈጸመው አሳድ ነው ቢሉም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግን ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

በሶሪያ ከ1 ሺህ 3 መቶ ቶን በላይ የኬሚካል መሳሪያ በመንግሥታቱ ድርጅት አማካኝነት መክኗል ቢባልም አሁንም በአገሪቱ የኬሚካል መሳሪያ ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

ቢቢሲ ከስድስት ዓመታት በፊት ባደረገው ምርመራ መሰረት በሶሪያ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ብቻ 106 የኬሚካል መሳሪያ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል ከአየር ድብደባው በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት ወታደራዊ ነጻ ቀጠና ወዳደረገው የጎላን ተራራ አካባቢዎች ወታደሮቿ ዘልቀው መግባታቸውን የሚያሳይ ምስል አጋርታለች።

የጎላን ተራሮች ከደማስቆ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 60 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ የሚገኝ አለታማ ስፍራ ነው።

እስራኤል ይህን አካባቢ በ1967 በተደረገው የስድስት ቀን ጦርነት መገባደጃ አካባቢ የያዘችው ሲሆን በብቸኝነት የያዘችው ደግሞ በ1981 ነው።

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር በሰጡት መግለጫ አካባቢዎቹን የሚቆጣጠሩት ለደኅንነት ጉዳይ ሲሆን የጊዜ ገደቡም ለተወሰነ ጊዜ እንደሚሆን ገልጸዋል።

እስራኤል በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት እና ይህኛው እርምጃ ግን የዜጎቿን ደኅንነት ለመጠበቅ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁንና መከላከያ ሚንስትሩ እስራኤል ሶሪያ ውስጥ የአየር መቃወሚያ፣ ሚሳኤል እና ሌሎች ስትራቴጅክ መሣሪያዎችን የማውደም ሥራዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

አገሪቱን የተቆጣጠረው የሃያት ታሂር አል ሻም ቡድን በቀጣዮቹ ቀናት ሶሪያውያንን ለከፍተኛ ግርፋት የዳረጉ ከፍተኛ የቀድሞው ስርዓት ሹማምንትን ስም ዝርዝር ይፋ አደርጋለሁ ብሏል።

የእነዚህን ሰዎች መረጃ ለሚያጋሩ ግለሰቦችም ሽልማት አበረክታለሁ ብሏል።

የአሳድ መንግሥት ከሄዝቦላህ እና ሩስያ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግለት ነበር። ይሁንና ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ እንዲሁም ሩስያ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ዩክሬን ስታደርግ የአሳድ መንግሥት ብቻውን ቀረ። ይህንን የተመለከቱት የሶሪያ አማጺያን ኃይላቸውን አደራጅተው በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አንኮታኮቱት።

ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ የአሳድ ስርዓት መውደቁ "ለመካከለኛው ምስራቅ ታሪካዊ ቀን ነው" ብለውታል።