ቻይና ሁለት ዜጎቿ ለዩኬ ሲሰልሉ ደረስኩባቸው አለች

የቻይና ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ዜጎቼ የሆኑ ጥንዶችን በሰላይነት ቀጥራ ስትሰልለኝ ነበር ስትል ዩናይትድ ኪንግደምን ከሰሰች።

የቻይና የደኅንነት ሚኒስቴር በዊቻት ይፋዊ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ የዩኬ የስለላ ድርጅት የሆነው ኤምአይ6 ዋንግ እና ዙ የተባሉ ባል እና ሚስቶችን ሰላይ አድርጎ ቀጥሯል ብሏል።

መግለጫው እንዳለው ሁለቱ ጥንዶች ጥብቅ ሚስጢር ባለበት የቻይና መንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ሰርተዋል።

የቻይና የደኅንነት ሚኒስቴር ኤምአይ6 ዋንግ የተባለውን ግለሰብ የምቅጠር እንቅስቃሴውን የጀመረው እአአ 2015 ላይ ዋንጋ በዩኬ ተማሪ ሳለ ነበር ብሏል።

በዩኬ ሳለ የኤምአይ6 ሰዎች “ፍላጎቱን እና ድክመቱን ለመረዳት” እራት እየጋበዙት እና ሽርሽር እየወሰዱት “በእንክብካቤ ይዘውታል” ብሏል።

“ለገንዘብ ያለውን ጥልቅ ፍቅር” በመረዳት የኤምአይ6 ባልደረቦች የቅርብ ጓደኛ አድርገው “በክፍያ የማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ” አድርገውታል ይላል መግለጫው።

የቻይና መንግሥት ሁለቱ ጠንዶች ከዩኬ የስለላ ተቋም ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጥልቅ ምርመራ እንደደረሰበት ገልጿል።

ከጊዜ በኋላ የኤምአይ6 ባልደረቦች ዋንግ የተሻለ ጥቅም እና የደኅንነት ጥበቃ እንዲያገኝ ለብሪታኒያ መንግሥት እንዲሰራ ጠይቀውታል።

ኤምአይ6 በዋንግ አማካይነት ዙ የተባችውን ሴት መቅጠሩም ተመልክቷል።

“ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ዋንግ የኤምአይ6 ጥያቄን ለመቀበል ፍላጎት ባያሳይም ተደጋጋሚ ጥያቄ፣ በውትወታ፣ በመደለል እንዳንዴም በማስፈራሪያ ፍቃደኛ ሆኗል” ይላል ዊቻት ላይ የወጣው ይፋዊ መግለጫ።

የቻይና መንግሥት በጥንዶቹ ላይ እያደረገውን ያለውን ምርመራ አለማጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን የሚቀርብባቸው ክስ ምን ሊሆን እንደሚችል ግለጽ አልተደረገም።

የሁለቱን ጥንዶች በተመለከተ እስካሁን ድረስ የዩኬ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምዕራባውያን አገራት እና ቻይና በስላላ ወንጀሎች አንዳቸው ሌላኛቸው ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይተዋል።