ቱርክ የኩርድ ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶችን ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ ፈጸመች

የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰራጨው የተዋጊ አውሮፕላን ምስል

የፎቶው ባለመብት, TURKISH DEFENCE MINISTRY

የምስሉ መግለጫ, የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰራጨው የተዋጊ አውሮፕላን ምስል

ባለፈው ሳምንት ኢስታንቡል ውስጥ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት ለመበቀል ቱርክ በጎረቤት አገሮች ውስጥ በሚገኙ የኩርድ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች።

የቱርክ አየር ኃይል በጥቃቱ ኢላማ ያደረጋቸው ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ፣ በአገሪቱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መነሻ ናቸው የተባሉ የኩርድ ታጣቂዎች ሰፈሮች መሆናቸውን የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

የሶሪያ ኩርዶች ቃል አቀባይ ግን በአየር ጥቃቱ በርካታ ሕዝብ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው ሁለት መንደሮች ተመትተዋል ብሏል።

የቱርክ መንግሥት ኢስታምቡል ውስጥ ተፈጽሞ ለበርካቶች ሞትና መጎዳት ምክንያት የሆነውን የቦምብ ጥቃት፣ አገሪቱ ሕገወጥ ያደረገችው ፒኬኬ የተባለው ቡድን እንደፈጸመው ይከሳል። የኩርድ ታጣቂ ቡድን ግን በጥቃቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት ያስተባብላል።

የአየር ጥቃቱ በተጀመረበት ጊዜ የቱርክ የመከላከያ ሚኒስቴር ተዋጊ አውሮፕላኖች ሲነሱ እና ፍንዳታን ከሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጋር “ዋጋ የሚከፈልበት ጊዜ” ደርሷል ከሚል ጽሁፍ ጋር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

በጥቃቱ “የሽብርተኞች መጠለያዎች፣ ምሽጎች፣ ዋሻዎች፣ መተላለፊያዎች እና ማከማቻዎች በተሳካ ሁኔታ ወድመዋል” ሲሉ የቱርክ መከላከያ ሚኒስትር ሁሉስ አካር ተናግረዋል።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴርም እንዳሳወቀው፣ በሰሜናዊ ሶሪያ እና በሰሜናዊ ኢራቅ ውስጥ በሚገኙ የኩርድ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች 89 ኢላማዎች ወድመዋል ብሏል።

ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ በቱርኮች የሚመሩ ኃይሎች እንዳሉት በጥቃቱ ኮባኔ የተባለችው ከተማ እና ሁለት በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው መንደሮች ተመትተዋል። ይህንንም ጥቃት እንደሚበቀሉት ዝተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትናንት እሁድ ከሰዓት በኋላ ከሶሪያ በኩል ወደ ቱርክ ድንበር ሮኬት ተተኩሶ ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውንም የቱርክ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ተከታታይ ቡድን እንዳለው፣ በሰሜናዊ ሶሪያ ውስጥ ቢያንስ 31 ሰዎች ተገድለዋል።

በቱርክ የአየር ጥቃት ኢራቅ ውስጥ የትኞቹ ኢላማዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ይህ የቱርክ የአየር ጥቃት የተካሄደው ከሳምንት በፊት በኢስታምቡል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሕዝብ በሚበዛበት ጎዳና ላይ የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ነው። በጥቃቱ ስድስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ80 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶናቸዋል።

የቱርክ ባለሥልጣናት ለጥቃቱ የኩርዶች ታጣቂ ቡድን የሆነውን ፒኬኬን ተጠያቂ አድርገውታል። ቡድኑን ቱርክ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ በሽብርተኛነት ይመለከቱታል።

ነገር ግን ፒኬኬ “ሰላማዊ ሰዎችን በቀጥታ ኢላማ እንደማያደርግ” በመግለጽ፣ የቦምብ ጥቃቱን እንዳልፈጸመ አስተባብሏል።

የቱርክ ባለሥልጣናት ከቦምብ ጥቃቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ቦምቡን ያጠመደች ናት የተባለች ሶሪያዊት ሴት ትገኝበታለች።

ግለሰቧ ከመያዟ በፊት የቱርክ ፍትሕ ሚኒስትር እንደተናገሩት፣ ቦምቡ የፈነዳው ሴትየዋ ለ40 ደቂቃ ያህል ተቀምጣበት ከነበረው መቀመጫ አቅራቢያ ከነበረ ቦርሳ ነው ብለው ነበር።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከቦምብ ጥቃቱ ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ቡልጋሪያ ውስጥ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የኩርድ ታጣቂዎች በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ ውስጥ የኩርዶችን የእራስ ገዝ አስተዳደር ለመመስረት ለአስርት ዓመታት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ባለፉት ዓመታት ቱርክ በቡድኑ በግዛቷ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በሰሜን ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኩርድ ቡድኖችን ኢላማ ያደረጉ ድርንበር ተሻጋሪ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ስታካሂድ ቆይታለች።