ሙሴ አሥርቱ ትዕዛዛትን 'በተቀበለባት' የሲና ተራራ ላይ ቅንጡ ሪዞርት መገንባት የፈጠረው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Universal Images Group via Getty Images
ሙሴ አሥርቱ ትዕዛዛትን ተቀብሎባታል የምትባለው የሲና ተራራ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን በእስልምናም ሆነ በአይሁዳውያን እምነት ዘንድ የተቀደሰች ስፍራ ናት።
በግብፅ የምትገኘው ይህች የተቀደሰች ስፍራ በአገሬው ነዋሪ ዘንድ 'ጃባል ሙሳ' ተብላ ትጠራለች ።
ስፍራዋ አምላክ መለኮታዊ ኃይልን ገልጦ ሙሴን ያነጋገረበት እንደሆነች ይገለጻል።
ሙሴን ሲያነጋግረውም ቁጥቋጦው በእሳት ይንቦገቦግ እንደነበር በቅዱሳኑ መጻሕፍት፤ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርዓን ተጠቅሷል።
በርካታ ጎብኚዎች ለዓመታት ይህችን ቅዱስ ተራራ ለመጎብኘት ይተሙ ነበር።
በስፍራው ሲደርሱ የአካባቢው ጥንታዊ ማኅበረሰብ፣ ቤዶዊኖች የተራራዋን መልክዓ ምድር አስደናቂነት ያስጎበኛሉ።
ይህች በሦስቱ የአብርሃም እምነት ዘንድ ቅዱስ ተብላ በምትጠራው ስፍራ ላይ የግብፅ መንግሥት ትልቅ ቅንጡ ሪዞርት ለመገንባት እና አካባቢውን አዲስ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ዕቅድ ውዝግብ አስነስቷል።
በስፍራው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባች የቅድስት ካትሪን ገዳም አለች።
ይህችን ገዳም የምታስተዳድረው የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናት።
የግሪክ ጫናን ተከትሎ የግብፅ ባለሥልጣናት ገዳሟን ለመዝጋት የነበራቸውን ሃሳብ በመቀልበሳቸው መነኮሳቱ በስፍራው ይቆያሉ ተብሏል።
ለረጅም ጊዜ ተገልላ የቆየችው ይህች በረሃማ ስፍራ ላይ የምትገኘው ገዳም፣ ተራራ እና ከተማን የምታቅፍ ሲሆን፣ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግባለች።
እናም በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉት ቅንጡ ሆቴሎች፣ ቪላ ቤቶች እና የመገበያያ መደብሮች የታሪክ አሻራውን ሊያጠፋው ይችላል የሚል ስጋትን ጭሯል።
በተጨማሪም ጥንታዊው የቤዶዊን ማኅበረሰብ ወይም የጀበሌያ ጎሳ መገኛም ነው።
የቅድስት ካትሪን ጠባቂ የሚባሉት እነዚህ ጎሳዎች መኖሪያ ቤታቸው እንዲሁም የቱሪስት ካምፖቻቸውን በአነስተኛ ወይም ያለምንም ካሳ እንዲፈርሱ ተደርገዋል።
በተጨማሪም በስፍራው ለሚገነባው አዲስ የመኪና ማቆሚያ መቃብሮቻቸውን ቆፍረው የቤተሰቦቻቸውንና የወዳጆቻቸውን አጽሞች እንዲያወጡ ተገድደዋል።

ይህ ፕሮጀክት ቱሪዝምን ለማጎልበት አስፈላጊ ዘላቂ ልማት በሚል ቢቀርብም በቤዶዊን ማኅበረሰብ ላይ ሳይፈልጉ እንደተጫነባቸው ከሲና ጎሳዎች ጋር በቅርበት የሠራው ብሪታንያዊው ፀሐፊ ቤን ሆፍለር ይናገራል።
ማኅበረሰቡ ይህንን ፕሮጀክት እንደ ልማት እንደማያየው እና የእነሱን ፍላጎት መስዋዕት በማድረግ በበለጠ ለውጭ ጎብኚዎች ቅድሚያ የሰጠ ነው ሲሉ ፀሐፊው ይተቻሉ።
"በማኅበረሰቡ ዙሪያ አዲስ ዓለም እየተገነባ ነው። ከዚህ ዓለም ራሳቸውን ለማራቅ መርጠው ነው የሚኖሩት። ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታም ፈቃዳቸውን አልሰጡም፤ ኑሯቸውንም ከስር መሠረቱ የሚቀይር ነው" ሲሉ ጸሐፊው ይወቅሳሉ።
ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች እየመጣ ስላለው ለውጥ በቀጥታ ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም።
ግሪክ ከገዳሙ ጋር ባላት ግንኙነት ምክንያት ፕሮጀክቱን በቀጥታ ከተቹት የውጭ አገራት መካከል ዋነኛዋ ሆናለች።
በዓለማችን ላይ ጥንታዊ ከሚባሉት ገዳሞች አንዷ የሆነችው ቅድስት ካትሪን በመንግሥት መሬት ላይ ነው የምትገኘው የሚል ውሳኔ የግብፅ ፍርድ ቤት ግንቦት ላይ መወሰኑን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ውጥረት ተከስቷል።
ከአሥርት ዓመታት ውዘግብ በኋላ ገዳሟ ያረፈችበትን መሬት እንዲሁም የአርኪዮሎጂ ሃይማኖታዊ ስፍራዎችን "ብቻ ነው መጠቀም" የምትችለው ብሏል።
የግሪክ ሊቀ ጳጳስ ኢሮኒሚስ 2ኛ ይህንን ውሳኔ በፍጥነት አውግዘውታል።
"የገዳሟ ንብረት እየታገደ እንዲሁም እየተዘረፈ ነው። ይህች የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ብርሃን በአሁኑ ወቅት የኅልውና ስጋት ውስጥ ገብታለች" ብለዋል።
የቅድስት ካትሪን የረዥም ጊዜ ሊቀ ጳጳስ ዳሚያኖስ ባልተለመደ መልኩ ከግሪክ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ውሳኔው ለቤተክርስቲያናችን ከባድ ጉዳት እንዲሁም አስነዋሪ ነው" ብለዋል።
ከገዳሟ ውዝግብ ጋር ተያይዞም ሊቀ ጳጳሱ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውም ተገልጿል።
ገዳሟን በበላይነት የሚያስተዳድረው በኢየሩሳሌም የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ገዳሟ የጥበቃ ደብዳቤ ከነብዩ መሐመድ እንደተሰጣት አክሏል።
አወዛጋቢው የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳለ ሆኖ አገራቱ ባደረጉት የዲፕሎማሲያዊ ድርድር የቅድስት ካትሪን ገዳም የግሪክ ኦርቶዶክስ ማንነነትን በጠበቀ መልኩ እንዲሁም ቅርሷም እንዲጠበቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ben Hoffler
ልዩ ስጦታ ወይስ ጣልቃ ገብነት?
ግብፅ በመንግሥት የሚደገፈውን ቱሪስቶችን ማዕከል ያደረገውን ታላቁን የለውጥ ፕሮጀክት የጀመረችው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው።
ዕቅዱ ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ ትልቅ የጎብኚ ማዕከል፣ በአቅራቢያው ያለውን አየር ማረፊያ ማስፋፋትን ጨምሮ በሙሴ ተራራ ላይ በገመድ ላይ የሚንሸራተት መጓጓዣ መግጠምን ያካትታል።
መንግሥት ይህንን ፕሮጀክቱን "ግብፅ ለመላው ዓለም እንዲሁም ለሁሉም ሃይማኖቶች የምታደርገው ስጦታ ነው" በሚል ነው እያስተዋወቀው ያለው።
"ፕሮጀክቱ ለጎብኚዎች ሁሉንም የቱሪዝም እና የመዝናኛ አገልግሎቶችን ያቀርባል። ቅድስት ካትሪን የምትገኝበትን ከተማም የአካባቢውን ተፈጥሮ፣ ዕይታ እና ቅርስን በመጠበቅ ልማት ማካሄድ የሚል ዕቅድ ይዟል" ሲሉ የቤቶች ጥበቃ ሚኒስትር ሸሪፍ ኤል ሸርቢኒ ባለፈው ዓመት ተናግረዋል።
በገንዘብ እጥረት ምክንያት ግንባታው ለጊዜው የቆመ ቢመስልም እስካሁን በተሠሩ የግንባታ ሥራዎች የአካባቢው ገጽታ እየተቀየረ ይገኛል።
በተለይም በገዳሟ ትይዩ ያለው የኤል ራሃ ሜዳ ተቀይሯል።
ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እያለ ተከታዮቹ የጠበቁበት ስፍራ ነው።
ተቺዎች ደግሞ የስፍራው ልዩ ገጽታ እየተበላሸ ነው ይላሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የቅርስ ጥበቃ ተቋም ዩኔስኮ የስፍራውን አስደናቂ መልክዓ ምድር ሲገልጽ "በዙሪያው ወጣ ገባ ያለው ተራራማው መልክዓ ምድር ለገዳሙ አስደናቂ ዕይታን የሚፈጥር ነው" ብሏል።
"የቦታው አቀማማጥ በአንድ በኩል ተፈጥሯዊው ውበት በሌላ በኩል የሰዎች መንፈሳዊነት ተቆራኝተው አንድ ላይ የሚመጡበት ስፍራ ነው" ሲል ነው ዩኔስኮ የገለጸው።
ከሁለት ዓመት በፊት ዩኔስኮ በፕሮጀክቶቹ ላይ ያለውን ስጋት ገልጾ ግብፅ ሥራውን እንድታቆም እና ተጽዕኗቸውን ፈትሻ ለአካባቢውን ቅርስ የጥበቃ ዕቅድ እንድታወጣ ጠይቋል። ሆኖም ግብፅ ይህንን አላደረገችም።
ሐምሌ ወር ላይ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የቅድስት ካትሪን ገዳም ለአደጋ በተጋረጡ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ አውጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Ben Hoffler
በተጨማሪም የገዳሟን ቅርስ ለመጠበቅ እና ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያኗን ጽሑፎች ለመጠበቅ ገንዘብ የሚያሰባስበው የቅድስት ካትሪን ፋውንዴሽን የበላይ ጠባቂ ንጉሥ ቻርለስ እንዲሆኑ የዘመቻው መሪዎች ጠይቀዋቸው ነበር።
ንጉሡ ገዳሟ "ለመጪው ትውልድ መጠበቅ ያለባት ታላቅ መንፈሳዊ ሃብት ናት" ሲሉ ተናግረዋል።
የግብፅ መንግሥት የአገሪቷን ልዩ ታሪክ ያላገናዘበ ፕሮጀክት አቅዷል በሚል ሲተች ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ነገር ግን መንግሥት እነዚህን ታላላቅ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማነቃቂያ አድርገው ነው የሚያያቸው።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተዳክሞ የነበረው የግብፅ ቱሪዝም ማንሰራራት ቢችልም በጋዛ ጦርነት ምክንያት እንዲሁም በቀጣናው ባለው አለመረጋጋት እየተዳከመ መጥቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2028 ወደ 30 ሚሊዮን የሚደርሱ ቱሪስቶችን የማምጣት ዕቅድ አለው።
ከዚህ ቀደምም ባሉ የግብፅ መንግሥታት ታሪካዊቷን የሲና ተራራን የማልማት ሥራዎችን የቤድዊን ማኅበረሰቦችን ሳያማክሩ ተካሂደዋል።
ይህች ስፍራ በአውሮፓውያኑ 1967 በነበረው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በእስራኤል ወረራ ተይዞ ነበር። ለግብፅም የተመለሰላት በአውሮፓውያኑ 1979 ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ ነበር።
የቤድዊን ማኅበረሰብ አባላት ለዓመታት እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠርን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ግብፅ የቀይ ባሕር መዳረሻዎች ግንባታ በሚል ፕሮጀክቷን የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 1980 በደቡባዊ ሲና ነው።

የፎቶው ባለመብት, Ben Hoffler
በርካቶች በአሁኑ ወቅት በቅድሰት ካትሪን ገዳም እየተከናወነ ያለው ቀደም ካለው ፕሮጀክት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
"የቤድዊን ማኅበረሰብ፤ የግዛቲቷ ነዋሪዎች፣ አስጎብኚዎች፣ ሠራተኞች ነበሩ" ሲል የግብፁ ጋዜጠኛ ሞሃናድ ሳብሪ ይናገራል።
የማኅበረሰቡ አባላት "ቱሪዝም በኢንዱስትሪ መልክ ተይዞ ከአካባቢው ተገፍተው እንዲወጡ ተደርገዋል" ሲል ጋዜጠኛው ይወቅሳል።
መንግሥት በበኩሉ ለቤድዊን ማኅበረሰቦች መኖሪያ ስፍራዎችን እያሻሻለ እንደሆነ ይናገራል።
የቅድስት ካትሪን ገዳም ባለፉት መቶ ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋለች።
ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ከዓለማዊው ሕይወት ተገልላ የነበረችው ገዳም በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች እየቀየሯት ይገኛሉ።
ከቀይ ባሕር ሪዞርቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ወደ ስፍራዋ እየተመሙ ይገኛሉ።
አምላክ መለኮታዊው ኃይል ገልጦበታል የሚባለውን የተቃጠለውን ቁጥቋጦ ቅሪት እንዲሁም ጥንታዊው እና የመጀመሪያው በእጅ የተጻፈ የሚባለውን የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የያዘውን ሙዚየም ይጎበኛሉ።
ገዳሟ እንዲሁም የስፍራው ጥልቅ ሃይማኖታዊ ፋይዳ የሚቀጥል ቢሆንም እየተካሄደ ባለው ፕሮጀክት አካባቢው እና ለዘመናት የዘለቀው የማኅበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ በማይመለስ መልኩ ተቀይሯል።















