ዩክሬን ደቡባዊ ግዛቶቿን ለማስመለስ ‘1 ሚሊዮን ጠንካራ’ ጦር አሰማራለሁ አለች

ምልምል የዩክሬን ጦር አባላት በዩናይትድ ኪንግደም ማንችስተር ልምምድ ሲያደርጉ።

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ምልምል የዩክሬን ጦር አባላት በዩናይትድ ኪንግደም ማንችስተር ልምምድ ሲያደርጉ።

ዩክሬን በሩሲያ ጦር የተያዘባትን ደቡባዊ ግዛቷን መልሳ ለመቆጣጠር ‘ጠንካራ’ ያለችውን ‘አንድ ሚሊዮን ጦር’ ልታሰማራ መሆኑን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ገለጹ።

ዩክሬን ጥቁር ባሕር አካባቢ ያሏትን ግዛቶች መልሳ መቆጣጠሯ ለአገሪቱ ምጣሄ ሃብት ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው መከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌስኪ ሬዝኒኮቭ ተናግረዋል።

ኦሌስኪ ሬዝኒኮቭ ወደ ደቡብ ዩክሬን ይሰማራሉ ያሏቸው አንድ ሚሊዮን ዩክሬናውያን ወታደሮች፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መሳሪያዎችን ይታጠቃሉ ብለዋል።

ሚንስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ በኪዬቭ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ የመከላከያ ሚኒስትሩ አስተያየት የጦራቸውን ሞራል ለመገንባት ካልሆነ በቀር ተጨባጭ ዕቅድ አይመስልም ብሏል።

ይህ የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌስኪ ሬዝኒኮቭ አስተያየት የተሰማው የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዶንባስ ግዛት ቁጥጥሩን እያስፋፋ ባለበት ወቅት ነው።

ሬዝኒኮቭ ከታይምስ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ዩክሬን የሶቪዬት ዘመን ስሪት ከሆኑ ጦር መሳሪያዎች፣ ወደ ዘመናዊ ከኔቶ ደረጃ ጋር የሚስተካከሉ የአየር መቃወሚያ ሥርዓቶች እና ተተኳሾችን እንድትታጠቅ የዩናይትድ ኪንግደም ሚና “ቁልፍ” ነው ብለዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ መፋጠን አለበት ብለዋል።

ዩክሬን የወራሪውን የሩሲያ ጦር መካላከል እንድትችል ከ30 ያላነሱ ምዕራባውያን አገራት የተለያዩ የጦር ድጋፎችን አድርገውላታል።

ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት መካከል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግድም እና የዩክሬን ጎረቤት የሆነችው ፖላንድ ይጠቀሳሉ።

ምዕራባውያኑ ለዩክሬን እየሰጡ ካሉት ጦር መሳሪያዎች መካከል ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሮኬቶች፣ ሆዊትዘር ፀረ ታንክ መሳሪያዎች፣ አየር መቃወሚያዎች፣ ታንኮች እና ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች ይገኙበታል።

“የወታደሮቻችንን ሕይወት ለመታደግ ጦር መሳሪያዎችን በፍጥነት እና በብዛት እንፈልጋለን። በየቀኑ ሆዊትዘር [መድፍ መሳይ ዘመናዊ ከባድ መሳሪያዎች] እየጠበቅን ነው። . . . በሠራዊታችን ውስጥ 700 ሺህ ኃይል አለን፤ ብሔራዊው ዘብ፣ ፖሊስ እና የድንበር ጠባቂ ሲደመር ጠንካራ እና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሠራዊት አለን” ሲሉ መከላከያ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑ ጃክ ዋትሊንግ (ዶ/ር) ግን በዚህ አሃዝ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

“ጠንካራ አንድ ሚሊዮን ጦር መልሶ ማጥቃት አያደርግም” ይላሉ ዋትሊንግ። የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር በይፋ ደቡባዊ ዩክሬንን መልሰን ለመቆጣጠር ዕቅድ አለን ማለታቸው ሩሲያ ይህን ስጋት ለመከላከል በአካባቢው በርካታ ጦር እንድታሰማራ ለማስገደድ ያሰበ ሊሆን ይችላል ብለዋል።