ትንታኔ፡ የዘገየው የሰላም ስምምነት ግድያን ያስቆም ይሆናል እንጂ ግጭቱን አይቋጨውም

ፍልስጤማዊያን ደስታቸውን ሲገልፁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    • ፀሐፊ, ጄሬሚ ቦዌን
    • የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታዒ

አንድ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለሥልጣን ስምምነቱ ተግራባራዊ በሚሆንበት በመጀመሪያው ቀን ሐማስ ሦስት ሴት ታጋቾችን እንደሚለቅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶሀ የሚገኙ አደራዳሪዎች ስምምነቱ እሑድ ከሚጀምር ሐሙስ ምሽት እንዲሆን ሙከራ እያደረጉ ነው።

ስምምነቱ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት መጀመሪያ 2023 ሐማስ እስራኤል ላይ በፈፀመው ጥቃት የተቀሰቀሰው ጦርነት ይቀጥላል ማለት ነው።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት 12 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃተ ተገድለዋል።

ይህ ክስተት ላለፉት 15 ወራት የሆነ ነው ይላል የቢቢሲው ተንታኝ ጄሬሚ ቦዌን። የተገደሉት ሰዎች አስከሬን በነጭ ጨርቅ ተጠቅልሎ ከሆስፒታል ደጃፍ ተደርድሯል።

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ትልቅ ዲምፕሎማሲያዊ ድል ተደርጎ ተቆጥሯል። እርግጥ የዘገየ ነው።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለመጀመሪያ ጊዜ ጠረጴዛ ላይ የቀረበው ባለፈው ዓመት ግንቦት ነበር። ሐማስ እና እስራኤል ለስምምነቱ መዝግየት አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ፍልስጤማውያን ደስታቸውን ሲገልፁ ቢቢሲ ተመልክቷል።

ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ ገብተው ዘገባ እንዲሠሩ እስራኤል አትፈልግም። በዚህ ምክንያት ቢቢሲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ላይ ጥገኛ ናቸው። ላለፉት 15 ወራት ያለእነዚህ ጋዜጠኞች የጋዛ ጦርነትን መዘገብ የማይታሰብ ነው።

እስራኤል በጋዛ 200 ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞችን ገድላለች።

ኡም ሙሐመድ የተባሉ የዕሜድ ባለፀጋ ፍልስጤማዊት በስምምነቱ ደስተኛ መሆናቸውን ለጋዜጠኞች ይናገራሉ።

"ስቃዩ ትንሽም ቢሆን ቀለል ብሎልናል። የሚጠፋ ግን አይደለም። በደስታው ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን የምንረሳው ይመስለኛል። የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈቱ። የተጎዱት ይታከሙ። ሕዝቡ ደክሞታል።

ፍልስጤማውያን ከጦርነቱ መትረፋቸው ሊያስደስታቸው ይችላል። በጦርነቱ እስራኤል ከ50 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ገድላለች። በእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

በሐማስ ጥቃት ከ1200 በላይ እስራኤላውያን ዜጎች ተገድለዋል። ከዚህ ጥቃት በኋላ በተጀመረው ጦርነት የጋዛ አብዛኛው ክፍል ወድሟል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጦርነቱ ከ50 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎች እና ተዋጊዎች ተገድለዋል። ላንሴት የተባለው የጤና መፅሔት በቅርቡ ባወጣው የጥናት ዘገባ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ይሆናል ይላል።

በእስራኤል ስምምነቱን ተከትሎ የነበረው ሁኔታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ስምምነቱን ተከትሎ የነበረው ሁኔታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቴል አቪቭ ሁኔታው ለየት ያለ ነው። የታገቱ ሰዎች ቤተሰቦች ስምምነቱ አስደስቷቸዋል። በስምምነቱ የመጀመሪያ ደረጃ 33 ሴቶች፣ አዛውንት፣ የታመሙ እና የቆሰሉ ታጋቾ በሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት ይለቀቃሉ። በምትኩ እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ከእስር ትለቃለች። የተቀሩት ታጋቾች ዕጣ ፈንታ በቀጣይ ድርድሮች ላይ የሚወሰን ይሆናል።

ስምምነቱ 16 ቀናት ሲሆን፣ ሁለተኛው ድርድር ይጀመራል። በዚህ ድርድር ሐማስ የተቀሩትን ታጋቾች ይለቃል። እስራኤል ደግሞ ፍልስጤማውያንን ትፈታለች እንዲሁም ከጋዛ ትወጣለች።

አንደኛው ፈተና የሚሆነው ስምምነቱ ሳይጣስ እንዲቆይ ማድረግ ነው። ጉምቱ የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ከስምምነቱ ከ42 ቀናት በኋላ ጦርነት ድጋሚ ሊጀመር ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የጋዛ ጦርነት ብዙዎች እንደፈሩት ወደ ቀጣናዊ ጦርነት ባያመራም በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፏል። የባይደን አስተዳደር ለዚህ ምስጋና ይገባኛል ይላል።

ሐማስ አሁንም መዋጋት ቢችልም የቀድሞ ጥንካሬው የለም። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና መከላከያ ሚኒስትራቸው በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በጦር ወንጀል ይፈለጋሉ።

አይሲሲ በደቡብ አፍሪካ በኩል የቀረበውን ክስ ተመልክቶ እስራኤልን በጅምላ ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) ወቅሷታል።

የጋዛን ጦርነት የተቀላቀለው ሔዝቦላህ በእስራኤል መልሶ ማጥቃት ተሽመድምዷል። ይህ ሁኔታ ተስፋፍቶ ለአሳድ መንግሥት መገርሰስም አስተዋፅዖ አድርጓል። ኢራን እና እስራኤል ቀጥታ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። ኢራን ከወትሮው ደክማለች። 'አክሲስ ኦፍ ሬዚዝስታንስ' የተባለው በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ኃይልም ተዳክሟል።

የመን የሚገኙት የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር በኩል የሚተላለፉ በአውሮፓ እና በእስያ መካከል የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ዒላማ አድርገዋል። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አማፂያኑ የራሳቸውን የተኩስ አቁም አውጀዋል። መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የሚያቆሙት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረስ ነው ብለው ነበር።

ዕድል፣ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት እና ጠንካራ ዲፕሎማሲን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊቀጥል ይችላል። በየመሐሉ መጣሱ የሚቀር አይደለም። ስምምነቱ ከዘለቀ በጋዛ ያለው ግድያ ሊቆም፣ ታጋቾች ወደ እስራኤል፤ እስረኞች ደግሞ ፍልስጤም ሊመለሱ ይችላሉ።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት የዘለው ግጭት ያለፉት 15 ወራት የመሰለ ጦርነት አይቶ አያውቅም። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ግጭቱን አያቆመውም። የደረሰው ውድመት እና ግድያ ለዓመታት የሚዘከር ነው።