በኢንዶኔዢያው የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 162 ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች ጉዳት ደረሰባቸው

ጉዳት የደረሰበት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጉዳት የደረሰበት ቤት

የኢንዶኔዢያ ዋነኛ ደሴት የሆነችውን ጃቫን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ቢያንስ የ162 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ700 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት እንዳደረሰ የአካባቢው ባለሥልጣን አስታወቁ።

የአካባቢው አስተዳዳሪ የሆኑት ሪድዋን ካሚሊ ናቸው አደጋው ከደረሰ በኋላ እየጨመረ የመጣው የሞቾች ቁጥር 162 መድረሱን ያስታወቁት።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እንዳመለከተው ምዕራባዊ ጃቫ ውስጥ የምትገኘውን የሲያንጁር ከተማን የመታው የመሬት መንቀጥቀጥ 5.6 ኃይል እንዳለው ተገልጿል።

አደጋውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ የሆስፒታል ክፍሎት ስላልበቁ ብዙዎች ሜዳ ላይ ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ርዕደ መሬቱ 100 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ በምትገኘው በአገሪቱ ርዕሰ መዲና ውስጥ ንዝረቱ የተሰማ ሲሆን፣ እዚያም ነዋሪዎች ከረጃጅም ህንጻዎች እንዲወጡ ተደርጓል።

ባለሥልጣናት ተከታይ ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሚችል እና በአደጋው የሞቱ ሰዎች አሃዝም ከፍ ሊል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በመሬት መንቀጥቀጡ የተመታው አካባቢ በርካታ ሕዝብ የሚኖርበት፣ ለመሬት መንሸራተት የተጋለጠ እና በተገቢው ሁኔታ ያልተገነቡ ቤቶች ያሉበት ነው።

የአደጋ ጊዜ ነፍስ አድን ሠራተኞች ከፈረሱ ቤቶች ውስጥ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ አንዲት ሴትን ከህጻን ልጇ ጋር ማትረፋቸውን ከአካባቢው የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በርዕደ መሬቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች በፍርስራሾች ስር ተቀብረው ያሉ ሲሆን፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥርም ከፍ ሊል ይችላል እየተባለ ነው።

ከ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የርዕደ መሬቱ ንዝረት በተሰማባት ጃካርታ ውስጥ በድንጋጤ በርካቶች ከየህንጻዎቹ ወጥተው ነበር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ከ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የርዕደ መሬቱ ንዝረት በተሰማባት ጃካርታ ውስጥ በድንጋጤ በርካቶች ከየህንጻዎቹ ወጥተው ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አደጋው የደረሰባት ምዕራብ ጃቫ አስተዳዳሪ ሪድዋን ካሚል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንዳረጋገጡት በርካታ ሰዎች ሞተዋል።

“ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እየመጡ ነው። 700 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ኃላፊው ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

በመሬት መንቀጥቀጡ ባለሥልጣናት ከ40 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ከገለጹ በኋላ ቁጥሩ ወደ 56 ደርሶ ነበር። የኢንዶኔዢያ የአደጋ መከላከያ ኤጀንሲ ባወጣው አዲስ መረጃ ደግሞ በአደጋው ቢያንስ 62 ሰዎች መሞታቸውን ካሳወቀ በኋላ፣ የአካባቢው ባለሥልጣን የሟቾች ቁጥር 162 መድረሱንና ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጸዋል።

ጨምሮም በርዕደ መሬቱ በተመታችው ሲያንጁር አካባቢ ከ5,000 በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ከ2,200 የሚበልጡ ቤቶች ፈርሰዋል።

ቀደም ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤኤፍፒ ባለሥልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው አብዛኞቹ ተጎጂዎች በቤቶች ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ እና የአጥንት መሰበር የደረሰባቸው ናቸው።

“ከተለያዩ መንደሮች የተጎዱ ሰዎችን የያዙ አምቡላንሶች ወደ ሆስፒታሎች እየመጡ ናቸው” ያሉት ባለሥልጣኑ “መውጣት ያልቻሉ በርካታ ቤተሰቦች አደጋው በደረሰባቸው መንደሮች ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ቪዲዮዎች በቤቶች እና በሱቆች ላይ የደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ።

በሲያንጁር አካባቢ በርካታ ህንጻዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ተቋም ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። ጉዳት ከደረሰባቸው መካከልም አንድ ሆስፒታል እና እስላማዊ አዳሪ ትምህርት ቤት ይገኙበታል።

በአቅራቢያ ባለችው ከተማ ሲያንጁር ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ በደረሰበት ጊዜ፣ በዋና ከተማዋ ጃካርታ ውስጥ ለአንድ ደቂቃ ያህል የቆየ ንዝረት የተሰማ ተሰምቷል። በዚህም ሳቢያ የቢሮ ሠራተኞች ከህንጻዎቹ በድንጋጤ ሮጠው ወጥተው ነበር ተብሏል።

“የእሳት ቀለበት” ተብሎ በሚጠራው ለርዕደ መሬት ተጋላጭ በሆነው የፓሲፊክ አካባቢ በምትገኘው ኢንዶኔዢያ የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ ነገር አይደለም።

አገሪቱ ከዚህ ቀደም እጅግ አውዳሚ በሆኑ ርዕደ መሬቶች እና ሱናሚዎች የተመታች ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በፊት ሱላዌሲን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።