በፔሩ ከአውሮፕላን ጋር የተጋጨው የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና በልምምድ ላይ ነበር ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው አርብ ፔሩ ውስጥ በሚገኘውና በርካታ መንገደኞችን በሚያስተናግደው አየር ማረፊያ ውስጥ ለመነሳት እየተንደረደረ ካለ አውሮፕላን ጋር የተጋጨው የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪና ቀደም ብሎ የታቀደ ልምምድ ላይ እንደነበረ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በደቡብ አሜሪካዊቷ ፔሩ ዋና ከተማ ሊማ ውስጥ በሚገኘው ጆርጅ ቻቬዝ አየር ማረፊያ ውስጥ ከላታማ አየር መንገድ የመንገደኞች ጄት ጋር በተፈጠረው በዚህ የመጋጨት አደጋ ሁለት የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ሕይወት ጠፍቷል።
በአደጋው በአውሮፕላኑ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት ከመድረሱ ውጪ የሞተ የለም።
የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው አየር መንገድ ላታማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደተናገሩት አውሮፕላኑ መንደርደሪያው ክፍት በመሆኑ መነሳት እንደሚችል ፈቃድ አግኝቶ ነበር።
ነገር ግን በዚያ ወቅት የአየር ማረፊያው በአደጋው ወቅት የእሳት አደጋ ሠራተኞች የተለመደ ልምምድ እያደረጉ ነበር ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ ቪዲዮ አውሮፕላኑ ከመኪናው ጋር ከተጋጨ በኋላ እስኪቆም ድረስ በእሳት ተያይዞ ጭስ እየወጣው በፍጥነት ሲጓዝ ያሳያል።
የሊማ አየር ማረፊያን የሚየስተዳድረው ተቋም ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ለአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ሲባል በሚያደርጉት ልምምድ ወደ መንደርደሪያው ሜዳ ለመግባት የሚያስችላቸውን አስፋለጊ ዝግጅት አድርገው ነበር።
የልምምዱ ሰዓት በበረራ መቆጣጠሪያው ክፍል የተረጋገጠ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ በረራ ለማድረግ በመንደርደር ላይ የነበረው አውሮፕላን ከእሳት አደጋው ተሽከርካሪ ጋር ተጋጭቶ አደጋው ተከስቷል።
ነገር ግን አደጋውን በተመለከተ በአገሪቱ የበረራ ተቆጣጣሪ አካል እና በአየር መንገዶች ባለሥልጣናት የተሰጠው አስተያየት እርስ በርሱ ይቃረናል እየተባለ ነው።
በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ዋነኛው የበረራ ማዕከል የሆነው የሊማ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአደጋው በኋላ ለ24 ሰዓታት ሥራውን አቁሞ ነበር።
በአደጋው ከሁለቱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ውጪ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ወይም የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ላይ ሞት እንዳላጋጠመ አየር መንገዱ በትዊተር ገጹ ላይ አመልክቷል።
በአደጋው ከሞቱት ሁለት የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ባሻገር፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 20 የሚሆኑ መንገደኞች በደረሰባቸው ጉዳት ህክምና እንደተደረገላቸውና ከመካከላቸው ሁለቱ ጉዳታቸው ከባድ እንደሆነ የፔሩ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አንድ የሆስፒታል ባለሥልጣን ከአደጋው በኋላ አንድ የ31 ዓመት የእሳት አደጋ ሠራተኛ በአስጊ ሁኔታ ላይ ሆኖ ሕክምና እየተደረገለት መሆኑን ገልጸዋል።
የፔሩው ፕሬዝዳንት ፔድሮ ካስቲሎ አደጋውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ የእሳት አደጋ ሠራተኞችን ስማቸውን ጠቅሰው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
“በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ለጀግኖቹ የእሳት አደጋ ሠራተኞች አንጌል ቶሬስ እና ኒኮላስ ሳንታ ጋዴ ቤተሰቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ከልቤ እገልጻለሁ” በማለት በትዊተር ላይ አስፍረዋል።












