ፔሩ ውስጥ ሲንደረደር የነበረ አውሮፕላን ከእሳት አደጋ መኪና ጋር ተጋጭቶ ሁለት ሰዎች ሞቱ

ከእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ጋር የተጋጨው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከእሳት አደጋ ተሽከርካሪ ጋር የተጋጨው አውሮፕላን

ፔሩ ውስጥ ለመነሳት በመንደርደር ላይ የነበረ አንድ አውሮፕላን ከእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪና ጋር በመጋጨቱ ሁለት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሕይወት አለፈ።

በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ ዋና ከተማ ሊማ ውስጥ በሚገኘው ጆርጅ ቻቬዝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ ውስጥ የላታም አየር መንገድ አውሮፕላን እና የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪው የተጋጩት ትናንት አርብ ምሽት ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጨ ቪዲዮ አውሮፕላኑ ከመኪናው ጋር ከተጋጨ በኋላ እስኪቆም ድረስ በእሳት ተያይዞ ጭስ እየወጣው በፍጥነት ሲጓዝ ያሳያል።

በአደጋው ከሁለቱ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ውጪ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ወይም የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ላይ ሞት እንዳላጋጠመ አየር መንገዱ በትዊተር ገጹ ላይ አመልክቷል።

አንድ የሆስፒታል ባለሥልጣን ከአደጋው በኋላ አንድ የ31 ዓመት የእሳት አደጋ ሠራተኛ በአስጊ ሁኔታ ላይ ሆኖ ሕክምና እየተደረገለት መሆኑን ገልጸዋል።

የፔሩ የጤና ሚኒስቴር 20 በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ መንገደኞች ላጋጠማቸው ጉዳት ሕክምና እንደተደረገላቸው እና ከመካከላቸውም ሁለቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ እንደሆነ አሳውቋል።

በአገር ውስጥ በረራ ላይ የነበረው አውሮፕላን ለመነሳት እየተንደረደረ በነበረበት ጊዜ የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪናው ለምን ወደ መንደርደሪያው መንገድ እንደገባ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆነው ላታማ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማኑኤል ቫን ኦርዲት ከአደጋው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ አውሮፕላኑ ተንደርድሮ ለመነሳት ፈቃድ አግኝቶ እንደነበር ገልጸዋል።

“ለምን የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪው ወደ መንደርደሪያው መስመር ውስጥ እንደገባ አላወቅንም” ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የፔሩ ዐቃቤ ሕግ ሰዎችን ነፍስ የማጥፋት ድርጊት ሊሆን ይችላል በሚል ክስተቱን እየመረመረው መሆኑን ዘግቧል።

ከአደጋው በኋላ የጆርጅ ቻቬዝ አየር ማረፊያን የሚያስተዳድረው ተቋም አስከ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አየር ማረፊያው ዝግ እንደሚሆን አሳውቋል።

በዚህም ሳቢያ በዋና ከተማዋ ሊማ ማረፍ ያለባቸው ዓለም አቀፍ በረራዎች ወደ ጎረቤት አገራት ኮሎምቢያ፣ ፓናማ እንዲሁም በሌሎች የፔሩ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያርፉ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የፔሩው ፕሬዝዳንት ፔድሮ ካስቲሎ አደጋውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ የእሳት አዳጋ ሠራተኞችን ስማቸውን ጠቅሰው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

“በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ለጀግኖቹ የእሳት አደጋ ሠራተኞች አንጌል ቶሬስ እና ኒኮላስ ሳንታ ጋዴ ቤተሰቦች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ከልቤ እገልጻለሁ” በማለት በትዊተር ላይ አስፍረዋል።