ግዙፉ የክሪፕቶከረንሲ ተቋም 3.1 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለበት ተነገረ

ኤፍቲኤክስ (FTX)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም ሁለተኛው የክሪፕቶከረንሲ የገንዘብ መለዋወጫ 50 የሚሆኑ ዋነኛ አበዳሪዎቹ 3.1 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለበት አንድ የፍርድ ቤት ሰነድ አመለከተ።

ችግር ላይ የወደቀው የክሪፕቶከረንሲ ተቋም ባለፈው ሳምንት መክሰሩን አሜሪካ ውስጥ ያሳወቀ ሲሆን፣ ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የ10 ዋነኛ አበዳሪዎቹ 1.45 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለበት ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ የኤፍቲኤክስ (FTX) የበላይ ኃላፊ ሳም ባንክማን-ፍራይድ ከተቋሙ መሪነት በፈቃዱ እንዲወርድ አስገድዶታል።

ይህ በዓለም ሁለተኛው ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ የገንዘብ መለዋወጫ የሆነው ኤፍቲኤክስ (FTX) ክስረት፣ ችግር ውስጥ የሚገኘውን የክሪፕቶ ገበያን አስተማማኝነት የበለጠ አናግቶታል።

ኤፍቲኤክስ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው የኪሳራ ማሳወቂያ ላይ የገጠመውን ውድቅት ተከትሎ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እና የንግድ ተቋማት ገንዘባቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ ብሏል።

ባለፈው ቅዳሜ ኤፍቲኤክስ እንዳሳወቀው በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሃብቶች ለሽያጭ ለማዘጋጀት ወይም አንዳንዶቹን የንግድ ተቋማት መልሶ ለማደራጀት የሚያስችል ግምገማ ማድረግ ጀምሯል።

የክሪፕቶከረንሲው ተቋም የኪሳራ ጉዳይን ለመመልከት ነገ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ የኪሳራ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ ካላፈ በኋላ በዝውውሩ ውስጥ ገንዘባቸውን ካፈሰሱት ሰዎች መካከል ምን ያህሉ ሃባታቸውን መልሰው ያገኛሉ የሚለው አስካሁን ግልጽ አይደለም። ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት የሚያገኙ ከሆነ ከአጠቃላይ ገንዘባቸው ባጣም ትንሹን ሊሆን ይችላል።

ባለፈው ሳምንት አዲሱ የኤፍቲኤክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆን ሬይ የከሰረው የክሪፕቶ ድርጅት ሲመራበት የነበረውን መንገድ “እንዲህ አይነት ድርጅት በመምራት ሂደት ውስጥ አጠቃላይ የቁጥጥር ውድቀት አጋጥሞኝ አያውቅም” በመላት ክፉኛ ተችተዋል።

በገዛ ፈቃዱ ከኃላፊነቱ የለቀቁትን ባንክማን- ፍሬይድን የተኩት ሬይ ጨምረውም በተቋሙ ውስጥ “እምነት የሚጣልበት የገንዘብ ዝውውር መረጃ ሙሉ ለሙሉ የለም” ሲሉም ተችተዋል።

የቀድሞው ኃላፊም ባንክማን-ፍራይድ ለቪክስ የዜና ድረ ገጽ የገንዘብ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎች ከእሳቸው ቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን በመጥቀስ ኤፍቲኤክስ ኪሳራ በማወጁ እንደሚጸጸቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም የገንዘብ ተቋማት ተቆጣጣሪዎች የነበራቸውን ቸልተኝነት ተችቷል።