‘የክሪፕቶው ንጉሥ’ ባልተጠበቀ ሁኔታ መክሰሩን አወጀ

ሳም ባንክማን ፍራይድ

የፎቶው ባለመብት, TOM WILLIAMS

የምስሉ መግለጫ, ሳም ባንክማን ፍራይድ

ግዙፉ የክሪፕቶከረንሲ ልውውጥ ኩባንያ፣ ኤፍቲኤክስ [FTX] መክሰሩን በይፋ አወጀ።

ይህን ተከትሎም የኩባንያው መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወጣቱ ቢሊየነር ሳም ባንክማን-ፍራይድ ሥልጣኑን በይፋ ለቋል።

የ30 ዓመቱ ሳም በዓለም ላይ ሁለተኛውን ግዙፉን የክሪፕቶከረንሲ ልውውጥ ኩባንያን በበላይነት ሲያስተዳድር ነበር። 

ኤፍቲኤክስ በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉ የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት ኩባንያዎች አንዱ የነበረ ሲሆን በአንድ ጀንበር እንዳልነበረ ሆኖ ተንኮታኩቷል።

“በጣም ነው የማዝነው፤ እንዲህ እንሆናለን አላልኩም ነበር። የምናገግምበት መንገድ ይኖር ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ጽፏል የክሪፕቶው ንጉሥ ሳም አርብ ዕለት በትዊተር ሰሌዳው ላይ። 

“ነገሩ እኔን ራሱ አስደንግጦኛል” ሲልም አክሏል።

ኤፍቲኤክስ በአንድ ጊዜ እንዲህ ከመንኮታኮቱ በፊት ሳም 'የክሪፕቶ ዋረን በፌት' ተብሎ ይወደስ ነበር። ሃብቱም ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር ይገመት ነበር።

ሰኞ ዕለት 15 ቢሊዮን ዶላር የተገመተው ሃብቱ ዛሬ ቅዳሜ መና ሆኗል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሾልከው የወጡ መረጃዎች የክሪፕቶ ግብይት ኩባንያው ኤፍቲኤክስ እና ሌሎች በሳም ተይዘው የነበሩ ኩባንያዎች የፋይናንስ መንገጫገጭ ገጥሟቸው እንደነበረ አሳይተዋል።

ይህ መረጃ ከወጣ በኋላ በርካታ ደንበኞች ክሪፕቶዎቸቸውን ለመመንዘር እሽቅድምድም ውስጥ በመግባታቸው ኩባንያው ኪሳራን በይፋ ለማወጅ ተገዷል። 

ኤፍቲኤክስ ክሪፕቶን በመሸጥ፣ ዲጂታል ገንዘብን የማለዋወጥ ሥራን የሚሠራ የዲጂታል ግብይት አሳላጭ ኩባንያ ነው። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በትንሽ ቀናት ውስጥ ድንገተኛ የገንዘብ እጥረት የገጠመው ወጣቱ የክሪፕቶ ንጉሥ ሳም፣ በገንዘብ የሚታደገው ፋይናንስ ተቋም ለማግኘት ቢጣጣርም አልሆነለትም።

አሁን በርካታ የክሪፕቶ ደንበኞች ዲጂታል ገንዘባቸውን በአንዳች ቁስ ወይም መደበኛ ገንዘብ ለመቀየር ሳይችሉ ቀልጦባቸው ቀርቷል።

አሁን በይፋ ኪሳራን በማወጁ ኩባንያው በፍርድ ቤት ክትትል ስር ሆኖ የተወሰነ ሥራ እንዲቀጥልና ራሱን ከወደቀበት እንዲያነሳ ዕድል ይሰጠዋል።

ኤፍቲኤክስ እንዳለው በአሁኑ ወቅት ግብ አድርጎ የተነሳው ሁኔታዎችን በስክነት አጥንቶ ያለውን ሃብት ወደ ገንዘብ ቀይሮ የኩባንያውን ባለድርሻዎች ከውድቀት መታደግ ነው። 

ኤፍቲኤክስ ኩባንያ ከ10 እስከ 50 ቢሊየን ዶላር ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሃብት እንዳለው ይገመታል። 

አሁን ቋሚ የኩባንያውን ንብረቶች በመሸጥ ለባለድርሻዎች ገንዘባቸውን በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ጥረቱ ተጀምሯል።

ወጣቱ ሳም በአሜሪካ ምርጫ ከፍተኛ የዲሞክራት ፓርቲ ለጋስ በመሆን ስሙ ይወሳል።

ይህ ክሪፕቶ ቢዝነስ በሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲኖረው ለማስቻልም ከዝነኞቹ ቶም ብሬዲ እና ጊሴል ባንቼን ጋር አብሮ ሠርቷል።

ይሁንና ወጣቱ ሳም ባሉት እህት ኩባንያዎች መካከል፣ በተለይም በኤፍቲኤክስ እና አላሜዳ፣ መካከል የጥቅም ግጭት ሊኖር እንደሚችል ቀድሞም ስጋት የነበራቸው ነበሩ።

የኤፍቲኤክስ መንኮታኮት በሌሎችም የክሪፕቶ ከረንሲ ግብይቶች ላይ ጥላውን ጥሏል።

ከክሪብቶከረንሲዎች ሁሉ ገናናው ቢትኮይን ለምሳሌ በ20 ከመቶ ዋጋው በዚህ ሳምንት ገበያው አሽቆልቁሎበታል።

አንዳንድ ደንበኞችም የክሪፕቶ ኩባንያዎቻቸው ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርስባቸው መተማመኛ እንዲሰጡ ከደንበኞቻቸው ጥያቄ እየቀረበባቸው ነው።

የኤፍቲኤክስ የክሪፕቶ ግብይት ኩባንያ ተቀናቃኝ የሆነው ቢናንስ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ እንደተናገሩት የተቀናቃኛችን መውደቅ የእኛ ድል ተደርጎ መታሰብ የለበትም።

“ደንበኞች እምነት እያጡ ነው። እምነት እያጡ ያሉት ደግሞ በአንድ ኩባንያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በዘርፉ ላይ ነው” ብለዋል። 

የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዎች በባህሪያቸው በቢዝነስ እንዲቀጥሉ በደንበኞች ላይ እምነት እንዲኖር የግድ ይላል። 

አሁን በኪሳራ የተንኮታኮተው ኤፍቲኤክስ የክሪፕቶ ግብይት ኩባንያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እና 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት ነበረው።