የዋነኛው ክሪፕቶከረንሲ ዋጋ እያሽቆለቆለ ያለው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያለፉት ጥቂት ቀናት ለቢትኮይንም ሆነ ለክሪፕቶከረንሲ አስከፊ ጊዜ ነው። አሁን ላይ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 21 ሺህ 974 ዶላር ነው።
ቢትኮይን ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ባለፉት አምስት ቀናት ብቻ 25 በመቶ አሽቆልቁሏል። ይህም ባለፉት 18 ወራት የተመዘገበው ዝቅተኛው ዋጋው ነው።
ቢትኮይን በዘመኑ ያወጣው ከፍተኛ ዋጋ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ዋጋው 70 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ነበር።
ለምን በፍጥነት ተንኮታኮተ?
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለዚህ ምክንያቱ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ነው። በእርግጥ በዓለማችን ነገሮች ጥሩ መስለው የማይታዩት በክሪፕቶከረንሲው በኩል ብቻ አይደለም።
በዓለም ዙርያ የምጣኔ ሃብት ቀውስ እያንዣበበ፣ የዋጋ ንረት እያሻቀበ፣ ወለድ እየጨመረ እና የኑሮ ውድነቱ እየናረ ነው።
የአክሲዮን ገበያዎችም ብርክ ይዟቸዋል። የአሜሪካው ስታንዳርድ ኤንድ ፑርስ 500 የድርሻ ገበያ (ስቶክ ማርኬት) በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ ከነበረው 20 በመቶ ቀንሷል።
የድርሻ ገበያ ማለት ኩባንያዎች የኩባንያው የባለቤትነት ድርሻን ለገበያ የሚያቀርቡበት እና ሰዎችም ይህንን ድርሻ ከገዙ በኋላ ኩባንያው ትርፋማ በሆነበት መጠን ድርሻቸውን መልሰው በመሸጥ ወይም ከትርፍ ክፍፍል ትርፋማ የሚያደርግ አሠራር ነው።
ይህ የድርሻ ገበያ በመቀነሱም ትላልቅ ባለሃብቶች ሳይቀሩ ኪሳራ እየገጠማቸው ነው። ሌሎችም በርካታ ተራ ባለሃብቶችም በማንኛውም ነገር ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ያላቸው ዕድል አነስተኛ ሆኗል።
በርካቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በዚህ ጊዜ እንደ ክሪፕቶከረንሲ ተለዋዋጭ እና እንዲህ ነው ተብሎ የማይተነበይ ነገር ላይ ማዋል ትልቅ አደጋ እንደሆነ ያስባሉ።
ክሪፕቶከረንሲ፣ በገንዘብ ባለሥልጣናት ቁጥጥር የማይደረግበትና የማይጠበቅ ዲጂታል ገንዘብ ነው። በመሆኑም የቆጠቡትን ገንዘብ እርሱ ላይ ለማፍሰስ እየተጠቀሙበት ከሆነና ዋጋ ካጡበት አሊያም የዲጂታል ገንዘብ ማስቀመጫዎን ( ክሪፕቶ ዋሌት) ካጡት ገንዘብዎ ጠፍቷል ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለምን አሁን?
ባለፈው ወር ሁለት ብዙም የማይታወቁ ግን በጣም ትልቅ የሆኑ ዲጂታል ገንዘቦች ተንኮታኩተዋል። ይህም በአጠቃላይ በዲጂታል ገበያው ላይ ያለውን አመኔታ አሳጥቷል።
በዚህም ምክንያት ያላቸውን ገንዘብ ለመሸጥ የሚወስኑ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
በርካታ ሰዎች ቢትኮይናቸውን በሸጡ ቁጥር ደግሞ ያለው ዋጋ እየቀነሰ ይመጣል። ምክንያቱም ዲጂታል ገንዘቦችን ዋጋቸው እንዲዋዠቅ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ይህ በመሆኑ ነው። ዋጋው የሚወደደው የሚገዛ ሰው ሲበዛ እንጂ የሚሸጥ ሰው ሲበረክት አይደለም።
ይህ ደግሞ በርካታ ሰዎች የቢትኮይን ዋጋ እየወረደ መምጣቱን በመመልከታቸው ያላቸውን እንዲሸጡ ገፋፍቷቸዋል። ዑደቱም በዚህ መልኩ ይቀጥላል።
የፋይናንሻል ታይምስ ማርኬትስ አርታኢ ኬቲ ማርቲን፣ “ቢትኮይን እንደ ሌሎች ባህላዊ አሴቶች እርሱን ለመደገፍ የሚያስችል ሌላ ንግድ፣ የገቢ ፍሰት ወይም ሌሎች ነገሮች የሉትም” ይላሉ።
ኬቲ አክለውም “ዋጋው ሰዎች ሊገዙ ያሰቡበት ዋጋ ብቻ ነው” ሲሉ የቢትኮይን ዋጋ የመሸጫ ሂሳቡ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ አስረድተዋል።
“በርካታ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ሸጠው ከወጡ፣ አበቃ። ምንም መቆሚያ የለም። ነገ በ10 ሺህ ዶላር ዋጋ መሸጡን የሚያስቆመው ምንም ነገር የለም” ብለዋል።
በመሆኑም ባለፉት ጥቂት ቀናት ቢናንስ የተባለው ዓለም አቀፋዊው ትልቁ የክሪፕቶ መገበያያ መድረክ ለተወሰኑ ሰዓታት ቢትኮይንን እንዳይወጣ አድርጎ ነበር። “ሁሉም ሰው ላያምን ቢችልም ይህንን ያደረግነው የገንዘብ ዝውውሩ በመቆሙ ነው” ብሏል።
የክሪፕቶ አበዳሪ ሴልሲየስም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። ይሁን እንጂ እርምጃውን የወሰደው በቴክኒክ ችግር ሳይሆን በከፍተኛ የገበያ ሁኔታ እንደሆነ ገልጿል።
አሁን ላይ ደግሞ የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ፣ ኮይንቤዝ ሠራተኞቹን በ18 በመቶ መቀነሱን አስታውቋል።
በሁኔታው የተደናገጡና ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ባለሃብቶችም ቢትኮይናቸውን መሸጥ ጀምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, CRYPTO.COM
ገበያው እንዴት ሊረጋጋ ይችላል?
የተፈጠረውን ቀውስ ለማረጋጋት ቢትኮይን ያላቸው ሰዎች ይዘው መቆየት እና ሌሎች ደግሞ እንደገና መግዛት መጀመር አለባቸው።
የክሪፕቶ አድናቂዎችም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት ርካሽ በመሆኑ ክሪፕቶ ለመግዛት ጊዜው አሁን እንደሆነ ይናገራሉ። ምክንያቱም ሁልጊዜም ቢትኮይን የሚሰራው በዚህ መልኩ ነው።
የዋጋ መዋዠቁ ሁልጊዜም የሚያጋጥም እንጂ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ተጠቃሚዎቹ ይገልጻሉ።
በክሪፕቶ በአጭር ጊዜ ቱጃር የሆኑ ሰዎች ታሪክ እና የታዋቂ ሰዎች ገበያውን መቀላቀልም አዲስ ዲጂታል ገንዘብን ይስባሉ።
ኤሎን መስክ ለክሪፕቶ ያለውን ፍቅር በትዊተር ገጹ አጋርቷል። መስክ በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና ኩባንያው፣ ቴስላ ባለፈው ዓመት 1.5 ቢሊየን ዶላር ቢትኮይን ላይ አፍስሷል። ሆኖም የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢንቨስትመንት አማካሪ ሆኑት አልታፍ ካሳም ስለክሪፕቶከረንሲ መስክ “እውነቱን ለመናገር፣ ደፋር ሰው ብቻ መግባት ያለበት ቦታ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ራዲዮ 5 ተናግረዋል።
እውቁ የሆሊዉድ ተዋናይ ማት ዴመን፣ እአአ ጥቅምት 2021 ላይ “ገንዘብ ለደፋሮች ታደላለች” በሚል መልዕክት የክሪፕቶ ማስታወቂያ ሰርቷል።
ማስታወቂያው በብሔራዊ የእግር ኳስ ሊግ ‘ሱፐር ቦውል’ ተለቅቆ በትዊተር እና በዩትዩብ 28 ሚሊየን ጊዜ ታይቷል።
ሆኖም ማስታወቂያው በተለቀቀበት ወቅት ቢትኮይን የገዙት ‘ደፋሮች’ ምን አልባት አሁን ላይ ምንም ጥቅም እንዳላገኙ ላይሰማቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ ደፋር በመሆናቸው የተጠቀሙት ገንዘብ እንደሌለ ሊረዱት ይችላሉ። ምክንያቱም ያኔ ቢትኮይን ዛሬ ከነበረው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ዋጋ ነበረው።












