በፕራግ ዩኒቨርስቲ 14 ሰዎችን የገደለው ታጣቂ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock
በቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ አንድ ታጣቂ ተኩስ ከፍቶ 14 ሰዎችን ሲገድል 25 ማቁሰሉን ባለስልጣናቱ ተናገሩ።
ጥቃቱም በዘመናዊ የቼክ ታሪክ አስከፊው ነው ተብሏል።
የ24 ዓመቱ ታጣቂ በታሪካዊቷ ፕራግ በሚገኘው ቻርለስ ዩኒቨርስቲ ያደረሰውንም ጥቃት ተከትሎም “መወገዱን” ፖሊስ አስታውቋል።
ጥቃቱ እየተፈጸመ በነበረበት ወቅት የዩኒቨርስቲው ሰራተኞች የቻሉትን መንገድ ተጠቅመው ክፍሎቹን እንዲዘጉ ተነግሯቸዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፊያላ ሐሙስ ዕለት የደረሰውን “አሳዛኝ ክስተት” ተከትሎም የነበራቸውን ዕቅዶች መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።
ጥቃቱ የተጀመረው በዩኒቨርስቲው የስነ ጥበባት ህንጻ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነበር።
በኋላም ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት አንዳንዶች ከህንጻው ፎቅ ሲዘሉ የታዩ ሲሆን የተኩስ ድምጽም ይሰማል።
በሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ በርካታ ሰዎች በቱሪስቶች ታዋቂ ከሆነው አካባቢ በፍርሃት ሲሸሹ ይታያሉ።
ታጣቂው የዩኒቨርስቲው ተማሪ እንደነበር የሃገሪቱ ፖሊስ አዛዥ እና የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሐሙስ እለት በሰጡት አጭር መግለጫ አስረድተዋል።
ከፕራግ 21 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኝ መንደር እንደመጣም ተነግሯል። የታጣቂው አባት ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ሐሙስ ቀደም ብሎ ሞተው ተገኝቷል። የታጣቂው ዓላማ ለጊዜው አልታወቀም።
በጥቃቱ ምንም አይነት የፖሊስ አባላት እንዳልተጎዱም የቅድሚያ መረጃዎች እንደጠቆሙ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ታጣቂው ባለፈው ሳምንት በፕራግ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ሞተው የተገኙ ሁለት ሰዎችን ሳይገድላቸው እንዳልቀረም ፖሊስ ጥርጣሬ አለኝ ብሏል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር የሆኑት ሰርጌይ ሜድቬዴቭ ጥቃቱ ሲጀመር ከዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ውስጥ በአንዱ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በወቅቱ እያስተማርኩ ነበር እናም መጀመሪያ ላይ ምን እንደተፈጠረ በትክክል አልተገነዘብኩም ነበር። ድምጾች ይሰሙ ነበር። እኔ አትኩሮቴ በሙሉ ትምህርቱ ላይ ስለነበር ብዙም አልሰማሁም። ተማሪዎቼ በተሻለ ሁኔታ ሰምተውታል” ሲሉም አስረድተዋል።
“ከዚያም አንድ ትልቅ ነገር መከሰቱን ብንረዳም በኢንተርኔት ላይም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ምንም መረጃ አልነበረም። ከዚያም ልዩ ኃይሎች በሩን ጥሰው ገቡና ፈለግ፣ ፈለግ አድርገው ውስጥ እንድንቆይ ነገሩን” ብለዋል።
አክለውም “ከአንድ ሰዓት በኋላ ሌላ የፖሊስ ቡድን መጥቶ በሩን ሰብረው በመግባት መሬት ላይ አንጋለሉን ከዚያም ለአጭር ጊዜ ከፈሹን በኋላ ህንጻውን ለቀው ወጡ” ሲሉም አስረድተዋል።












