ሲቲ ከዩናይትድ - ማን ያሸንፋል? የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ሀላንድ እና ብሩኖ

ማንቸስተር ሲቲ ከማንቸስተር ዩናይት እሑድ ዕለት በኤቲሀድ ይገናኛሉ። ሁለቱም ቡድኖች ድል ናፍቋቸዋል።

"እንዲህ ያለ ሁለቱም ቡድኖች ለድል የተጠሙበት የማንቸስተር ደርቢ አይተን እናውቅ ይሆን? አይመስለኝም" ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።

"ማንቸስተር እንደመሆኑ ዝናብ መዝነቡ አይቀርም። ለነገሩ ሁለቱም ቡድኖች የውጤት እጦት ደመና አጥልቶባቸዋል።"

ሱተን ሁሉንም የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት ያስቀምጣል። እነሆ የ16ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት።

ቅዳሜ

የአርሰናል እና ኤቨርተን አርማ

አርሰናል ከኤቨርተን

አርሰናል ባለፈው ሳምንት ከፉልሀም ጋር አቻ ቢለያይም የተሻለ ተጫውቷል። ነገር ግን በዚህ ጨዋታ ብዙ የጎል ዕድሎች አልፈጠሩም።

ፉልሀም የተደራጀ ቡድን ነው። የሚኬል አርቴታ ልጆች የተቸገሩትም ለዚህ ይሆናል።

ማርቲን ኦዴጋርድ እንደ ቀድሞው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ባይችልም መድፈኞቹ ከቆሙ ኳሶች ጎሎች ማግኘት ይችላሉ። ሰዎች አርሰናል ጎል የሚያስቆጥረው ከማዕዘን ምት (ኮርና) ብቻ ነው የሚል ትችት ያሰማሉ። እኔ ግን ይህ አንድ ተጨማሪ ኃይላቸው ነው ብዬ ነው የማምነው። እንደውም አንዳንድ የሊጉ ቡድኖች ልክ እንደ አርሰናል ከቆሙ ኳሶች ጎል ማግኘት ቢችሉ ይመኛሉ።

አርሰናል ግስጋሴው በኤቨርተን ይረታል ብዬ አላስብም። የሾን ዳይች ቡድን ለመከላከል ቢሞክርም ከመርታት አይተርፍም። ይህ ጨዋታ የትኛው ቡድን በማዕዘን ምት የተሻለ ነው የሚለው የሚወሰንበት ይመስለኛል። እኔ አርሰናል ነው ባይ ነኝ።

ግምት፡ 2 - 0

ውጤት፡ 0 - 0

የሊቨርፑል እና ፉልሀም አርማ

ሊቨርፑል ከፉልሀም

ፉልሀም ባለፈው ሳምንት ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ጨዋታ የጎል ክልላቸውን በማስጠበቅ ጥንቁቅ ነበሩ። በዚህኛውም ጨዋታ ይህን ያደርጋሉ ብዬ እገምታለሁ።

ነገር ግን እንዳለፈው ሳምንት ጨዋታ ይሳካላቸዋል አልልም።

የአርን ስሎት ቡድን በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከጂሮና ጋር በነበራቸው ጨዋታ ይህን ያህል አስፈሪ አልነበሩም። ነገር ግን በርካታ ቡድኖች በአውሮፓ እና በሀገር ውስጥ ውድድሮች ተጠምደው የሚገኙበት ወቅት ስለሆነ የሊቨርፑል መቀዛቀዝ ዜና አይደለም።

በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው ጎል ወሳኝ ነው ብዬ አስባለሁ። የመጀመሪያውን ጎል ደግሞ የሚያስቆጥረው ሊቨርፑል ነው። ጨዋታውን ሳይጎረብጠው ያሸንፋል።

ግምት፡ 3 - 0

ውጤት፡ 2 - 2

ኒውካስል ከሌስተር

ሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐርን አሰናብቶ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ሩድ ቫን ኒስትልሮይን ሾመዋል። ሩድ የመጀመሪያ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል።

ወደ ኒውካስል ስንመጣ አሰልጣኝ ኤዲ ሀው የሚፈልጉትን አይነት የውድድር ዘመን እያሳለፉ ነው ማለት ከባድ ነው። ነገር ግን አርሰናልን አሸንፎ ከሊቨርፑል አቻ መውጣት የሚችል ቡድን ሊናቅ አይገባም።

የኤዲ ሀው ቡድን አንድ ወጥ ያላቸው ነገር ወጥ አለመሆናቸው ነው። ነገር ግን መሆን የሚፈልጉትን ለማሳካት ብዙም ሩቅ አይደሉም።

ኒውካስል ይህን ጨዋታ በቀላሉ ያሸንፋል ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 3 - 0

ውጤት፡ 4 - 0

ዎልቭስ ከኢፕስዊች

ዎልቭስ በዚህ ጨዋታ ጎል ያስቆጥራል? አዎ።

ኢፕስዊችስ በዚህ ጨዋታ ጎል ያስቆጥር ይሆን? ምናልባት። ምክንያቱም ዎልቭስ ላይ ሁሉም ቡድን ጎል እያስቆጠረ ነው።

እኔ ጫማዬን ከሰቀልኩበት አውርጄ ዎልቭስ ላይ ጎል ማስቆጠር ችላለሁ። የተከላካይ መስመራቸው ይህን ያህል ነው የተጎሳቆለው።

ዎልቭስ ተሰጥኦ ያሏቸው ተጫዋቾች ቢኖሩትም ይህን ያህል ጎል እየተቆጠረበት በፕሪሚዬር ሊጉ ይቆያል ማለት ዘበት ነው።

ኢፕስዊች ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ምንም ነጥብ ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ጨዋታ ዎልቭስ የተሻለ ነጥብ ያገኛል ብዬ አስባለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ውጤት፡ 1 - 2

ኖቲንግሀም ፎረስት ከአስተን ቪላ

ይህ በአምስተኛ ደረጃ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ጨዋታ ነው። ከባድ ፍልሚያ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።

አስተን ቪላ ከውጤት ቀውስ በኋላ የተሻለ ነገር ያሳዩን ጀምረዋል። በሳምንቱ አጋማሽ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተጫውተው ነው አሁን ወደ ሊጉ የተመለሱት። ይህ ደግሞ እየከበዳቸው የመጣ ይመስላል።

ኖቲንግሀም ፎረስት በሜዳቸው ሲጫወቱ ድል ይቀናቸዋል፤ አሊያም ለተቃራኒ ቡድን ከባድ ናቸው። በያዝነው የውድድር ዘመን ከሜዳቸውም ውጭ በተለይ በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ውጤታ ማምጣት ችለዋል።

በዚህኛው ጨዋታ ይሸፈናሉ የሚል እምነት የለኝም። ቪላም ይሸነፋል ብዬ አላስብም። ጨዋታው በአቻ ይጠናቀቃል ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ውጤት፡ 2 - 1

እሑድ

ብራይተን ከክሪስታል ፓላስ

ብራይተን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ብዙ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት እያጠናቀቀ ነው። በሜዳው አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ክሪስታል ፓላስ ደግሞ በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ 7 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ፓላስ ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ ወጥተዋል።

ይህ ጨዋታ ለግምት ከባድ አይመስለኝም። ግጥሚያው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 - 1

የሲቲ እና የዩናይትድ አርማ

ማን. ሲቲ ከማን. ዩናይትድ

ማንቸስተር ሲቲ እንዲህ ይንኮሻኮሻል ብሎ ማን ገመተ?

ሲቲ ካለፉት 10 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው ምንም ጎል ያልተቆጠረበት። አሰልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ ተጫዋቾቼ ደክሟቸዋል እያለ ነው።

የጉዋርዲዮላ ነገር አይታወቅም። አንዳንድ ጊዜ ግራ አጋቢ መልሶች ይሰጣል። ነገር ግን ማንቸስተር ሲቲ አሁን ያላቸው አቋም እጅግ አሳሳቢ ነው። ፔፕ እንዴት አድርጎ ነው ይህን የሚቀይረው?

በሌላ በኩል የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከተሾሙ ብዙም ሳይሆናቸው የክለቡ ባለቤት ሰር ጂም ራትክሊፍ የቡድኑ አባላት "ብቃታቸው እምብዛም ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

አሞሪም የስፖርቲንግ አሰልጣኝ ሆኖ የመጨረሻ ጨዋታውን ሲያደርግ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ማንቸስተር ሲቲን 4-1 መርታቱ ይታወሳል። ነገር ግን ወደ ኦልድ ትራፈርድ ከመጡ በኋላ ደጋፊዎች ደስተኛ ቢሆኑም ተጫዋቾቹ ከኤሪክ ቴን ሀግ የተለየ አቋም እያሳዩ አይደሉም።

ሁለቱም ቡድኖች አቋማቸው ላሽቋል። ይህን ጨዋታ ምን ብዬ ነው የምገምተው?

ባለፉት ጨዋታዎች በማንቸስተር ደርቢ ሲቲ ያሸንፋል ብዬ ነበር የምገምተው። በዚህኛውም ሲቲ በሜዳው ውጤት ይቀናዋል ልበል።

ኤሪክ ቴን ሀግ ለሁለት ዓመት በዩናይትድ በነበራቸው ቆይታ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፎ አያውቅም። አሞሪም በዚህ ጨዋታ ከተሸነፈ በአንድ ወር ውስጥ ይህን ማስታወስ የማይፈልገውን ክብረ-ወሰን ይሰብራል ማለት ነው።

ግምት፡ 3 - 1

የቼልሲ እና ብሬንትፈርድ አርማ

ቼልሲ ከብሬንትፈርድ

አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ብሬንትፈርድን የቀየሩበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነው።

ነገር ግን ይህ ፍልሚያ ለመገመት ቀላል ከሆኑ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም ንቦቹ (ብሬንትፈርድ) በሜዳቸው አናብስት ከሜዳቸው ውጭ ደግሞ ከባሕር የወጣ ዓሳ ናቸው።

ቼልሲ ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም። ይህ ጨዋታ እሑድ ምሽት 4፡00 ነው የሚደረገው። ይህ የሆነው ቼልሲ ሐሙስ ምሽት በአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ በመጫወቱ ነው።

ግምት፡ 2 - 1

ሳውዝአምፕተን ከቶተንሀም

ይህ ጨዋታ ጥሩ ኳስ የምናይበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ሳውዝአምፕተንም ሆነ ቶተንሀም ከሚታወቀው አጨዋወታቸው ውጭ ንቅንቅ የሚሉ አይደሉም።

ቶተንሀም ባለፈው ሳምንት በሜዳው በቼልሲ ተረትቷል። ምንም እንኳ ስፐርስ ለማየት ደስ የሚያሰኝ ኳስ ቢጫወቱም ውጤት ማምጣት አልቻሉም።

ሳውዝአምፕተን በፕሪሚዬር ሊጉ ላይቆዩ ይችላሉ። በዚህኛውም ጨዋታ ይሸንፋሉ።

ግምት፡ 1 - 2