“የአህያ ሥጋን ጨምሮ አጥንቱ ሳይቀር ወደ ቻይና ይላካል እንጂ አገር ውስጥ አይቀርም”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የሚገኘው የአህያ ማረጃ ቄራ የአህያ ምርቶች በሙሉ ለቻይና ገበያ የሚቀርብ እንጂ አገር ውስጥ የሚቀር ምርት የለም ሲል ለቢቢሲ ገለጸ።
ሮግቻንድ የተባለው የአህያ ማረጃ ቄራ አስተባባሪ የሆኑት ቺቺ አማን ቄራው በቀን ከ50 እስከ100 አህዮችን እያረደ ቆዳቸውን፣ ሥጋቸውን እና አጥንታቸውን ወደ ቻይና እንደሚልክ ተናግረዋል።
ድርጅቱ እንደሚለው ከአህዮች እርድ የሚገኙት ሁሉም ምርቶች “አንጥንታቸው እንኳ ሳይቀር ተፈጭቶ ወደ ውጪ ይላካል። እዚህ የሚቀር ምንም የለም” በማለት ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀር ነገር እንደሌለ አመልክቷል።
በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የአህያ ሥጋ ምርት ከበሬ ሥጋ ጋር ተመሳስሎ በልኳንዳ ቤቶች ለገበያ እየቀረበ ነው የሚል መረጃ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።
ይሁን እንጂ አቶ ቺቺ ይህ መረጃ “የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ነው” ያሉ ሲሆን፣ እርሳቸው የሚያስተዳድሩት ቄራ በግብርና ሚኒስቴር ክትትል እንደሚደረግበት ጭምር ተናግረዋል።
የአህያ ሥጋ፣ ቆዳ እና አጥንት በቻይና ገበያ ተፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ቁጥር አንድ ምክንያቱ የቻይና ባሕላዊ መድኃኒቶችነ ለመሥራት የሚረዳው ኢጂአኦ የተባለ ንጥረ ነገር በአህዮች ውስጥ ስለሚገኝ ነው።
ይህ ቄራ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአህያ ቆዳ፣ ሥጋ እና አጥንት ወደ ቻይና ሲልክ መቆየቱን የሚገልጹት አስተባባሪው፤ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ እያስገኘ ነው ይላሉ።
ይህ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቄራ ከዚህ ቀደም ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ተቃውሞዎች ተሰምተው ሥራው እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር።
በርካቶች በባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች የአህዮች መታረድን በመቃወም ድምጽ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አህዮች ለገጠሩ ማኅብረሰብ በተለይ ለሴቶች የሚሰጡትን ግልጋሎት እንዲሁም ሰብዓዊነትን ከግምት በማስገባት የአህያ እርድን የሚቃወሙ በርካቶች ናቸው።
አደጋ የተደቀነባቸው የኢትዮጵያ አህዮች
ብሩክ ኢትዮጵያ የተባለ የእንስሳት መብት ተሟጋችም ይህ የአህያ ማረጃ ቄራ እንዲዘጋ ድምጻቸውን ከሚያሰሙት መካከል አንዱ ነው።
የብሩክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቃሲም አህዮች ለቆዳቸው ሲሉ መታረድ የለባቸውም ይላሉ።
አቶ ዮሐንስ የአህያ እርድ በአገሪቱ ያሉትን የአህዮች ቁጥርን በከፍተኛ መጠን እንዲመናመን አድርጎ በሕብረተሰቡ ላይ ጫና ያሳድራል ይላሉ።
እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጸ ለቻይና የባሕል መድኃኒቶች ሲባል 4.8 ሚሊዮን አህዮች ያስፈልጋሉ። ለመድኃኒት ምርት ሲባል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አህዮች በቻይና ውስጥ በመታረዳቸው አገሪቱ 70 በመቶ የሚሆነውን የአህያ ቁጥሯን አጥታለች ይላሉ።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ጎረቤት አገር የሆነችው ኬንያም ከነበሯት አህዮች መካከል 15 በመቶውን እንዳጣች ጨመረው ገልጸዋል።
ስምንት ሚሊዮን ገደማ አህዮች እንዳሏት በምትገመተው ኢትዮጵያም የአህያ ቄራ ተስፋፍቶ የሚቀጥል ከሆነ የእንስሳቱ ቁጥር ላይ ከፍተኛ አደጋ ይደቅናል ሲሉ ያሰስባሉ።
እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ኮትዲቯር ባሉ አገራት ውስጥ የአህያ ቄራዎች መዘጋታቸውን በማስታወስ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበት አቶ ዮሐንስ መፍትሄ ያሉትን ጠቁመዋል።
“ከአህያ ቆዳ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ አህያ ለማኅብረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት የበለጠ ነው” የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ በኢትዮጵያ ሰዎች አህያን ለሸክም ብቻ ሳይሆን ለግብርና ሥራም ይጠቀማሉ ይላሉ።
የሮግቻንድ ጠአህያ ቄራ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቺቺ አማን ግን፣ ቄራው በኢትዮጵያ የሚገኙ አህዮችን ቁጥር ያመናምናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
ለእርድ ወደ እኛ የሚመጡት አህዮች “ከሞት የተነሱ ናቸው” በማለት ለእርድ የሚቀርቡት አህዮች አካላዊ የጤና ጉድለት ያለባቸው እና የአገልግሎት ዘመናቸውን እያጠናቀቁ ያሉ እንደሆኑ በመጥቀስ አገለግሎት የሚሰጡ አህዮች ለቄራው እንደማይቀርቡ ይናገራሉ።
“በጣም የተጎሳቆለ አገልግሎት የማይሰጥ ወንድ አህያ ነው ወደኛ የሚመጣው። ሴት አህያ እኛ ጋር ለእርድ አይቀርቡም።”
ጨምረውም “ገጠር ውስጥ ሰዎችን አደራጅተን ጀርባቸው የቆሰሉ፣ እግራቸው የተሰበረ ወይም ዐይናቸው ጠፍቶ ለአውሬ የተተዉ አህዮችን ፈልገን በመኪና ጭነን ነው የምናመጣቸው” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የወደፊት ዕቅድ
በኢትዮጵያ የአህያ ቄራ እንዲዘጋ የሚጠይቁ ድምጾች መሰማታቸው ቢቀጥልም በአገሪቱ ብቸኛ የሆነው ቄራ ግን ወደፊት ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸውን አህዮችን በማረድ “ለአገር የማስገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ አቅጄ እየሰራሁ ነው” ይላል።
በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 100 አህዮች እያረደ የሚገኘው ቄራ ወደፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ አህዮችን ለማረድ ዕቅድ እንዳለው የቄራው አስተባባሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጨምረውም ቄራው ለ250 ሰዎች የሥራ ዕድልን መፍጠሩን በማመልከት፣ በዚህም በአካባቢው የተደራጁ ወጣቶች ለእርድ የሚሆኑትን አህዮችን ፈልገው በመግዛት ለቄራው ያቀርባሉ።
የአህዮቹ ቄራ በአሁኑ ወቅት አንድ ለእርድ የሚቀርብ አህያን በአማካይ ከሁለት አስከ ሦስት ሺህ ብር በሚሆን ገንዘብ እንደሚገዛ አቶ ቺቺ ተናግረዋል።
የቄራው አስተባባሪው እንደሚሉት የአህዮቹ እርድ መከናወን እንዲችል ከአካባቢው ማኅብረሰብ ጋር ባለፉት ሁለት ዓመታት ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን በማንሳት “የአካባቢው ማኅበረሰብ ቄራው የእኔ ነው ብሎ አምኖ ተቀብሏል” ይላሉ።
ከሰሞኑ መነጋገሪያ የሆነውን ጉዳይም በተመለከተ በቄራቸው የሚታረዱ አህዮች ሥጋም ሆነ የትኛውም ተረፈ ምርት በተለያየ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ወደ ቻይና የሚላክ በመሆኑ በአገር ውስጥ ለሽያጭ የሚቀርብበት ዕድል እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።












