የናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ላይ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ ለማገት በመሞከር እና ጥቃት በማድረስ ተከሰሰ

ፖል ፔሎሴ ሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው ቤታቸው አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖል ፔሎሴ ሳንፍራንሲስኮ በሚገኘው ቤታቸው ሰረጎ በገባ ሰው ባለፈው አርብ ጥቃት ደርሶባቸዋል

የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ላይ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ ፔሎሲን ለማገት በመሞከር እና ባለቤታቸው ላይ ጥቃት በማድረስ ክስ ቀረበበት።

የ42 ዓመቱ ተከሳሽ ባለፈው አርብ ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘውን የጥንዶቹን መኖሪያ ቤት ሰብሮ በመግባት የ82 ዓመቱ ፖል ፔሎሲ ላይ በመዶሻ ጥቃት አድርሷል።

በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንደገባ አፈ ጉባኤዋን እየፈለገ እንደነበረ የተነገረ ሲሆን “ናንስሲ የታለች?” እያለ ይጣራ ነበርም ተብሏል።

ሆኖም በዚያን ዕለት ከፕሬዝዳንቱ በመቀጠል በአሜሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ፔሎሴ በቤት ውስጥ አልነበሩም።

ክስተቱ እየተመረመረ ቢሆንም ፖሊስ ድርጊቱን “በድንገት የሆነ” አይደለም ብሏል።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት፣ ዴቪዲ ዲፓፔ የተባለው ግለሰብ ላይ ትናንት ሰኞ ሁለት የፌዴራል ሕጎችን በመተላለፍ ክስ መስርቶበታል።

የመጀመሪያው የአሜሪካ ባለስልጣናትን በሥራቸው ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ማጥቃት የሚል እና እሰከ 30 ዓመት ሊያሳስር የሚችል ክስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፔሎሲን ለማገት መሞከር የሚል እና እስከ 20 ዓመት ሊያስፈርድ የሚችል ክስ ነው።

የሳንፍራንሲስኮ አውራጃ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በበኩሉ የግድያ ሙከራ እና አዛውንትን ማሰቃየት የሚልን ጨምሮ ተጨማሪ 6 ክሶችን መስርቶበታል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብሮክ ጄንኪንስ ጥቃቱ “ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው” ብለዋል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት ፕላስተር፥ ነጭ ገመድና መዶሻ ጨምሮ የተለያዩ ቁሶችን ይዞ እንደነበር የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ተጠርጣሪው ፔሎሲን በማገት “የሚዋሹት ከሆነ የጉልበታቸውን ሎሚ በመስበር” ጉዳት ሊያደርስባቸው ዕቅድ እንደነበረው ከፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።

በተጨማሪም ፔሎሲ የሚጎዱ ከሆነ በተሽከርካሪ ወንበር ወይም ዊልቼር ወደ ምክር ቤት ሲገቡ ለሌሎች ፖለቲከኞች መልዕክት ያስተላልፋል ሲልም ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ተናግሯል።

በዚያ ወቅት ዋሽንግተን ዲሲ የነበሩት የ82 ዓመቷ ፖለቲከኛ ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ በጥቃቱ ምክንያት በእጅና ትከሻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ባለቤታቸውን ለመጎብኘት ቀዶ ጥገና ወዳደረጉበት ሆስፒታል አምርተዋል።

ሁለቱ ጥንዶች እንደ አውሮፓውያኑ በ1963 ነበር ጋብቻ የመሰረቱት።

“ፖል ረጅም የማገገም ሂደት በሚፈልገው ህክምና መሻሻል እያሳየ ነው” ብለዋል ፔሎሴ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ።

ተጠርጣሪው ከአሜሪካ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዋና አንጋፋዋ ፖለቲከኛ ናንሲ ፔሎሲ በተጨማሪም ሌሎች ፖለቲከኞች ላይ ጥቃት የማድረስ ዕቅድ እንደነበረው ተሰምቷል።

ፖል ፔሎሲ እና ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተከሳሹ ሳንፍራንሲስኮ ወደ ሚገኝ እስር ቤት የተወሰደ ሲሆን ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

ጥቃት በደረሰበት ወቅት ባለቤታቸው ተኝተው እንደነበር እና መኝታ ክፍላቸው እስኪገቡ ድረስ ተጠርጣሪውን እንዳልተመለከቱት እንደነገሯቸው ፔሎሲ ተናግረዋል።

ከዚያም ባለቤታቸው ለተጠርጣሪው መጸዳጃ ቤት መሄድ እንደሚፈልጉ ነግረው ወደ 911 በግል ስልካቸው መደወላቸውንም ፔሎሲ አክለዋል።

ታዲያ ፖሊስ የፔሎሲ ባለቤት እና ተጠርጣሪው ሲታገሉ የደረሱ ሲሆን በያዘው መዶሻ ጉዳት አድርሶባቸው ነበር።

ፖሊስ ደርሶ ተጠርጣሪው የያዘውን መሣሪያ በሚያስጥሉበት ወቅት ፖል ፔሎሲ ራሳቸውን ስተው መሬት ላይ ወድቀው ነበር።

የአገሪቱ ምክር ቤትን ማን ይቆጣጠራል የሚለውን የሚወሰነው የማሟያ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ሳምንት ሲቀር የደረሰው ይህ ጥቃት ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶች ይበረክታሉ የሚል ስጋትን አጭሯል።

ይህ ጥቃት በተፈጸመ በሰዓት ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ምርጫውን ተከትሎ በእጩዎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች ፖለቲካዊ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ጽንፈኝነት በተሟላበት መልኩ የአገር ውስጥ ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለ በመጠቀስ የማሳሰቢያን መልዕክት አሰራጭቷል።

ቢቢሲ የተመለከተው እና በተጠርጣሪው ስም የተከፈተ ብሎግ፣ ድረ ገጽ እና ማኅበራዊ ገጾች አይሁድ ጠል የሆኑ፣ የተፈጸሙ እልቂቶችን የሚክዱ፥ የሴራ ትንታኔን የያዙ እና የቀኝ አክራሪዎችን ድረ ገጽ የሚጠቁሙ ይዘቶች ታይተውበታል።

በተጨማሪም ስለምርጫው ያልተረጋገጡ የማጭበርበር መረጃዎችን እንዲሁም የቀኝ አክራሪዎችን እና የጽንፈኞችን ነጥቦች አጋርቷል።

ጥቃቱን የተመለከቱ ያልተረጋገጡ መረጃዎችም በበይነ መረቦች ተስፋፍተው ታይተዋል።