በንግሥት ኤልዛቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የታደሙ አፍሪካውያን መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ሰኞ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. በተካሄደው የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥን የቀብር ሥነ ሥርዓት ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ውስጥ ታድመዋል።
ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች በዌስትሚኒስትር አቤ ተገኝተዋል።
ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ በለንደን ከተገኙ የአገራት እና የመንግሥታት መሪዎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደተገኙ በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ለደን በደረሱበት ዕለት በሐዘን መግለጫ መዝገብ ላይ መልዕክት ማስፈራቸው ተገልጿል።
አመሻሽ ላይ በተፈጸመው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በለንደን ከተማ ከተገኙ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል የደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎሳ፣ የኬንያው ዊልያም ሩቶ፣ የጋናው ናና አኩፎ አዶ፣ የታንዛኒያዋ ሱሉሁ ሳሚያ ሐሰን እና የሴኔጋሉ ማኪ ሳል ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Embassy of Ethiopia, London
በተጨማሪም የኮመንዌልዝ ሊቀ መንበር የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና በቅርቡ ኮመንዌልዝን የተቀላቀለችው ጋቦን መሮ አሊ ቦንጎም የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም ለንደን ተገኝተዋል።
በለንደን የተገኙት የተለያዩ አገራት መሪዎች ቁጥር ብዙ ስለሆነ በተለያየ መኪና መሄድ ስላልቻሉ በአንድ አውቶብስ እንዲሄዱ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አመራር ሰጥቷል።
አንዳንድ የሱዳን አክቲቪስቶች ወታደራዊ መሪው ጄኔራል አብደል ፈታ አልቡርሃን ወደ ለንደን መሄዳቸውን ተቃውመዋል።
ናይጄሪያ በምክትል ፕሬዝዳንቷ የሚ ኦስኒባጂ እንዲሁም ዚምባብዌ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፍሬድሪክ ሻቫ ተወክላለች። ዚምባብዌ በቅርቡ ነው ከኮመንዌልዝ የወጣችው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግን ‘ዘ ቢስት’ በሚባለው የግል ሊሞዚናቸው ነው ሥነ ሥርዓቱን የታደሙት።
የአፍሪካ መሪዎች በአውቶብስ ወደ ቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንዲጓዙ መደረጉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አነጋጋሪ ሆኗል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙት አፍሪካውያን መሪዎች መካከል የተወሰኑትን በምስል እነሆ፡















