የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት እና የመጨረሻ ስንብት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ አስክሬን ዛሬ ግብአተ መሬቱ ይፈጸማል።
የዓለም ርዕሳነ ብሔራት ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም ለንደን ገብተዋል።
የዛሬው የቀብር ሥነ ሥርዓት ታላቁ ዊንስተን ቸርችል ከ60 ዓመት በፊት ሲሸኙ ከታየው ሥርዓት ወዲህ በታላቅ ሐዘን የሚከናወን የመጀመሪያው የቀብር ሥነ ሥርዓት ይሆናል።
ንግሥቲቱ በግል በሥነ ሥርዓቱ እንዲካተቱላቸው የጠየቋቸው የኑዛዜ ኩነቶችም ይኖራሉ።
የዛሬ ሰኞ የዳግማዊት ኤልዛቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዝርዝር መርሐ ግብር እነሆ፦
የጊዜ ሰሌዳው በለንደን ሰዓት አቆጣጠር መሆኑን ልብ ይሏል።
06:30
የንግሥቲቱ አስክሬን በለንደን እምብርት በሚገኘው ዌስትሚኒቴር ታላቁ አዳራሽ ማረፉ ይታወቃል፤ ይህም እስከ ዛሬ ማለዳ ብቻ ይሆናል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላለፉት ቀናት ወደዚህ አዳራሽ ተሰልፈው እየገቡ የንግሥቲቱን አስክሬን ሲሰናበቱ እንደነበር አይዘነጋም።

08:00
እንግዶችን ለመቀበል የዌስትሚኒቴር አቤይ በሮች ይከፈታሉ።
የበርካታ አገራት ርዕሳነ ብሔራት በዚህ ሥነ ሥርዓት ለመገኘት የንጉሣዊ ቤተሰቡን ለማጽናናት፣ የንግሥቲቱን ሥራ እና ሕይወትን ለመዘከር ወደዚህ መትመመቻቸው ይታወቃል።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ታላላቅ ፖለቲከኞች እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም በዚሁ ሥፍራ ይገኛሉ።
ከንግሥቲቱ ጋር በደም የሚዛመዱና በልዩ ልዩ የአውሮፓ አገራት ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ።
የቤልጂየሙ ንጉሥ ፍሊፔ እና ንግሥት ማቲልዴ፣ የስፔኑ ንጉሥ ፌሊፕ እና ንግሥት ሌቲዚያ የተዘጋጀላቸውን የክብር ቦታ ይይዛሉ።

10:44
የዕለቱ ሥነ ሥርዓት በይፋ ይጀመራል። የንግሥቲቱ የአስከሬን ሳጥን ከተሸፈነበት ያጌጠ የክብር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ዌስትሚኒቴር አቤይ ይወሰድና ለቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጁ ይደረጋል።
አስክሬኑ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በዚህ የዌስትሚኒቴር አቤይ የክብር አዳራሽ ለሕዝብ ሽኝት መቀመጡ ይታወሳል።
አስክሬኑ በባሕር ኃይል የክብር ሰረገላ ታጅቦ ወደዚያው ያቀናል።
142 የባሕር ኃይል መኰንኖች ያጅቡታል።
ይህ የክብር ሰረገላ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው እንደነርሱ አቆጣጠር በ1979 ለልዑል ፍሊፕ አጎት ሎርድ ሞንትባተን ጊዜ ነበር።
አገልግሎት ላይ የዋለው ደግሞ የንግሥቲቱ አባት ጆርጅ አራተኛ በሞቱ ጊዜ ነው፤ ይህም እአአ በ1952 ነበር።
የባሕር ኃይል መኮንኖች ጋር አዲሱ ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ እና ልዑላኑ ዊሊያምና ሔሪ ይኖራሉ።

11:00
የንግሥቲቱ ይፋ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ 2000 እንግዶች ይገኛሉ። ይህም በዌስትሚኒቴር አቤይ ይከናወናል።
ሥነ ሥርዓቱ ብሔራዊ ደረጃ የሚከናወን ነው።
ይህም ለነገሥታት የሚደረግ ጥብቅ መመሪያና ፕሮቶኮል የሚከተል ይሆናል።
ይህ የጸሎተ ፍትሐት ሽኝት ሥነ ሥርዓት በአቤ አዳራሽ የሚከናወን ነው የሚሆነው።
አቤይ የብሪታኒያ ነገሥታት ዘውድ ሲጭኑ ሥርዓቱ የሚፈጸምበት ቦታ ነው።
ንግሥቲቱ በ1953 ዘውድ የጫኑትም እዚሁ ሥፍራ ነበር።
ከዘውዱ በፊትም ልዕልት ኤልዛቤጥና ልዑል ፊሊፕን በ1947 (እአአ) ጋብቻ የፈጸሙበት እጅግ የተከበረ ሥፍራ ነው።
በዚህ ሥፍራ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተፈጸመ ንጉሥ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የለም።
ይሁንና የንግሥቲቱ እናት ሲሞቱ በዚሁ ሥፍራ ሥነ ሥርዓቱ ተደርጎላቸዋል። ይህም በ2002 ነበር።
ይህ የፍትሐት ሥነ ሥርዓት በካንተንበሪው ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ቡራኬ ይመራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ሌሎች ሥነ ሥርዓቶችን ይመራሉ።
11:55
የሥነ ሥርዓቱ ማብቂያን ለማወጅ ሁለት ጊዜ ጡሩንባ ይነፋል። ይህን ተከትሎ የሁለት ደቂቃ አርምሞ ይደረጋል።
የብሔራዊ መዝሙር ይዘመራል። የሥነ ሥርዓቱ ማብቂያም ይታወጃል።
12:15
ይህን የፍትሐት ሥነ ሥርዓት ተከትሎ፣ የንግሥቲቱ አስክሬን በእግር ጉዞ ከዌስትሚኒቴር አቤይ ወደ ዊሊንግተን አርክ ይወሰዳል። ይህም ሃይድ ፓርክ ኮርነር የሚገኝ ነው።
የእግር ጉዞ ሽኝቱ በወታደርና በፖሊስ ሠራዊት የሚታጀብ ነው።
ግዙፉ የለንደን የሰዓት ማወጂያ ማማው፣ ቢግ ቤን በየአንድ ደቂቃው ደውል ያሰማል።
ከሃይድ ፓርክ የክብር መድፍም ይተኮሳል። ነዋሪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው የአስክሬን ሽኝቱን ሥነ ሥርዓቱን መመልከት ይችላሉ።
ንጉሥ ቻርለስ ሣልሳዊ ከተቀሩት የንግሣዊያን ቤተሰቦችና ልዑላን ጋር በመሆን የእግር ጉዞ ሽኝቱን አስክሬኑን ከያዘው ሰረገላ ጎን በመሆን ይመራሉ።
ካሚሊያ፣ የዌልሷ ልዕልት የሰሴክስ ሶፋኒት እና የተቀሩት ሉዑላን በተዘጋጀላቸው መኪና ይከተላሉ።

13፡00
አስክሬኑ ወደ ዊንድሶር ካስል ጉዞውን በሌላ የቤተ መንግሥት አስክሬን ማጓጓዣ ተሽከርካሪ እንዲዛወር ተደርጎ ወደዚያው ይወሰዳል።
ዊንድሶር ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ለንግሥቲቱ ልዩ ሥፍራ የነበረው ነው።
ለንጉሣዊያን ቤተሰቡም ላለፉት አንድ ሺህ ዓመታት ተፈራርቀው ኖረውበታል።
በተለይ ንግሥቲቱ ወጣት ሳለች ለንደን የቦምብ አደጋ ስጋት ላይ በነበረችበት ጊዜም ወደዚሁ ቤተ መንግሥት ተወስደው ነበር።
ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰ ጊዜም ንግሥቲቱ በዚሁ ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ እራሳቸውን አግልለው ነበር የከረሙት።
15:00
የአስክሬን መኪናው 5 ኪሎ ሜትሮችን ያህል በአጀብ ይጓዛል።
ይህም ወደ ዊንድሶር ካስል የሚደረግ ጉዞ ነው።
በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ንግሥቲቱን በጎዳናዎች ወጥቶ ካለበት ቦታ ሆኖ እንዲመለከት ይሆናል።
ንጉሡና ልዑላን ኳድራንግል አካባቢ በድጋሚ ብቅ ይላሉ።

16:00
አስክሬኑ ግብአተ መሬቱ የሚፈጸምበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይገባል።
ሴይን ጆርጅ ቻፕል ቤተ ክርስቲያን ወትሮም በንጉሣዊ ቤተሰቡ ለጋብቻም፣ ለክርስትናም ለቀብርም የሚመረጥ ነው።
የሰሴክስ መስፍን እና ሶፋኒት፣ ልዑል ሐሪ እና ሜጋን በ2018 የተጋቡት እዚህ ነበር። የንግሥቲቱ ባል ግብአተ መሬትም የተፈጸመው በዚህ ሥፍራ ነበር።
በዚህ ሥፍራ የሚኖረው ሥነ ሥርዓት 800 ሰዎች ብቻ የሚታደሙበት ይሆናል።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በካንተቤሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ቡራኬ ይመራል።
በዚህ ሥነ ሥርዓት የንግሥቲቱን መጨረሻ የሚያመላክቱ ሥነ ሥርዓቶች የሚንጸባረቁበት ይሆናል።
ለምሳሌ የንግሥቲቱ ዘውድ፣ አምባር እና የንግሥናቸው በትር በቤተ መንግሥቱ የጌጣጌጥ ባለሙያ ከአስክሬኑ ላይ በክብር ይነሳሉ።
ይህም ንግሥቲቱ ለመጨረሻ ጊዜ 70 ዓመታትን ከዘለቀ ንግሥናቸው መለያየታቸውን ያውጃል።
ከዚህ በኋላ “እግዚአብሔር ንጉሡን ይጠብቅ” (God Save the King) የሚለው ዝማሬ ይሰማል።
ይህ ዝማሬ እንዲዘመር ንግሥቲቱ በኑዛዜ ያስቀመጡት ነው ተብሏል።
16:45
የንጉሣዊያን ቤተሰብ በሙሉ የጸሎት ቤቱን ለቀው ይወጣሉ።
16:30
በዚያው ምሽት፣ ለቤተሰብ ብቻ በሚደረግ ሽኝት ንግሥቲቱ ግብአተ መሬታቸው ይፈጸማል።
አስክሬናቸው የሚያርፈውም የኤደንበራው መስፍን ከነበሩት ባለቤታቸው ጎን፣ በንጉሥ ጆርጅ አራተኛ መታሰቢያ መቅደስ ውስጥ ነው።
በመጨረሻም በመቃብሩ እምነ በረድ ላይ ዳግማዊት ኤልዛቤጥ (ከ1926-2022) የሚል ጽሑፍ ይታተማል።












