ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች፡ ፈረንሳይ ድል ሲቀናት አርጀንቲና እጅ ሰጥታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአምናዋ የዓለም ሻምፒዮና ፈረንሳይ ከመመራት ተነስታ 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አውስትራሊያን በማሸነፍ አጀማመሯን አሳምራለች።
ፈረንሳይ እንደካሪም ቤንዜማ፣ ንጎሎ ካንቴ እና ፖል ፖግባ ያሉ ኮከቦቿን በጉዳት አጥታ ነው ወደ ዓለም ዋንጫው ያቀናችው።
ትላንት በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታዋ በአውስትራሊያ ቀድሞ ጎል ተቆጥሮባታል። ክሬግ ጉድዊን ነው ጎሏን ለቢጫ ለባሾቹ ያስቆጠረው።
አድሪዬ ራቢዮ ሰማያዊዎቹን በ27ኛው ደቂቃ አቻ አደረገ። ኦሊቨር ዥሩ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ፈረንሳይ 2 ለ 0 በምምራት ወደ መልበሻ ክፍ አመሩ።
ምሽቱን ድንቅ ሆኖ ያመሸው ክሊያን ምባፔ ሦስተኛዋን ጎል አስቆጥሯል። ዥሩ አራተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 4 ለ 1 ተጠናቋል።
ዥሩ ለብሔራዊ ቡድኑ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ቁጥር 51 አድርሷል። በዚህም ከቲዬሪ ሄነሪ እኩል ለመሆን በቅቷል።
በዚሁ ምድብ አራት የሚገኙት ቱኒዝያ እና ዴንማርክ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይተዋል።
በርካታ የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ተጫዋቾችን ያሰለፉት ዴንማርኮች በኤጁኬሽን ስታዲየም ጠንካራ ፉክክር ገጥሟቸዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ያስቆጠሯቸው ጎሎች ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽረዋል።
በ95 ደቂቃ ኳስ ፍጹም ቅጣት ክልል ውስጥ በእጅ ተነክቷል በሚል ዳኛው ሜዳ ዳር የሚገኘውን ቴሌቪዥን ደጋግመው ቢመለከቱም ፍጹም ቅጣት ምቱን ለዴንማርክ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
የምድብ ሦስት ጨዋታዎችም ትላንት ነው የተከናወኑት።
በእግር ኳስ ታሪክ የጎላ ስም የሌላት ሳዑዲ አረቢያ ለዋንጫው የምትገመተውን አርጀንቲናን ማሸነፍ ችላለች።
ሳዑዲዎች በሉሳይል ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው አንድ ለባዶ ከመመራት በመነሳት ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ምድብ ሦስትን መምራት ጀምረዋል።
አርጀንቲና ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ሊዮኔል ሜሲ አስቆጥሮ አገሩን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር።
በአርጀንቲና በኩል በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ባደረጓቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ቢችሉም ከጨዋታ ውጪ በመሆናቸው ተሰርዘዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ በ10 ደቂቃ ውስጥ ሳዑዲ ውጤት ቀያሪውን ግብ አስቆጠረች።
ሳሌህ አል-ሼህሪ የመጀመሪያዋን ጎል ሲያስቆጥር ሳሌም አል ዳወሳሪ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑን አሸናፊ አድርጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምድቡ ደካማ ቡድን በሆነችው ሳዑዲ የተሸነፈችው አርጀንቲና ቀጣይ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በውድድሩ የሚኖራትን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ።
ሳዑዲ በታሪኳ ለዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የበቃችው በ1994 ነበር።
ሪያድ ደስታዋን ለመግለጽ አንድ ቀን አይበቃኝም ብላለች። ልዑል ሳልማን ረቡዕም ብሔራዊ በዓል ነው ሲሉ ደስታው እንዲራዘም ፈቃዳቸው ሆኗል።
ሜሲ እና አርጀንቲና ቀጣይ ጨዋታቸውን በሐዘን ለመጠበቅ ተገደዋል።
በምድቡ ሌላ ጨዋታ ሜክሲኮ እና ፖላንድ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
የፖላንዱ አምበል እና የጎል ቀበኛ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ አገሩን ለድል ልታበቃ የምትችል ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
በስታዲየም 974 በተደረገው ጨዋታ የሜክሲኮው ግብ ዘብ ጉሌርሞ ኦቾአ ፍጹም ቅጣት ምቱን አድኗል።
በርካታ የሜክሲኮ ደጋፊዎች የታደሙበት ጨዋታ ይህ ነው የሚባል ፉክክር ሳይታይበት ተጠናቋል።
ምድቡን ሳዑዲ ስትመራ ፖላንድ እና ሜክሲኮ ይከተላሉ።
ምድቡ ግርጌ ላይ የምትገኘው አርጀንቲና በቀጣይ ከሜክሲኮ ትጫወታለች።
የዓለም ዋንጫው ዛሬም ቀጥሎ ይካሄዳል።
የምድብ አምስት እና ስድስት ጨዋታዎች ዛሬ ይከናወናሉ።
ምድብ አምስት ላይ ጀርመን እና ጃፓን ይገናኛሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በኻሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም 10 ሰዓት ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ስፔን እና ኮስታሪካም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የአል ቱማማ ስታዲየም የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ አንድ ሰዓት ላይ ያስተናግዳል።
በምድብ ስድስት አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ከክሮሽያ ትጫወታለች።
ጨዋታው ቀን ሰባት ሰዓት በአል ባይት ስታዲየም ይከናወናል።
ቤልጂየም ደግሞ ካናዳን ትገጥማለች።
ምሽት አራት ሰዓት የሚከናወነው ጨዋታ በአህማድ ቢን አሊ ስታዲየም ይደረጋል።












