ዩክሬን ገደልኳቸው ያለቻቸው ጄኔራል በሕይወት መኖራቸውን ሩሲያ ‘በቪዲዮ አሳየች’

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን ገደልኳቸው ያለቻቸው ጄኔራል በሕይወት መኖራቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው ‘ቪዲዮ አሳየ’።
ዩክሬን በክሪሚያ፣ ሴባስቶፖል ውስጥ በሚገኘው የሩሲያ የባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ላይ የሚሳኤል ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት ነው የጦር አዛዡ ጄኔራል መገደላቸውን ያሳወቀችው።
ጄኔራሉ በጥቁር ባሕር የሚገኘው የሩሲያ የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ መሆናቸውም ተገልጿል።
በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ገጽ ላይ የወጣው እና ጄኔራል ቪክቶር ሶኮሎቭ የሚታዩበት ቪዲዮ መቼ እንደተቀረጸ ግን ግልጽ አይደለም።
ሚኒስቴሩ ባለንበት ሳምንት ማክሰኞ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገ ውይይት እንደሆነም አስፍሯል።
የዩክሬን ልዩ ኃይሎች በሴባስቶፖሉ የሚሳኤል ጥቃት ጄኔራል ቪክቶር ሶኮሎቭ እና ሌሎች 33 መኮንኖች መገደላቸውን ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።
ረቡዕ ዕለት በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያም ከጄኔራሉ ጋር የተደረገ የቪዲዮ ቃለ ምልልስ አሳይቷል።
በዚህ ቪዲዮ ላይም የጦር ጄኔራሉ በሴባስቶፖል የሚገኘው መርከብ በተሳካ ሁኔታ ተግባሯን እያከናወነች እንደምትገኝ ነው የተናገሩት።
ቪዲዮው መቼ እንደተቀረጸ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
ዩክሬን የጄኔራሉን ስም ባትጠቅስም የጦር አዛዡ ተገድለዋል ብላለች። ሆኖም መሞታቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃም አላቀረበችም።
ሩሲያ ጄኔራሉ በሕይወት መኖራቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ማውጣቷን ተከትሎም ዩክሬን ሪፖርቶቹን “እያጣራን ነው” ብላለች።
“እንደሚታወቀው በሩሲያ የጥቁር ባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ላይ በደረሰው የሚሳኤል ጥቃት 34 መኮንኖች ተገድለዋል” ሲል የዩክሬን ልዩ ኃይል ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
“በደረሰው ጉዳት ምክንያት የሞቱት ሰዎች አሁንም አልተለዩም” የሚል መግለጫን አክሏል።
በዚህ መግለጫ ምንጮችን በመጥቀስ የጦር አዛዡ አንዱ መሆናቸውን አመልክቶ ነበር።
ከተገደሉት መካከል አዛዡ አንዱ መሆናቸውን በእርግጠኝነት አሳውቃ የነበረችው ዩክሬን በአሁኑ መግለጫዋ መጠራጠር ታይቶበታል።
የዩክሬን አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ረስተም ኡሜሮቭ የጦር አዛዡ ቪክቶር ሶኮሎቭ ከሞቱ “ለሁሉም መልካም ዜና ነው” ሲሉ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታም የጄኔራሉን ሞት ማረጋገጥ አልቻሉም።












