ሩሲያ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነቷ እንዲመለስ እየሞከረች ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዩክሬን ወረራ ከፈጸመች በኋላ ከተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የተሰረዘችው ሩሲያ አባልነቷን ለማደስ እየሞከረች ነው።
የሩሲያ የአባልነቴ ይመለስ ጥያቄም ለሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ አቋሙን የሚፈትሽ ይሆናል።
የሩሲያ ዲፕሎማቶች አገራቸው ለሶስት ዓመታት በምክር ቤቱ አባልነት በድጋሚ እንድትመረጥም እየጣሩ ይገኛሉ ተብሏል።
ሩሲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላትም ድጋፍ እንዲሰጧት እየጠየቀችበት ያለውን የአቋም መግለጫ ቅጂም ቢቢሲ አግኝቷል።
ምርጫው በሚቀጥለው ወር ይካሄዳል።
በዚህ ሰነድ ላይ ሩሲያ “ለሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መፍትሄዎችን” ለማበጀት ቃል ገብታለች።
ምክር ቤቱ ውስን ያሏቸውን ሃገራት የፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ መሳሪያ እንዳይሆን ለማድረግም ሩሲያ ትሰራለች ይላል።
ሩሲያ በሰነዱ ላይ ውስን ብላ የጠቀሰቻቸው አገራት የምእራቡ ዓለምን ለማመላከት ነው።
በግዛቷም ውስጥ ሆነ በዩክሬን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተከሰሰች ያለችው ሩሲያ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ተዓማኒነትን ለማግኘት ተስፋ እያደረገች ትገኛለች።
ሩሲያ እየፈጸመቻቸው ያሉ ጥሰቶችን በተመለከተ የዩክሬን አጣሪ ኮሚሽን በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ሰላማዊ ሰዎችን ማሰቃየት፣ መድፈር እና ጥቃቶችን ጨምሮ የጦር ወንጀሎች ስለመቀጠላቸው የሚያሳዪ ማስረጃዎች እንዳሉም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ኤሪክ ሞሴ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሩስያ ልዩ ራፓርተር ማሪያ ካትዛሮቫ ከሁለት ሳምንታት በፊት ባወጡት ሌላ ሪፖርት በሩሲያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ ነው ብለዋል።
በዩክሬን የተፈጸመውን ወረራ በሚተቹ ሰዎች ላይ የዘፈቀደ እስራት፣ ማሰቃየት እና እንግልቶች እየተፈጸሙባቸውም እንደሆነም ሪፖርቱ ያስረዳል።
መቀመጫውን በጄኔቫ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት 47 አባላት ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ አባላትም ለሶስት ዓመታት የሚመረጡ ናቸው።
ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ሩሲያ ለማዕከላዊ እና ምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ተወካይነት በተዘጋጀው የምክር ቤቱ ሁለት መቀመጫም ከአልባኒያ እና ከቡልጋሪያ ጋር ትወዳደራለች።












