ከ100 በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ቡድኖች በጋዛ የጅምላ ረሃብ መኖሩን አሳወቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የረድኤት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዛ የጅምላ ረሃብ እንዳለ በማስጠንቀቅ መንግሥታት እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት እያደረጉ ነው።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች (ኤምኤስኤፍ)፣ ሴቭ ዘ ችልድረን እና ኦክስፋም ባልደረቦቻችን እና የጋዛ ነዋሪዎች "እያለቁ ነው" በማለት ተፈራርመው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ሁሉም የድንበር ማቋረጫ መንገዶች እንዲከፈቱ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ነፃ የእርዳታ ፍሰት እንዲኖር ጠይቀዋል።
ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ በሙሉ የምትቆጣጠረው እስራኤል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የምግብ እጥረት ተጠያቂ መሆኗን ታስተባብላለች።
መግለጫው የወጣው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ከእሁድ ጀምሮ 12 ሕጻናትን ጨምሮ 33 ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሞታቸውን ከገለጸ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምግብ እጦት ምክንያት በከፍተኛ የድካም ስሜት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን እና ሌሎችም በጎዳናዎች ላይ እየወደቁ ነው ብሏል።
"የእስራኤል መንግሥት ከበባ የጋዛን ሕዝብ በረሃብ ሲያጠቃ፣ የእርዳታ ሠራተኞች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ሲሉ ብቻ በእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለመሰለፍ እና በጥይት ለመመታት እየተጋለጡ ነው" ሲሉ 109 የሰብዓዊ ድርጅቶች ረቡዕ ዕለት በጋራ ያወጡት መግለጫ አመልክተዋል።
"አሁን አቅርቦቱ ሙሉ በሙሉ እየተሟጠጠ ባለበት ሁኔታ የሰብዓዊ ድርጅቶች የራሳቸው የሥራ ባልደረቦች እና አጋሮቻቸው ዓይናቸው እያየ እየጠፉ ነው።"
እስራኤል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ አጠቃላይ የእርዳታ አቅርቦትን ወደ ጋዛ እንዳይገባ በማገድ እና ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጥቃቷን አጠናክራ በመቀጠል ለሁለት ወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ስምምነት አፍርሳለች።
የኔታንያሁ አስተዳደር በዚህ መልኩ የቀሩት እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስፈታት በታጣቂው ቡድኑ ላይ ጫና መፍጠር እንደሚፈልግ ይናገራል።
ምንም እንኳን እገዳው ለሁለት ወራት ያህል ከቆየ በኋላ በከፊል የተነሳ ቢሆንም፣ የዓለማቀፍ ባለሙያዎች ረሃብ እያንዣበበ መሆኑን ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ባለበት ወቅት የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት ተባብሷል።
"ዶክተሮች በተለይ በሕፃናት እና በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መታየቱን ተናግረዋል። እንደ አጣዳፊ ተቅማጥ ያሉ ሕመሞች እየተስፋፉ ነው፤ ገበያው ባዶ ሆኗል፤ ቆሻሻ እየተከመረ ነው፤ ጎልማሶች በረሃብ እና በውሃ እጥረት በየጎዳናው ላይ እየወደቁ ነው" ሲሉ የሰብዓዊ ድርጅቶቹ አስጠንቅቀዋል።
"የሥነ ልቦና ማኅበራዊ ድጋፍን የሚሰጥ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ በልጆች ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ተጽዕኖ ሲናገር 'ልጆች ለወላጆቻቸው ወደ መንግሥተ ሰማይ መሄድ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። ምክንያቱም ቢያንስ መንግሥተ ሰማያት ምግብ አለው'" ብሏል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ እአአ ከግንቦት 27 ጀምሮ ከ1,050 በላይ ፍልስጤማውያን ምግብ ለማግኘት በሚጠብቁበት ወቅት በእስራኤል ጦር መገደላቸውን ሪፖርት ማድረጉን አስታውሰዋል።
በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን (GHF) የሚመራው አወዛጋቢው የእርዳታ ማከፋፈያ ዘዴ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሚመራው በተቃራኒ አማራጭ ሆኖ መንቀሳቀስ በጀመረ ማግስት በእርዳታ ማከፋፈያዎች አቅራቢያ በርካታ ግድያዎች ተመዝግበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው፣ በፋውንዴሽኑ አራት የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አካባቢ ቢያንስ 766 ሰዎች ተገድለዋል።
እነዚህ በእስራኤል ወታደራዊ ቀጣናዎች ውስጥ የሚገኙ እና በአሜሪካ የግል የደኅንነት ተቋራጮች የሚተዳደሩ ማከፋፈያዎች ናቸው። በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ ማከፋፈያዎች አቅራቢያ ደግሞ ሌሎች 288 ሰዎች ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን ጣቢያዎች አቅራቢያ የተሰማሩ ወታደሮቹ የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን ብቻ መተኮሳቸውን እና ሆን ብለው ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደማይተኩሱ ሲገልጽ፣ ፋውንዴሽኑ በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት የጋዛ የጤና ሚኒስቴር "ሐሰተኛ እና አሳሳች" አሃዞችን እየተጠቀሙ ነው ብሏል።
የሰብዓዊ ድርጅቶቹ በተጨማሪም ሁሉም የጋዛ ሕዝብ ተፈናቅሏል ማለት እንደሚቻል ጠቅሶ አሁን በእስራኤል የልቀቁ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ከ12 በመቶ ያነሰ ግዛት ወይም በእስራኤል ወታደራዊ ቀጠናዎች ውስጥ በመገደቡ የእርዳታ ሥራዎችን ለማከናወን አዳጋች እንዳደረገበት ገልጿል።
እናም በጋዛ በየቀኑ በአማካይ 28 የጭነት መኪናዎች እርዳታ ብቻ እየተከፋፈለ ነው ሲል አክሏል።
"ከጋዛ ወጣ ብሎ፣ በመጋዘኖች ውስጥ እና በጋዛ ውስጥ እንኳን በርካታ ቶን ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ የሕክምና አቅርቦቶች፣ የመጠለያ ቁሳቁሶች እና ነዳጅ የሰብዓዊ ድርጅቶች እንዳይደርሱባቸው ወይም እንዳያከፋፍሉ ታግዶ ተቀምጧል።"
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል አካባቢውን እንደተቆጣጠረ ኃይል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሰብዓዊ እርዳታ ለተቸገሩ ዜጎች ሁሉ እንዲደርስ የማድረግ ግዴታ አለባት ብሏል።
እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደምትሠራ እና እርዳታ ወደ ሐማስ እንዳይደርስ ስትከላከል መቆየቷን ትናገራለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለፍልስጤማውያን የሚደርሰው የአቅርቦት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አምና፤ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችን ተጠያቂ አድርጋለች።
ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ የሚያስተባብረው የእስራኤል ወታደራዊ አካል ሰኞ ዕለት በኤክስ ገፁ ላይ እንደፃፈው ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ወደ 4,500 የሚጠጉ እርዳታ የጫኑ መኪኞች ጋዛ ገብተዋል፤ ከእነዚህም መካከል 2,500 ቶን የሕፃናት ምግብ እና ከፍተኛ የካሎሪ ይዘት ያለው ልዩ የሕፃናት ምግብ ይገኝበታል።
በኬረም ሻሎም እና በዚኪም የድንበር ማቋረጫዎች በተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መወሰድ የነበረባቸው 950 እርዳታ የጫኑ መኪኖች መካከል ጥቂቶቹን የሚያሳዩ የድሮን ምሥሎችን ይፋ አድርጓል።
የእስራኤል ወታደራዊ አካል "የእርዳታ ክምችት ማነቆው ወጥ የሆነ የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገባ ዋነኛው እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል" ሲል ተናግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እርዳታዎቹን ከድንበር አካባቢ ለመውሰድ እና በወታደራዊ ቀጣናዎቹ ለማጓጓዝ በቀጠለው ግጭት፣ የነዳጅ እጥረት እና የእስራኤልን ፍቃድ በማግኘት ላይ ባለው ችግር ምክንያት ተግዳሮት እንደገጠመው አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊነት ቢሮ እንደገለጸው እአአ በሐምሌ 9 እና 15 መካከል፣ በጋዛ ዙሪያ የታቀዱ የእርዳታ እንቅስቃሴዎችን ለማስተባበር ከ66 ሙከራዎች ውስጥ 17 በመቶ የሚሆኑት በእስራኤል ባለሥልጣናት ውድቅ ሆነዋል።
ተጨማሪ 33 በመቶ ያህሉ በመጀመሪያ ተቀባይነት አግኝተው ነገር ግን እገዳዎች ወይም መዘግየትን ጨምሮ ሌሎች እንቅፋቶች አጋጥሟቸዋል፤ እና 5 በመቶ በሎጂስቲክስ፣ በአሠራር ወይም በደኅንነት ችግሮች ምክንያት መስተጓጎል ገጥሟቸዋል።
የሰብዓዊ ድርጅቶቹ መንግሥታት "ቆራጥ እርምጃ ካልወሰዱ፤ አሁን ባሉት የአሠራር ሂደቶች ተግባራዊ ይሆናል ብለን ተስፋ ማድረግ አንችልም" ብለዋል።
"አፋጣኝ እና ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እንጠይቃለን፤ ሁሉም የቢሮክራሲያዊ እና የአስተዳደር ገደቦችን ይነሱ፤ ሁሉንም የድንበር መሻገሪያ መንገዶች ይከፈቱ፤ በጋዛ ያሉ ሁሉንም ሰዎች መድረስ መቻላችን ይረጋገጥ።
"በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ያሉ የሥርጭት መንገዶች ይነሱ፤ በመርኅ ላይ የተመሠረተ በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ የሰብዓዊ እርዳታ ወደነበረበት መመለስ እና በመርኅ ደረጃ እና በገለልተኛ የሰብዓዊ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይቀጥል።"
አክለውም "አገራት ከበባውን ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው፤ ለምሳሌ የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች ማስተላለፍን ያቁም" ብለዋል።
ሰኞ ዕለት 28 አገራት በጋዛ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫው "ከእውነታው የራቀ እና የተሳሳተ መልዕክት ለሐማስ ያስተላልፋል" ብሏል።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 ሰዎች ካገተ ወዲህ የእስራኤል ጦር በጋዛ መጠነ ሰፊ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።
በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 59,106 ሰዎች ተገድለዋል።















