የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት 'ደኅና ሥፍራ' መደበቃቸውን ተናገሩ

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሬ ሮሃሊና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሬ ሮሃሊና ካለፈው ረቡዕ በኋላ ከዕይታ ተሰውረዋል

ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ለሳምንታት የቀጠለ ተቃውሞ የገጠማቸው የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሬ ሮሃሊና የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ "አስተማማኝ ሥፍራ" መደበቃቸውን ተናገሩ።

በፌስቡክ የትስስር ገፅ በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት የ51 ዓመቱ ፕሬዝዳንት "የወታደራዊ መኮንኖች እና የፖለቲከኞች ቡድን እኔን ለመግደል ዕቅድ ነድፏል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት አንድሬ ሮሃሊና ያሉበትን ሥፍራ ባይገልፁም ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች በፈረንሳይ ወታደራዊ አውሮፕላን አገራቸውን ጥለው መኮብለላቸውን ያመላክታሉ።

በዋናነት በወጣት ሰልፈኞች ለተከታታይ ሳምንታት የተደረገው አገራዊ ተቃውሞ ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ማንሳትን ዒላማ አድርጓል።

ፕሬዝዳንቱ ካቢኔያቸውን በመበተን እና ሌሎች እርምጃዎችን በመውሰድ "ጀን ዚ ማዳ" በመባል የሚታወቁትን ወጣት ተቃዋሚዎች ለማረጋጋት ያደረጉት ጥረት አልሰመረላቸውም።

ካለፈው ረቡዕ በኋላ ከሕዝብ ዕይታ የተሰወሩ ሲሆን በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት ቢሯቸው ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣናቸው ለማስወገድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብሏል።

በሕንድ ውቅያኖስ በምትገኘው ደሴት ወታደሮች ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያውን እንቆጣጠራለን ብለው መዛታቸውን ተከትሎ ሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንቱ ሊያደርጉት የነበረው ንግግር ለበርካታ ገዜ ተስተጓጉሏል።

በስተመጨረሻም በፌስቡክ ባሰራጩት ንግግር "ከመስከረም 25 [መስከረም 15/2018 ዓ.ም.] ጀምሮ የግድያ እና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጎብኛል። የወታደራዊ መኮንኖች እና የፖለቲከኞች ቡድን እኔን ለመግደል ዕቅድ አውጥቷል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ራሴን ለመጠበቅ አስተማማኝ ሥፍራ እንደፈልግ ተገድጃለሁ"።

"እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው። ይህም በአገሪቱ ውስጥ አገለግሎት ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማክበር ነው" ብለዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ ፕሬዝዳንት ሮሃሊናን እ.አ.አ በ2009 ወደ ሥልጣን እንዲመጡ የረዳው 'ካፕሳት' የተባለው የጦር ሠራዊቱ ጠንካራ ክፍል ራሱን የጦር ኃይሎች አዛዥ አድርጎ በመሾም የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን ያዳከመ ሲሆን፤ አንዳንድ ወታደሮች ደግሞ በዋና ከተማው አንታናናሪቮ ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።

ሰኞ ዕለት የወታደራዊ አዛዦች ስብሰባን ተከትሎ በ'ካፕሳት' የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ተደርገው የተሾሙት ጀነራል ዶሞተን ፒኮላስ የፀጥታ ኃይሎች በአገሪቱ ሕግ እና ሥርዓትን ለመመለስ እየሰሩ እንደሆነ ለሕዝብ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ጀነራሉ ቀውሱን ለመፍታት ሰኞ ምሸት በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው መገኘታቸው ታውቋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ለቢቢሲ ማዳጋስካር አሁን ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ ሥርዓት እየተመራች ነው ብለዋል።

የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራቫሎማናን ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አጋራችም ወደ ጎረቤት ሞርሺየስ መኮብለላቸው ተነግሯል።

ማዳጋስካር ምንም እንኳ በተፈጥሮ ፀጋ የተትረፈረፈች አገር ብትሆንም በዓለም በጣም ደሃ ከሆኑ አጋራት መካከል አንዷ ናት።

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው 75 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ከድህነት ወለል በታች ይኖራል።

ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ በውሃ እና መብራት መቆራረጥ ምክንያት ቁጣቸውን መግለፅ ቢጀምሩም፤ በኋላ ላይ በሥራ አጥነት፣ሙስና እና በኑሮ ውድነት ምክንያት በፕሬዝዳንቱ እና መንግሥታቸው ላይ ተቃውሞው ተቀጣጥሏል።