የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቀው የአዲሱ ትውልድ ተቃውሞ እንዴት እዚህ ደረሰ?

ጭንብል የለበሱ እና መነጽር ያደረጉ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Gamma-Rapho via Getty Images

ባለፈው ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ የማዳጋስካር ዜጎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ጎዳናዎችን ተቆጣጥረው አሳልፈዋል።

በኢንዲያን ውቅያኖስ በምትገኘው የደሴት አገር ውስጥ የተካሄደው ከፍተኛ የተቃውሞ ማዕበል፤ ባለፉት 15 ዓመታት ያልታየ ነው።

በመሠረታዊ የውሃ እና አቅርቦቶች እጥረት ምክንያት የተነሳው ቁጣ በፍጥነት ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆሊና ከባድ ፈተና ሆኗል። ከ2018 ጀምሮ ለሁለት ጊዜ ፕሬዝዳንት የሆኑት ራጆሊና ለተነሳባቸው ተቃውሞ መልስ ለመስጠት በሚል መንግሥታቸውን በትነዋል።

የአዲሱ ትውልድ አባላት፣ "ጄን ዚ"ዎቹ የማዳጋስካር ሰልፈኞች ግን በዚህ አልረኩም፤ አሁን ተቃውሟቸው ፕሬዝዳንቱም ጭምር ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቅ ሆኗል።

በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሰረት ተቃውሞ ከተነሳ ወዲህ ቢያንስ 22 ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። የአገሪቱ መንግሥት ግን "በአሉባልታ እና ሀሰተኛ መረጃ" ላይ የተመሰረተ ሲል ይህንን የተጎጂዎች ቁጥር ተቃውሞታል።

ተቃውሞውን ምን ቀሰቀሰው?

ተቃውሞው መቀጣጠል የጀመረው ሁለት ታዋቂ ፖለቲከኞች በመስከረም 9/2017 ዓ.ም. ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ፖለቲከኞቹ፤ በአገሪቱ እየታየ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውሃ አቅርቦት ችግር የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ ለማካሄድ አቅደው ነበር።

ንብረትነቱ የመንግሥት የሆነው 'ጂራማ' የተሰኘ የኤሌክትሪክ እና ውሃ አቅራቢ ኩባንያ በየቀኑ ለሰዓታት የሚያቀርበውን አገልግሎት እያቋረጠ ነበር።

በርካታ የአገሪቱ ዜጎች፤ የፖለቲከኞቹን መታሰር ህጋዊ ተቃውሞን ለማፈን እንደተደረገ ሙከራ ስለቆጠሩት ጉዳዩ ህዝባዊ ቁጣን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። እርምጃው የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች ጥያቄውን እንዲያስቀጥሉት እና "ጄን ዚ ማዳ" የተባለው በወጣቶች የሚመራ የኦንላይን እንቅስቃሴ እንዲፈጠር አድርጓል።

ተቃውሞው በዋና ከተማዋ ብቻ የተገደበ አልነበረም። በአገሪቱ በሚገኙ ስምንት ከተሞችም ተስፋፍቷል። እስካሁንም የመርገብ ሁኔታ አልታየበትም።

መፈክሮቻቸውን ከፍ አድርገው አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች የአገልግሎት መቆራረጡን ተቃውመዋል። መንግሥታቸው መሠረታዊ መብትን ለማስጠበቅ እንዳልቻለ በመንሳትም ወቅሰዋል።

አክቲቪስቶች ደግሞ በኩባንያው ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና ለተፈጠረው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ቀውስ ምክንያት እንደሆነ በማንሳት ወንጅለዋል።

ሰልፈኞቹ እነማን ናቸው?

ጄን ዚ የሚል መፈክር የያዘ ሰልፈኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጄን ዚ ማዳ በመባል የሚጠሩት አዲሱ ትውል አባላት ተቃውሞው እንደተጀመረ ራሳቸውን ሲያደራጁ የነበረው እንደ ፌስቡክ እና ቲክ ቶክ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በመጠቀም ነው። የጄን ዚ ማዳ አባላት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች እና ታዋቂ ፖለቲከኞች የጋራ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ የሚካሄዱትን ሰልፎች የሚያስተባብር ኮሚቴ አዋቅረዋል።

ተቃውሞው ከተጀመረ በኋላም ሌሎች ቡድኖች እንቅስቃሴውን ተቀላቅለዋል። በአገሪቱ ትልቁ የሆነውን 'ማላጋሳይ ትሬድ ዩኒየን ሶሊዳሪቲ'ን ጨምሮ በርካታ የሠራተኛ ማህበራት በወጣቶች ለሚመራውን እንቅስቃሴ አስተዋጾ አድርገዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች "ማዳጋስካር ወደ ቀውስ ወይም የእርስ በእስር ጦርነት እንዳትገባ ለመከላከል" በቤተ ክርስቲያ የሚመራ ንግግር እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሲቴኒ ራንድሪአናሶሎአይኮ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማርክ ራቫሎማናና ረዕቡ ዕለት ባልተለመደ መልኩ ባጋራ ባወጡት መግለጫ ለተቃውሞው ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

ሁለቱ ፖለቲከኞች የማዳጋር ህዝብን "መክዳት ነው" በማለት የራጆሊናን መንግሥት እንዲቀላቀሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

የተቃዋሚዎቹ ፍላጎት ምንድነው?

ሰልፈኞቹ ዓላማቸውን ዘርዝሮ ያስቀመጠ ማኒፌስቶ ይፋ አላደረጉም። ይሁን እንጂ በህዝብ አገልግሎት ምክንያት የተነሳው ቁጣ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲደረግ ወደሚጠይቅ ሰፊ ተቃውሞ አድጓል።

አስተማማኝ ባልሆነ እና ዝቅተኛ ገንዘብ በሚከፍል ስራ እድል የተማረሩት በርካታ የማዳጋስካር ወጣቶች፤ እያጋጠማቸው ላለው ችግር ተጠያቂ የሚያደርጉት ፕሬዝዳንቱን ነው። ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱም እየጠየቁ ነው።

ረዕቡ ዕለት በዋና ከተማዋ በተደረጉ ተቃውሞዎች ላይ "ራጆሊና ውጣ" የሚሉ ቃላትን ያዙ ባንዲራዎች እና መፈክሮች ታይተዋል።

የጄን ዚ ማዳ ቃል አቀባይ፤ ፕሬዝዳንቱ እንዲወርዱ እና "ብሔራዊ ምክር ቤቱ እንዲጸዳ" እንደሚፈልጉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።

በተጨማሪም ራጆሊና፤ ተቃውሞው ምክንያት በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ለተባሉት ሰዎች ሞት ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ይፈልጋሉ።

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የምርጫ ኮሚሽን እና የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲበተኑ ጠይቀዋል።

የፕሬዝዳንት ራጆሊና መንግሥት ምን ምላሽ ሰጠ?

የወታደር ሪፎርም እና ጭንበል ያደረገ የጸጥታ ኃይል መሳሪያ ይዞ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የጸጥታ ኃይሎች በመዲናዋ አንታናናሪቮ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ከፍተኛ መጠን ተሰማርተዋል። ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን አስለቃስ ጭስ እና የውሃ መርጫ መሳሪያ (water cannon) ተጠቅሟል።

በዋና ከተማዋ የገንዘብ ሚኒስቴር ቢሮዎችን በእሳት ማቀጣጠልን ጨምሮ ሌሎች የአመጽ እና የዝርፊያ ተግባራት እየተከናወኑ ነው መባሉን ተከትሎ ከአመሻሽ እስከ ንጋት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ተጥሏል።

ፕሬዝዳንት ራጆሊና በቅድሚያ የወሰዱት ተቃዋሚዎች ያረጋጋሉ ያሏቸውን እርምጃዎች ነበር። መንግሥታቸውን መበተኑን ፕሬዝዳንቱ፤ ከወጣቶች ጋር ንግግር ለማድረግ ጥሪ አቅርበው ነበር። የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ለማስቀረት ለሚደረገው ጥረት የሚውል ገንዘብ ከዓለም ባንክ እንዲገኝም ሲናገሩ ተደምጠዋል።

እነዚህ እርምጃዎች ሰልፈኞቹን ማረጋጋት ሲያቅታቸው ግን አካሄዳቸውን ቀየሩ።

ፕሬዝዳንቱ በፌስቡክ ገጻቸው በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ተቃዋሚዎች "መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ መጠቀሚያ ሆነዋል" በማለት ከስሰዋል። የውጭ ኃይሎች እርሳቸውን ከስልጣን ለማንሳት በሚል ተቃውሞውን በገንዘብ እንደደገፉም አንስተው ወንጅለዋል።

አመጽ እንዳይስፋፋ በመሰጋቱ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በዋና ከተማዋ እና በአቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

ባለሥልጣናት ይፋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚደረጉ ስብሰባዎች ለሕዝብ ደህንነት ስጋት እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ሕይወት ማዳጋስካር ውስጥ ምን ይመስላል?

ማዳጋስጋር በዓለም ላይ ከሚገኙ ደሃ አገራት አንዷ ነች። 75 በመቶ ሚሆነው ህዝቧም ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ መረጃ ደግሞ ማዳጋስጋር ካላት 30 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ የአሌክትሪክ አቅርቦት የሚያገኘው አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ መሆኑን ያመለክታል።

አንድ ሰልፈኛ "የማዳጋር ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ቀን በቀን እያሽቆለቆለ እና እየባሰበት እንደሄደ" ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

ፕሬዝዳንቱ ስጋት ውስጥ ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፖለቲካ ተመራማሪ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ኬታካንድሪያና ራፊሮቶሰን ለኤኤፍፒ እንደተናገረችው፤ ባለስልጣናት ተቃውሞን ለማፈን ኃይል መጠቀምን የሚመርጡ ከሆነ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን ሊያራዝሙ እና ሊያባብሱት ይችላሉ።

"ውጤቱ የፖለቲካ መከፋፈልን፣ አለ ትበሎ የሚታሰብን የውጭ ጣልቃ ገብነት በተመለከተ ጠንካራ ብሄርተኛነት እና ኢኮኖሚያዊ መዘዞችን ያስከትላል" ትላለች።

ነገር ግን መንግሥት ሰዓት እላፊ መጣሉ እና የተባበሩት መንግሥታት የጉዳት ሪፖርቶችን ውድቅ ማድረጉ ወደ ስምምነት ከመምጣት ይልቅ አፈናን በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል የሚያመለክት ሊሆን እንደሚችል ጠቁማለች።

ፕሬዝዳንት ራጆሊና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እና ቁልፍ ተቋማት ላይ ያላቸው ቁጥጥር አሁኑን የተቃውሞ ማዕበል እንዲያልፉ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።

የስነ መንግሥት ባለሞያዎች ደግሞ ወታደራዊው አካል ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚሰጠውን ትዕዛዝ የማይቀበል ከሆን ወሳኝ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ይላሉ።

የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ሎቫ ራኖሮማሮ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፉት ጽሁፍ፤ "መፈንቅለ መንግሥት አንፈልግም፤ ምክንያቱም መፈንቅለ መንግሥት ሀገርን ያጠፋል፤ ምክንያቱም መፈንቅለ መንግሥት የልጆቻችንን የወደፊት ተስፋ ያጠፋል" ብለዋል።

ማዳጋስካር እ.አ.አ በ1960 ነጻነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ህዝባዊ አመጾችን አስተናግዳለች። በአውሮፓውያኑ በ2009 የቀድሞው ፕሬዚዳንት ራቫሎማናና ወርደው ራጆሊና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ያደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠቃሽ ነው።

ራጆሊና በ2018 እና በ2023 በተካሄዱት ምርጫዎች አሸንፈዋል። ይሁን እንጂ ምርጫዎቹ ጥያቄ የሚነሳባቸው እና ተቃዋሚዎች ያልተሳተፉባቸው ናቸው።