የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት በወጣቶች ተቃውሞ ምክንያት መንግሥታቸውን በተኑ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ውሃ እና መብራት ለረዥም ጊዜ በመቋረጡ ምክንያት የተቀሰቀሰውን የማዳጋስካር ወጣቶች ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግሥታቸውን እንደሚበትኑ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ አንድሪ ራጆሊና ሰኞ ዕለት በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ "የመንግሥት አባላት የተሰጣቸውን ሥራ አላከናወኑ እንደሆነ ለዚህ ዕውቅና እንሰጣለን፤ ይቅርታም እንጠይቃለን" ብለዋል።
"ጄን ዚ" በመባል የሚጠሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት የአዲሱ ትውልድ አባላት በተቃውሞ ሰልፍ የአገሪቱን ከተሞች ማጥለቅለቅ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነበር።
በአብዛኛው ወጣት የሆኑት ተቃዋሚዎች "መኖር እንጂ ዕለት ተዕለት ከሚያጋጥመን ችግር እየተረፍን ሕይወታችንን መግፋት አንፈልግም" የሚል ሐሳብ ያለው መፈክር ሲያሰሙ ሰንብተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኃላፊ፤ የአገሪቱ ጸጥታ ኃይሎች ተቃውሞውን ለመቆጣጠር በተጠቀሙት "አላስፈላጊ የሆነ ኃይል" ምክንያት ቢያንስ 22 ሰዎች እንደተገደሉ እንዲሁም 100 ሰዎች እንደቆሰሉ አስታውቀዋል።
የማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በተባበሩት መንግሥታት ተቋም የወጣው ቁጥር "በአሉባልታ ወይም የተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው" በማለት ውድቅ አድርጎታል።
በአገሪቱ በዋና ከተማ አንታናናሪቮ የተጀመረው ተቃውሞው በስምንት ከተሞች ተስፋፍቷል።
በዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ አመጽ እና ዘረፋ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ከአመሻሽ እስከ ንጋት ድረስ የሚቆይ ሰዓት እላፊ ተጥሏል። ፖሊስ የተሰበሰቡ ሰዎችን ለመበተን የፕላስቲክ ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ፤ በጸጥታ ኃይሎች ኃይል የቀላቀለ እርምጃ መደናገጣቸውን ገልጸዋል። ሰልፈኞች ሲታሰሩ እንዲሁም ሲደበደቡ እና ጥይት ሲተኮስባቸው መልከታቸውንም ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ "የጸጥታ ኃይሎች አላስፈላጊ እና ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ እንዲሁም በዘፈቀደ የታሰሩ ተቃዋሚዎችን በሙሉ በአስቸኳይ እንዲለቅቁ አሳስባለሁ" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሞቱት መካከል "በጸጥታ ኃይል አባላት የተገደሉ ተቃዋሚዎች እና ተሳትፎ ያልነበራቸው ሰዎች" ይገኙበታል። "ሌሎች ደግሞ ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት በሌላቸው ግለሰቦች እና ወንበዴዎች በተስፋፋ ጥቃት እና ዘረፋ ተገድለዋል" ብሏል።
የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ሥራውን በአግባቡ አላከናወነም ያሉትን የኢነርጂ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ከኃላፊነት አንስተዋል።
የተቃዋሚዎች ፍላጎት ግን ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የቀሩት የአገሪቱ መንግሥት አመራሮች ከሥልጣን እንዲወርዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህንን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ሰኞ ዕለት ጎዳናዎችን ተቆጣጥረዋል።
ፕሬዝዳንት ራጆሊና በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው "ቁጣውን፣ ሀዘኑን እንዲሁም በኃይል መቋረጥ እና በውሃ አቅርቦት ምክንያት የተፈጠረውን ችግር እረዳለሁ" ብለዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና [የተቀረውን] የመንግሥት አካል ማባረራቸውንም" ገልጸዋል።
አዲሱ መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ባሉት ቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ውስጥም ራሳቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያቀርቡ ሰዎች ጥቆማ እንደሚሰበሰብም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከወጣቶች ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ ከታዩት መፈክሮች አንዱ "ችግር አልፈልግም፤ የምንፈልገው መብታችንን ብቻ ነው" የሚል ነበር።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ባለፈው ሳምንት የወጡ ተቃዋሚዎች ቢያንስ የሁለት የምክር ቤት አባላትን መኖሪያ አውድመዋል። ሰልፈኞቹ ይህንን ያደረጉት ቤቶቹን በእሳት በማያያዝ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
የ "ጄን ዚ" እንቅስቃሴ መሪዎች በበኩላቸው ተከፍሏቸው የመጡ ወንበዴዎች የወጣቶቹን ተቃውሞ ለመጥለፍ የተለያዩ ሕንጻዎችን ዘርፈዋል በማለት ከስሰዋል።
ማዳጋስካር በአውሮፓውያኑ 1960 ነጻነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አመጾችን አስተናግዳለች። በ2009 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማርክ ራቫሎማናና ሥልጣናቸውን ለቅቀው የአሁኑ ፕሬዝዳንት ራጆሊና ወደ መንበሩ የመጡትም በርካታ ሰዎች በተሳተፉበት ተቃውሞ ነው።
የአሁኑ ተቃውሞ ፕሬዝዳንቱ በ2023 ለሦስተኛ ጊዜ ከተመረጡ ወዲህ ያጋጠማቸው ትልቁ ተግዳሮት ነው።












